Monday, 16 August 2021 00:00

የሕዋ ጌቶች፣ ምን ያመሳስላቸዋል?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

• ሦስቱም ግለሰቦች፤ ከ20 ዓመታት ልፋትና ውጣውረድ በኋላ የህዋ ጌትነታቸውን እያስመሰከሩ ነግሰዋል- ሃያላን መንግስታት ያልቻሉትን ነገር እየሰሩ፣      አዲስ የሰው ልጅ ታሪክ በግለሰቦች ስኬት አድምቀው እየጻፉ ነው።
   •ሦስቱም በየፊናቸው በቅርበት የሚያውቁት አርአያ አላቸው። የኢሎን ሞስክ አያት በባለ አንድ ሞተር የግል አውሮፕላን ከአፍሪካ ወደ አውስትራሊያ      ውቅያኖስ የተሻገሩ የመጀመሪያ አብራሪ ናቸው።
   •የጄፍ ቤዞስ አያት፣ ለታሪከኛው የጨረቃ የጠፈር ጉዞ፣ የሮኬት ስራ ላይ በሃላፊነት የተሳተፉ ባለሙያ ናቸው። ቤዞስ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን      በአንደኛነት ሲያጠናቅቅ፣ መድረክ ላይ ወጥቶ ተናግሯል። የ18 ዓመት ወጣት ነበር። ያኔ ያቀረበው ንግግር፣ የጠፈር ጉዞና ፣ በጠፈር የሰው ሰፈራ ላይ           ያተኮረ ነው።
   •ሪቻርድ ብሮንሰን፣ … ከደጃፉ በሰፈሩ፣ የአውሮፕላን በረራ እያየ ነው ያደገው። የስሌት መንገድ በነጻ ገበያና በግል ቢዝነስ መንገድ መሆኑም የሦስቱ      ግለሰቦች በተግባር ያሳየሉ።
            

             በወጣትቷ፣ ዳንስ እየተማረች በነበረችበት ወቅት ነው፤ ህይወቷን የሚቀይር አጋጣሚ የተፈጠረው። አስባው አልማው አታውቅም። የአየር ኃይል ማስታወቂያ አየች። ነገርዬው፣ ለወንዶች ብቻ ነበር የሚፈቀደው። እናም፣ ወንድ ለመምሰል፣ አለባበሷን ለወጠችና ሄደች። የአብራሪዎች አሰልጣኝ ለመሆን ተወዳደረች። በእርግጥ፣ ማብረር ይቅርና፣ አውሮፕላን ተሳፍራ አታውቅም። ቢሆንም፣ ደፍራ ገባችበት።
ተፈቀደላትና አብራሪነቷ የሚታይበት ሰዓት ደረሰ። ቀላል በረራ አልሆነላትም። እንዲያውም፣ ለትንሽ ነው የተረፈችው። በዝግታ ማረፍ አልቻለችም። የአውሮፕላን ማረፊያው ላይ ባትከሰከስም፣ ክፉኛ ተላተመች፤ እየተንደረደረች ተምዘገዘገች። ለሷ ብቻ ሳይሆን ለተመልካቾችም አስፈሪ ነበር። ነባርና እጩ መኮንኖች ሁሉ በድንጋጤ፣ ፊታቸው አመድ መስሏል። መጨረሻዋን ለማየት፣ የማረፊያ ሜዳው ላይ እየሮጡ ሄዱ።
ደግነቱ በህይወት ተረፈች። “እየተንቀጠቀጥኩ ነበር የወረድኩ”ት ትላለች - ትዝታዋን ስትተርክ። ጉብዝናዋ፤ “በቃኝ” አለማለቷ ነው። ለትምህርትና ለሙያ፣ በጣም ፈጣን መሆኗ ደግሞ ጠቀማት። ሴት እንደሆነች ቢታወቅም፣ የአብራሪዎች አሰልጣኝ ሆነች።
ከዓመታት በኋላ ከስራዋ ከተሰናበተች በኋላም፤ የአውሮፕላን በረራ አላቆመችም። የምትጓጓለት መዝናኛዋ ነው። ታዲያ፣ ተራ በረራ አይደለም። እየተገለባበጡ እየተሽከረከሩ ማብረር ያስደስታታል። ለተዋጊ አውሮፕላኖች ነበራ አብራሪዎችን የምታሰለጥነው።
ከመኖሪያ ሰፈራቸው አቅራቢያ፣ ከገላጣው ሜዳ ላይ አውሮፕላኗን እያንደረደረች ትከንፋለች። በሸለቆው መሃል ሰንጥቃ ስትምዘገዝግ፣ በተራራው አናት ሽቅብ ስትመጥቅ፣ በአውሮፕላኗ “አክብሮባት” ስትሰራ እያየ ነው ያደገው - ልጇ ሪቻርድ ብሮንሰን።
“አደገኛ ነገሮችን” በላቀ ብቃት ማሸነፍ ምን ማለት እንደሆነ የተማረው ገና ከሕፃንነቱ ነው። አፍ የሚያስከፍቱ ድንቅ ትዕይንቶችንና ጀብዶችን መፈጸም ምን ማለት እንደሆነ የተማረው ከእናቱ ነው። በአይኑ በብረቱ፤ ከዓመት ዓመት  አይቷል። ያደገበት ነገር ነው። አዲስ ነገር አይደለም።
ነገር ግን፤ ከእናቱ ያየው የብቃትና የጀብድ ትዕይንት ላይ፤ እሱ በተራው፣ እጥፍ ድርብ አድርጎ ጨመረበት። “በባሉን” የአትላንቲክ ውቅያኖስን መሻገር፣ በጀልባ ከአሜሪካ እንግሊዝ ድረስ የዓለም ሪከርድ መስበር… ብዙ አደገኛ ተግባራትን ፈጽሟል። ቅዝቃዜው  ከበረዶ የማይተናነስ አጥንት የሚሰብር ውቅያኖስ ውስጥ ሰጥሞ፣  ገደል ውስጥም ተከስክሶ ሊቀር ነበር። ግን ተርፏል። በታሪክ ላይ፣ ሌላ አዲስ ታሪክ ለመስራት በቅቷል። አሁንም ገና ታሪክ እየሰራ ነው።
ለጠፈር ጉዞ፣ “ቨርጂን ጋላክቲክ” የተሰኘ የግል ኩባንያ መስርቷል። በግል ሮኬትና መንኮራኩር፣ የመጀመሪያው የሽርሽር ተጓዥ ጎብኚ ሆኗል - ባለፈው ወር። ይሄ፣ ከእስከ ዛሬዎቹ የሪቻርድ ብሮንሰን የጀብዱ ትዕይንቶች ሁሉ የላቀ፣ ትልቁና አስቸጋሪው ገድል ነው።
ቨርጂን አየር መንገድ! በ39 ዶላር።
እስከ ቅርብ አመታት ድረስ፣ የሮኬትና የጠፈር መንኮራኩር ስራ፤ ከመንግስታት ውጭ የሚሞከር አልነበረም። ለዚያውም፣ የጥቂት መንግስታት ብቻ። ይህን አጥር የሰበረ አዲስ ታሪክ መፍጠር፣ መስበርም ብቻ ሳይሆን፣ የላቀና የበለጠ ስኬት፣ የቀድሞውን የሚያስከነዳ ድንቅ ትዕይንት በእውን መፈጸም፤  ከባድ ነው። ለህልም ለሀሳብ እንኳ ያስቸግራል። ለነገሩ፣ እንደዋዛ አይደለም የተሳካለት። ለበርካታ ዓመታት ለፍቷል። ያላገጡበትም፣ ጥቂት አይደሉም።
ብሮንሰን፣ ወደኋላ አላለም። አስቸጋሪና አደገኛ ስራዎችን የሚሸሽ አይደለም። ከእናቱ የተማረውና ያደገበት የጀብድ መንፈስ የት ሄዶ? እሱ ራሱም፣ “አይታሰቡም፤ አይሞከሩም” የተባሉ ስራዎችን ሰርቷል። የግል ሮኬት፣… የግል የጠፈር መንኮራኩርና ሽርሽር ግን፣ ከሁሉም የከበደ ነው። እንኳን በጠፈር፣ ምድር ለምድር የግል አየር መንገድ መጀመርስ ከባድ አይደል? ከአርባ ዓመታት በፊትማ በጣም ከባድ ነበር። የአየር ትራንስፖርት፣ በብዙ ሀገራት ለመንግስት ብቻ ነበር የሚፈቀደው።
ብሮንሰን፣ እንደ ድንገት፣ አየር መንገድ ለማቋቋም የወሰነበትን አጋጣሚ ያስታውሳል። ጉዞ ላይ ነበር። የአውሮፕላን ትኬት ቆርጧል። ሰዓቱን ጠብቆ፣ አውሮፕላን ጣቢያ ላይ ተገኝቷል። ወደ ትንሽየዋ ደሴት ለመጓዝ አውሮፕላን ተሳፍሯል። ግን አውሮፕላኑ አልተነሳም። ከብዙ ጥበቃ በኋላ፣ “በቃ ውረዱ፤ በረራው ተሰርዟል” ተባለ። ለምን? አውሮፕላኑ አልሞላም። የተሳፋሪው ቁጥር ጥቂት ነው። ውረዱ።
ደንበኞችን እንዲህ ማንገላታት ተገቢ ነው? ትኬት ተገዝቶ፣ ቀንና ሰዓት ተቆርጦ፣ ለጉዞ ጓዛቸውን ይዘው የመጡ ደንበኞችን ሜዳ ላይ መጣል? ምንም ማድረግ አይቻልም አሉት። በቃ፣ አሰራሩ ነው፤ ተሳፋሪ ካነሰ በረራውን መሰረዝ እንደሚቻል፣ ትኬቱ ላይ ተጽፏል - በደቃቅ ፊደላት ቢሆንም። “እና አሁን ምን ይሻላል?”
አነስ ያለ አውሮፕላን ቢከራይ፣ ወጪው ቀላል አይሆንለትም። ግን፣ ከታሰበበት መፍትሔ አይጠፋም። ብሮንሰን፣ አውሮፕላን ተከራየ። “በረራ አይሰረዝም” የሚል መሀላ በአእምሮው ውስጥ ተፀንጿል። እዚያው ነው ስራውን የጀመረው።
“ቨርጂን አየር መንገድ፣… በ39 ዶላር” የሚል ማስታወቂያ፣ ካርቶን ላይ ፅፎ መንገደኞችን ማግባባት ጀመረ። በረራ የተሰረዘባቸው መንገደኞች አይናቸውን አላሹም። ብሮንሰን የተከራያት አነስተኛ አውሮፕላን፣ በተሳፋሪዎች ሞላች። የብሮንሰን የግል አየር መንገድ የተወለደው፤ በዚህ አጋጣሚ መነሻነት ነው። ከቦይንግ፣ አንድ አውሮፕላን ተከራይቶ፣ ከለንደን ኒውዮርክ፣ የበረራ አገልግሎቱን ሀ ብሎ ጀመረ። ዛሬ፤ ከዓለማችን ትልልቅ አየር መንገዶች አንዱ ነው - የብሮንሰን ቨርጂን።
ሕዋ ጠጠር ነው። ሮኬት እሳት ነው። ይፋጃከል።
ገና በጥዋቱ፣ የሙዚቃ መፅሔት በማሳተም፣ ወደ ቢዝነስ አለም የገባው ብሮንሰን፣ የሙዚቃ አልበም ወደ መቸርቸር ተሸጋገረ። ከዚያም ሙዚቃ ማሳተም ጀመረ።  የቢዝነስ ስራው እየተቃናለት፣ አይነቱም እየበረከተለት፣… የሞባይል ስልክ አገልግሎት፣ ሆቴሎች፣ መዝናኛ መርከቦች፣… አየር መንገድ፣… በሃብት ከበረ - ቢሊዮነር ሆነ። የሕዋ ቢዝነስ ግን፣ እንደሌሎቹ ይሆንለታል? አንድ ቀልድ አለ።
“በሕዋ ቢዝነስ፣… ማለት በሮኬትና በጠፈር መንኮራኩር ቢዝነስ ውስጥ ገብቶ፣ ሚሊዮነር መሆን ይቻላል?‹
“አዎ፤ ሚሊዮነር መሆን ይቻላል፤ ቢሊዮነር ሆኖ ለገባበት።”
ይሄ፤ ለበርካታ ዓመታት ያገለገለ ቀልድ ነው። በርካታ ባለሃብቶች፣ የህዋ ቢዝነስ ውስጥ ገብተው፣ ብዙ ከስረዋል። የሕዋ ቢዝነስ፣ ኪስ ያሳሳል። ሽቅብ የመምጠቅ ሕልም፤ ቢሊዮነርን ወደ ሚሊዮነር ያወርዳል። ሰማዩ ሲታይ፣ ወሰን ድንበር የግንብ አጥር የሌለው፣ ወለል ብሎ የተከፈተ፣ እንደ ልብ የሚከንፉበት ስስ አየር ይመስላል። ግን፣ እንደ አለት የጠጠረና የከበደ ፈተና ነው።
“Space is Hard” ይላሉ - በርካታ የናሳ ሰዎች። ከባድነቱ ታዲያ፣ ለከባድ ሰዎች ነው። የጠለቀ የመጠቀ እውቀት፣ የረቀቀ የሙያ ጥበብና የተራቀቀ የቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ የበርካታ አመታት ትጋትና ፅናት ቢሟላም እንኳ፣ በቀላሉ ይሳካል ማለት አይደለም። የሕዋ ጉዞ፣ ከባድና ረዥም ጉዞ ነው። አእምሮን፣ አካልንና መንፈስን ክፉኛ ይፈታተናል። እና ኪስን።
በዚያ ላይ አደገኛ ነው - የሕዋ ሮኬትና መንኮራኩር።
የሚታቀፈው ነዳጅን ነው፣ የሚተነፍሰው እሳትን ነው። አነፃፅሩት። ከትልልቅ አውሮፕላኖች ክብደት፣ ሩብ ያህሉ፣ የተሳፋሪና የጭነት ክብደት ነው። ሩብ ያህሉ ደግሞ የነዳጅ ክብደት። ቀላል ሸክም አይደለም። ግን፣ ያለ ነዳጅ መንቀሳቀስ አይቻልም።
የህዋ ጉዞ ላይ ግን፣ ከሮኬትና ከመንኮራኩሩ ጠቅላላ ክብደት ውስጥ፣ 90% ያህሉ፣ ነዳጅ ነው። የህዋ ጉዞ፣ “ነዳጅ ይበላል” ቢባል፤ በደንብ አይገልፀውም። ነዳጅ መፍጀት ነው - የሮኬት ሕይወት። በአንድ ደቂቃ ውስጥ መቶ ሺ ሁለት መቶ ሺ ሊትር ነዳጅ የሚያቃጥል ማሽን ምን ይባላል? እሳትና ፍንዳታ ነው እስትንፋሱ። እቶኑ፣ ኃይሉና ጉልበቱ፣… ከዚህ የባሰ አደገኛ ቦታ ከየት ይገኛል?
የህዋ ሮኬት ከመሬት ለመነሳት፣ ብዙ ነዳጅ ከጉያው መታቀፍና መሰነቅ እንዳለበት ሁሉ፤ ብዙ መነሻ ገንዘብ ያስፈልገዋል። ነዳጅ የማቃጠል ፍጥነቱ ያህልም፣ በዚያው መጠን ገንዘብ ለማቃጠል ጊዜ አይሰጥም። ቡን ነው። ብልሽትና አደጋ ሲደርስበት፤ ቁራጭ ስባሪ የሚቀር ቅርስ የለውም። የህዋ ሮኬት፣ ከነመንኮራኩሩና ከነጭነቱ፣… በትንፋሽ ፍጥነት ፈንድቶ፣ ጭስና አመድ ይሆናል። በአንዲት ቅጽበት፣ የመቶ ሚሊዮኖች ዶላር ሃብት፣ ብናኝ እንኳ ሳያስቀር ይጠፋል።
የዛሬ 5 ዓመት፣ የስፔስኤክስ የብዙ ሚሊዮን ዶላር ሮኬት፣ መቶ ሚሊዮን ዶላር ከሚያወጣ ጭነቱ ጋር፣ በቅጽበት ፍንዳታ፣ እንዳልነበረ ሆኗል። ገና ከመሬት ሳይነሳ፣ ገና ነዳጅ እየተሞላ ሳለ ነው የጋየው። ከዚያ በፊትም፣ ተመሳሳይ ሮኬት፣ አየር ላይ ፈንድቶ ተበታትኗል፤ ከነጭነቱ።
የሁለቱ አደጋዎች ኪሳራ፣ ከ400 ሚሊዮን ዶላር ይበልጣል። ኩባንያው፣ በዚያው ያልቅለታል ተብሎ ነበር። ትንበያው ከንቱ ሟርት ነው ለማለት ያስቸግራል። ኪሳራው ቀላል አይደለማ። ግን ደግሞ፣ በኢሎን ሞስኮ የተመሰረተው ስፔስአክስ፣ ለውድቀት ትንበያ አዲስ አይደለም። ለነገሩ፣ አይገርምም። ስንቱ ባለሃብት፣ በህዋ ቢዝነስ ስንቴ ቀልጦ ቀርቷል! “የህዋ ቢዝነሶች ከወረት አያልፉም። ከአንድ ወር የማይሻገሩ ወሬዎች ናቸው። ይሄኛውም አይከርምም፤ ቢከርምም ዓመት አይሻገርም። በህልም እንጂ፣ በእውን ቅንጣት ሮኬት አያመጥቅም። የህዋ ጉዞ፣ በመንግስት ካልሆነ በቀር፣ በግል ቢዝነስ አይሳካም” ተብሏል።
ብዙ ውድቀት ተተንብዮበታል።
ከፊሎቹ፣ የስራውን ከባድነት በማመዛዘን፣ ስጋታቸውን ይናገራሉ።
ሌሎቹ፣ የግል ቢዝነስን ለማናናቅ፣ በክፋት ስሜት ያሟርታሉ።
አስገራሚው ነገር፣ በመንግስት የተጀመረው የህዋ ጉዞ፣ እንደ አጀማመሩ አልዘለቀም።
መንግስታት የተሸነፉበት የሕዋ ጉዞ፤ በነፃ ገበያና በግል ኢንቨስትመንት ነፍስ ዘራ።
ከ1972 ወዲህ፣ ወደ ጨረቃ የሄደ የጠፈርተኛ መንኮራኩር የለም። የጠፈርተኞች ጉዞ፣ በአጭር ተገድቧል። የጠፈር ጉዞ ከአለማቀፍ የጠፈር ማዕከል የማያልፍ ሆኗል።
ልዩነቱ የትና የት! የጠፈር ማዕከል፣ እዚሁ ቅርብ በ400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ነው።
የጨረቃ ርቀት፣ በሺ እጥፍ ይበልጣል - 400,000 ኪሎ ሜትር ገደማ ነው።
የሕዋ ጉዞ፣ ከጨረቃ አልፎ ወደ ማርስ ይቀጥላል እንዳልተባለ፤ ጨረቃም የሩቅ ህልም ሆነች።
ከዚያስ? የጠፈር ማዕከል ጉዞ፣ የዛሬ 10 ዓመት ተቋረጠ። የናሳ መንኮራኩሮች፣ ለአጭር ጉዞም  ተቸገሩ፤ አየር ላይ ሁለቴ በደረሰ አደጋ፣ ሁለት የቢሊዮን ዶላር መንኮራኩሮች ፈንድተው ቀርተዋል። 14 ጠፈርተኞችም ሞተዋል። አደጋቸው በዛ። ወጪያቸውም ከመጠን አለፈ። ገንዘብ ማፍሰስ የማይጨንቀው መንግስት ሳይቀር፤ ወጪው ከበደው። የአሜሪካ የጠፈርተኞች መንኮራኩር በ2011፤ ከበረራ ታሪክ ወጣ።
የአሜሪካው ዝነኛ የጠፈር ተቋም ናሳ፣ ጠፈርተኞቹን ለማብረርና ለመመለስ፣ የሩስያ መንኮራኩሮች ተከራይና ተሳፋሪ ሆነ። ውድ ዋጋ እየከፈለ።
ይሄ፣ ትልቅ ውድቀትና ውርደት አይደለም? ስለ አሜሪካ፣ ስለናሳ የምናወራ ይመስላል? ኧረ አይመስልም። የኋሊት የመንሸራተት ውድቀት፣ ከአሜሪካ ተፈጥሮ ጋር ይሄዳል? “አይሄድም፤ በጭራሽ አይሄድም። ድንዛዜና ውድቅት፣ ለአሜሪካ አይመጥንም።
አሜሪካ፣ ሩቅ ለማለም፣ ወደ ከፍታ ለማነጣጥር፣ በጥረት ለመሻሻልና ለመምጠቅ የተፈጠረች አገር ናት። የመንግስት ቢሮክራሲ በሚደነቅራቸው መሰናክሎች ሳቢያ፣ በአጭር መታጠር የማይገባት አገር ናት። አሜሪካ፣ ለስኬት የታሰበች አገር ናት” ባይ ነው ኤሎን ሞስክ። የትውልድ አገሩ አይደለችም። ነገር ግን  “ሞክሬ አይቻታለሁ” ብሎ ሊመሰክርላት ይችላል። በእርግጥም፣ ለስኬት የታሰበች አገር ናት- ኢሎንሞስክ በኢንተርኔት የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስኬታማ የሆነው አሜሪካ ከገባ በኋላ ነው።
 ግን ደግሞ፣ ለስኬት በታሰበችው አሜሪካ ውስጥ፣ የሕዋ ቴክኖሎጂና ጉዞ በድንዛዜ ተይዟል፤ የኋሊት ተንሸራትቷል። ይህ የውድቀት ጉዞ የሚቀየረውና ወደ ከፍታ ግስጋሴ የሚለወጠው በግል ቢዝነስ ሆኗል።
አሜሪካ፣ ከነአፈጣጠሯ፣ ከባባድ ስራዎችንና ፈተናዎች የመጋፈጥ፣ ወደተሻለ ወደላቀ ከፍታ የማለም፣ የመሞከር፣ ደጋግሞ የመጣር መንፈስ ላይ የቆመች አገር ናት።
በሌላ ሰው ወጪና መስዋዕትነት ሳይሆን፣ በራስ ጥሪት የራስን ሃሳብ ለማሳከት የመትጋት አገር ናት።
በመንግስት ድጎማ ሳይሆን፣ በግል ቢዝነስና በግል ድጋፍ፣ በግል እየተገበያዩ በግል እየተረዳዱ፣ ወደ አዲስ ምዕራፍ የመጓዝ፣ የፈር ቀዳጅነትና የስኬት መንፈስን ያበቀለች፣ በዚህም የለመለመች አገር ናት።
የህዋ ጉዞም፣ በአሜሪካ መንፈስ፣ በፈር ቀዳጅ የስኬት መንፈስ፣ በመንግስት ሳይሆን በግል ቢዝነስ አማካኝነት፣ ከውድቀት መነሳት፣ ወደ አዲስ ከፍታዎችም መገስገስ አለበት እያለ ሰብኳል - ሞስክ።
በተናገረበት ለመዋልም፤ በ2002 የህዋ ድርጅት ከፈተ፤ ሃብቱን አፈሰሰ - ለሮኬት ቴክኖሎጂ። አዎ፤ ጣጣው ብዙ ነው። እያንዳንዱን ሮኬት አፍንጫና ጅራት ከዜሮ መጀመርና ሰርቶ መሞከር ብዙ ጊዜ ይፈጃል። ዛሬ፣ የኢሎን ሞስክ ኩባንያ ስፔስኤክስ፣ የመላው አለም መሪ ሆኗል- በሕዋ ቴክኖሎጂዎችና በሕዋ ጉዞ።

Read 2830 times