Saturday, 14 August 2021 12:19

ሲፋን ልዩ የኦሎምፒክ ሃትሪክ ሰርታለች

Written by  ግሪም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

  ከ35 በላይ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዜግነት
               ቀይረው ለ14 የተለያዩ አገራት እየሮጡ ናቸው


             በ32ኛው ኦሎምፒያድ ላይ በአትሌቲክስ ውድድሮች ሶስት ሜዳልያዎች (2 የወርቅና 1 የነሐስ) ያስመዘገበችው  ሲፋን ሀሰን የዓለም ኮከብ አትሌት ሽልማትን እንደምታገኝ ተጠብቋል፡፡ ቶኪዮ ላይ በ5000 ሜትር ፤ በ10 ሺ ሜትር እንዲሁም  በ1500 ሜትር  ያገኘቻቸው ሜዳልያዎች በኦሎምፒክ የታሪክ መዝገብ ላይ የሚሰፍሩ ናቸው፡፡ በማጣርያ ውድድር ላይ ተጠልፋ ከወደቀች በኋላ ተነስታ ውድድሩን በማሸነፍ ያሳየችው ተጋድሎም በከፍተኛ ደረጃ የዓለም ስፖርት አፍቃሪን ትኩረት አስገኝቶላታል፡፡ የ28 ዓመቷ ሲፋን ሀሰን ኢትዮጵያ ውስጥ ብትወለድም ወደ ሆላንድ የተሰደደችው ከ13 ዓመታት በፊት ነው፡፡ በ2013 እኤአ ላይ የሆላንድ ዜግነቷን በማግኘት በዓለም የአትሌቲክስ ውድድሮች ስትሳተፍ የቆየች ሲሆን በተለይ ባለፉት ሶስት የውድድር ዘመናት በ1500 ሜትር እንዲሁም በረጅም ርቀት 5ሺ እና 10ሺ ሜትር ውድድሮች ከፍተኛ ውጤት አግኝታለች፡፡ ሆላንድ በ32ኛው ኦሎምፒያድ ላይ 278 ኦሎምፒያኖችን በማሳተፍ በሜዳልያ ሰንጠረዡ እስከ 10ኛ ደረጃ ለመጨረስ አቅዳ የነበረ ሲሆን  በ33 ሜዳልያዎች 10 የወርቅ 11 የብርና 12 የነሐስ ሜዳልያዎች ከዓለም ስምንተኛ ደረጃ ላይ ጨርሳለች፡፡  በአትሌቲክስ የሲፋንን 3 ሜዳልያዎች ጨምሮ ሰባት ሜዳልያዎች የሰበሰበች ሲሆን በብስክሌት ፤ውሃ ዋና ፤ ጁዶ፤ ቀስት ውርውራ፤ ቦክስ፤ ሆኪና ሌሎች የተለያዩ የውሃ ላይ የኦሎምፒክ ውድድሮች ሌሎቹ ሜዳልያዎች ተገኝተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሴቶች 10ሺ ሜትር የፍፃሜ ውድድር ላይ 3 ትውልደ ኢትዮጵያዊ አትሌቶች ፉክክር ውስጥ መግባታቸው የዓለም አቀፍ ዜና አውታሮችን ትኩረት ስቧል፡፡ ሲፋን ሃሰን ለሆላንድ የወርቅ ሜዳልያ ስትወስድ በሁለተኛ ደረጃ የብር ሜዳልያ የወሰደችው  ደግሞ ለባህሬን የምትሮጠው ትውልደ ኢትዮጵያዊት ቃልኪዳን ገዛሐኝ ነበረች፡፡
ከ35 በላይ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዜግነታቸውን በመቀየር ለ14 የተለያዩ አገራት እየሮጡ መሆኑን ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ማህበር Transfer of allegiance ብሎ ከሚያወጣው ሪፖርት  ለማወቅ ተችሏል፡፡  ዜግነታቸውን ቀይረው ለሌሎች አገራት የሚሮጡ ትውልደ ኢትዮጵያውያን 7 ለባህሬን፤ 7 ለእስራኤል፤ 5 ለቱርክ፤ 3 ለኳታር፤ 2 ለታላቋ ብሪታኒያ፤ 2 ለዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ፤ 2 ለሆላንድ፤ ለአሜሪካ፤ ለቤልጅየም፤ ለጀርመን፤ ለሆላንድ፤ ለስፔን፤ ለስዊድንና  ለአውስትራሊያ የተመዘገቡ ናቸው፡፡
የትውልድ ዜግነትን በመቀየር ለሌላ አገር የመወዳደር ሁኔታ በአለም ስፖርት አስተዳደር ይሁንታ ማግኘቱ የኦሎምፒክን መርህ እየተፈታተነው መጥቷል፡፡  የኦሎምፒክ መድረክ ኦሎምፒያኖች ለሚወክሏቸው አገሮች ብሔራዊ ኩራትን የሚያመጡበት ቢሆንም ለአንዳንዶች የመወዳደር ዕድል ብቻ ሆኖ መታየት ጀምሯል። ኦሎምፒያኖች ዜግነት እንዲቀይሩ ወይም እንደ ግለሰብ እንዲወዳደሩ የሚያስችሉ ሕጎች መኖራቸው ስደቱን አባብሶታል፡፡ እንደየትውልዳቸው የአገሮቻቸውን ባንዲራ ወክለው ሳይሆን  እድል በሰጣቸው አገር ስር በዓለም ዙሪያ ካሉ ኦሎምፒያኖች ጋር እንዲወዳደሩ ህጉ ያበረታታል፡፡ አትሌቶች ወደ ሌላ አገር ዜግነት ከመቀየራቸው በፊት ቢያንስ ለሦስት ዓመታት ያለ ውድድር ይቆያሉ፡፡ የትኛውን አገር መወከል እንደሚፈልጉ ሙሉ የምርጫ እድል ይሰጣቸዋል፡፡ በተለይ ደግሞ በዜግነት ቅየራው ውስጥ የገቡት ሁለቱም አገራት መስማማታቸው ፍልሰቱን ያፈጥነዋል፡፡



Read 1242 times