Monday, 16 August 2021 00:00

ዘጠነኛው ዙር የበጎ ሰው ሽልማት ነሀሴ 30 ይካሄዳል

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

   በላይነህ ክንዴ በስራ ፈጠራ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ በመምህርነት አለምፀሃይ ወዳጆ በዲያስፖራ ዘርፍ ታጭተዋል

              ዘጠነኛው ዙር የበጎ ሰው ሽልማት ነሀሴ 30 ቀን 2013 ዓ.ም በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል እንደሚካሄድ የበጎሰው ሽልማት ድርጅት አስታወቀ። የድርጅቱ የቦርድ አባላት አቶ ስንታየሁ ደምሴና አቶ ቀለመወርቅ ሚደቅሳ ትላንት ከሰዓት በኋላ በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በዘጠኝ ዘርፍ ወደ መጨረሻው ዙር ያለፉ ከየዘርፉ ሶስት ሶስት ዕጩዎችን ይፋ አድርገዋል። ከዘጠኙ ዘርፎች በተጨማሪ በጥቆማና በውድድር የማይቀርብ አንድ ልዩ ተሸላሚ የሚሸለም ሲሆን ይህ ልዩ ተሸላሚ በሽልማቱ ቀን ብቻ ይፋ እንደሚሆን ታውቋል።
 በዚህ  ሽልማት በኪነ-ጥበብ ዘርፍ የወግና የአጫጭር ታሪኮች ፀሃፊዎች የታጩ ሲሆን ታደሰ ሊበን፣ ጃርሶ ሞት ባይኖር ኪሩቤል በውቀቱ ሥዮም ወደ መጨረሻው ዙር አልፈዋል። በማህራዊ ጥናት ዘርፍ ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ፣ ፕ/ር ጌትነት ታደለና ዶ/ር አሉላ ፓንክረስት ሲያልፉ፣ በመምህርነት ዘርፍ ደግሞ ፕ/ር ጥሩሰው ተፈራ ዶ/ር ልዑልሰገድ አለማየሁና ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ተካትተዋል።
የመንግስታዊ የስራ ሃላፊነትን በአግባቡ በመወጣት አቶ ይኩኖ አምላ መዝገቡ፣ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለና ኢ/ር ሀብታሙ ተገኝ ሲያልፉ በሚዲያ ዘርፍ ጋዜጠኞቹ ደጀኔ ጥላሁን፣ የፋናውና በዓባይ ዙሪያ ተግቶ የሚሰራው ስላባት ማናዬና ዶ/ር ንጉሴ  ተፈራ አልፈዋል።
በቅርስና ባህል ዘርፍ ሲሳይ ደምሴ፣ ዶ/ር መንግስቱ ጎበዜና ቢላሉል ሐበሺ ሙዚየም ወደመጨረሻው ዙር ሲያልፉ፣ በበጎ አድራጎት ዘርፍ ማርያ ሙኒር፣ አማረ አስፋው የእልልታ ውመን አልፈዋል። በንግድና ሥራ ፈጠራ ዘርፍ እውቁ ባለሀብት በላይነህ ክንዴ፣ ወጣት ሎሬት ብሩክታዊት ጥጋቡና ፓን አፍሪካን ሎጂክስቲክስ ወደ መጨረሻው ዘርፍ ማለፋቸው የተገለፀ ሲሆን፣ በዲያስፖራ ዘርፍ የፀሀይ አሳታሚው አቶ ኤልያስ ወንድሙ፣ አርቲስት ዓለም ፀሀይ ወዳጆና ዶ/ር እንዳወቅ ይዘንጋው ተካትተዋል። በሳይንስ ዘርፍ ደግሞ ፕ/ር አለማየሁ ተፈራ ፣ ዶ/ር አየለ ተሾመና ፕ/ር ወይንሃረግ ፈለቀ ለመጨረሻው ዙር ሲሸጋገሩ የልዩ ተሸላሚው ማንነት በሽልማቱ ዕለት ይገለፃል-ተብሏል።
በዘንድሮው የዕጩ ምልመላ 500 ያህል ሰው በእጩነት ተጠቁሞ የነበረ ሲሆን በውድድሩ በ2012 ዓ.ም በኮቪድ 19 ምክንያት ሽልማት ባልተካሄደባቸው ዘርፎች የተጠቆሙትም መካተታቸውን የቦርዱ አባላት ተናግረዋል።


Read 10665 times