Saturday, 14 August 2021 11:07

ኢትዮጵያ በ3ኛው ዙር የኮቪድ ማዕበል ውስጥ አየገባች ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

    - ዴልታ የተባለው እጅግ አደገኛው የኮቪድ-19 ዝርያ ወደ አገራችን ሳይገባ አይቀርም ተብሎ ተሰግቷል
     - በአዲስ አበባ ዕድሜያቸው ከ35 ዓመት በላይ ለሆኑ ሰዎች ትላንት አርብ ክትባት መስጠት ተጀምሯል፡፡
                                  
              ኢትዮጵያ በ3ኛው ዙር የኮቪድ-19 ማዕበል ውስጥ እየገባች ነው ተባለ፡፡ የጤና ሚኒስቴር ከትናንት በስቲያ ሃሙስ በሰጠው መግለጫ፤ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ካለፉት 3 ሳምንታት ወዲህ በከፍተኛ መጠን አሳሳቢ በሆነ ፍጥነነት እየጨመረ ነው፡፡
እንደ ጤና ሚኒስቴር መግለጫ፤ በበሽታው የሚያዙ፣ በፅኑ የሚታመሙና ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ነው፡፡ ሳምንታዊ በሽታው የሚገኝባቸው  አማካይ ቁጥር ከ831 ወደ 3302 ወይም በአራት እጥፍ አድጓል፤ በበሽታው ተይዘው ወደ ህክምና ማዕከላት የሚገቡ ህሙማን ቁጥር የ2.5 እጥፍ ጭማሪ በማሳየት ከ353 በላይ ፅኑ ታማሚዎች በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ገብተዋል፡፡ ሳምንታዊ አማካይ የሞት ምጣኔም፣ ከ13 ወደ 36 ከፍ ማለቱን የጤና ሚኒስቴር መግለጫ ያመለከተው፡፡
በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በዚህ ፍጥነት እየጨመረ የሚሄድ ከሆነ፣ ወደ ፅኑ  ህሙማን ክፍል የሚገቡ ሰዎች ቁጥርም በከፍተኛ መጠን  እንደሚጨምርና ከፍተኛ የሆነ የአልጋና ሰው ሰራሽ መተንፈሻ መሳሪያ እጥረት ሊገጥም እንደሚችል የጤና ሚኒስቴር መግለጫ ጠቁሟል፡፡ በሌሎች አገራት በ3ኛው የኮቪድ ማዕበል ምክንያት የደረሰው ከፍተኛ ጉዳት በአገራችን እንዳይደርስ ህብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባም መግለጫው አሳስቧል፡፡
በበርካታ የዓለም አገራት ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለውና ዴልታ የተባለው የቫይረሱ ዝርያ ወደ አገራችን ተገብቷል የሚል ስጋት መኖሩንም የጠቆሙት ምንጮቻችን፤ ክትባት የወሰዱ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው ፅኑ ህሙማን ክፍል እንደገቡና ይህም በክትባቱ ብቻ ተማምኖ ጥንቃቄ  አለማድረግ ለከፍተኛ ችግር የሚያጋልጥ መሆኑን አመላካች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ህብረተሰቡ ከበሽታው ሊከላከል የሚችልባቸውን የጥንቃቄ እርምጃዎች አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም እነዚሁ ምንጮች አሳስበዋል፡፡ የአሜሪካ መንግስት በኮቪድ ፋሲሊቲ በኩል ለኢትዮጵያ የለገሰውን የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባት 1.65 ሚሊዮን  ዶዝ መረከቡን የገለፀው የጤና ሚኒስቴር፤  ይህንኑ በአንድ ዙር ብቻ የሚሰጠውን ክትባት በአዲስ አበባ  ዕድሜያቸው ከ35 ዓመት በላይ ለሆኑ እንዲሁም ለክልል ከተሞች እድሜያቸው ከ55 ዓመት በላይ  ለሆኑና ከዚህ ቀደም ምንም አይነት ክትባት ላልወሰዱ ሰዎች ከትናንት ጀምሮ መስጠት መጀመሩን አስታውቋል፡፡ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ ሆኖ ተጓዳኝ የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች በአዲስ አበባም ሆነ በሁሉም ክልሎች የክትባት አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ  የጤና ሚኒስቴር መግለጫ አመልክቷል፡፡ እስከ አሁን ድረስ 2 ሚሊዮን 254 ሺ 270 ሰዎች የመጀመሪያውን ዙር የኮቪድ-19  ክትባት የወሰዱ ሲሆን ከ300 ሺ በላይ የሚሆትኑ ደግሞ ሁለተኛውን ዙር ክትባትም መውሰዳቸውን መግለጫው አመልክቷል፡፡


Read 13201 times