Saturday, 14 August 2021 11:17

ክትባትም ሆነ መድሃኒት የሌለው አደገኛ ቫይረስ ከፍተኛ ስጋትን ፈጥሯል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  ከሰሞኑ በጊኒ የተገኘውና አንድ ሰው ለሞት የዳረገው ማርበርግ የተሰኘ ኢቦላ መሰል አደገኛ ቫይረስ በስፋት በመሰራጨትና በወረርሽኝ መልክ በመከሰት ብዙዎችን ሊገድል ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት መፍጠሩንና የአለም የጤና ድርጅት ቫይረሱን በቁጥጥር ስር ለማዋል የተጀመረውን ጥረት ለመደገፍ ወደ አገሪቱ መጓዛቸውን አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
እስካሁን ድረስ ምንም አይነት ክትባትም ሆነ ፈዋሽ መድሃኒት እንደሌለውና ከኢቦላ ቫይረስ ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው የተነገረለት ማርበርግ ቫይረስ፣ ከሁለት ሳምንታት በፊት በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ተከስቶ ለሞት ከዳረገው ሰው ጋር ንክኪ አላቸው የተባሉ አራት ሰዎች በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲገቡ መደረጉን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የመግደል አቅሙ እስከ 88 በመቶ ይደርሳል የተባለው ይህ አደገኛ ቫይረስ ከፍተኛ ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ ድካምና በአይንና በጆሮ በኩል የሚፈስስ ደምን ጨምሮ የተለያዩ ምልክቶች እንዳሉት የተነገረ ሲሆን፣ በንክኪ የሚተላለፈው ቫይረሱ ከዚህ በፊትም በአንጎላ፣ ኮንጎ፣ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካና ኡጋንዳ ቢከሰትም በምዕራብ አፍሪካ አገራት ሲከሰት ግን ይህ የመጀመሪያው መሆኑንም አስታውሷል፡፡
በሌላ የጤና ዜና ደግሞ፣  እስካለፈው ረቡዕ ድረስ በመላው አፍሪካ የኮሮና ክትባት የወሰዱ ሰዎች ከ51 ሚሊዮን ማለፉንና በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥርም ከ7 ሚሊዮን በላይ መድረሱን የዘገበው ኦልአፍሪካን ኒውስ፣ የሟቾች ቁጥር ወደ 179 ሺህ ሲጠጋ ያገገሙት ቁጥር ደግሞ 6.2 ሚሊዮን መድረሱን አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ በጊኒ የኮሮና ክትባት መውሰዳቸውን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት ያልያዙ ዜጎች ወደ ስራ ገበታቸው እንዳይገቡ በአገሪቱ መንግስት መከልከላቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በመላ አገሪቱ የሚገኙ ሁሉም የመንግስት ሰራተኞች የኮሮና ክትባት መውሰዳቸውን የሚያረጋገጥ ህጋዊ ማስረጃ ማቅረብ እስካልቻሉ ድረስ ወደስራ ቦታቸው መግባት እንደማይችሉ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አልፋ ኮንዴ ከሰሞኑ ባወጡት መግለጫ ማሳወቃቸውን ነው ዘገባው ያመለከተው፡፡

Read 3548 times