Saturday, 14 August 2021 11:01

ዜጎች ያለ ፖለቲካ ልዩነት የህልውና ትግሉን እንዲቀላቀሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥሪ አቀረቡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

   ዜጎች በአንድነት መንፈስ በአሸባሪነት በተፈረጀው ህወኃት ላይ እንዲዘምቱና ቡድኑን ለመደምሰስ የሚደረግን ጥረት ያለ ፖለቲካ ልዩነት እንዲተባበሩ  የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪ አቀረቡ።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ንቅናቄ፣ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ እና የመላ ኢትዮጵያውያ አንድነት ድርጅት እንዲሁም 17 የደቡብ ክልል ፓርቲዎች ሰሞኑን ባወጧቸው መግለጫዎች፤ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላት ለመደምስስ በሚደረገው ጥረት ሁሉ ዜጎች ያለ ፖለቲካ ልዩነት እንዲተባበሩ ተጠይቀዋል።
“ትህነግ የአክራሪ ብሔርተኝነት የመጨረሻው ማሳያ ነው” ያለው ባልደራስ፤ ይህ ሃይል አሁንም በህልውና የሚቀጥል ከሆነ የሃገሪቱን ሰላምና አንድነት ይፈታተናል ብሏል።
ትህነግ ካለፈ ጊዜ ጥፋቱ ሊማር የማይችል ድርጅት መሆኑን ያስገነዘበው ባልደራስ፤ አለማቀፉ ማህበረሰብ በሰብአዊነት ሽፋን የሞተውን ድርጅት ከመቃብር ለማስነሳት የሚያደርጉት ጥረት በኢትዮጵያውያን ዘንድ  ተቀባይነት የለውም ብሏል።
“የኢትዮጵያን መንግስት አፈራርሳለሁ፤ በአማራ ላይ ሂሳብ አወራርዳለሁ” በሚል አደገኛ እብሪት ትህነግ እየተንቀሳቀሰ ነው  ያሉት  ደግሞ አብን፣ አዴሃን እና ብልፅግና ፓርቲዎች በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫቸው ነው።
ትህነግ ዋና አላማው ኢትዮጵያን ማፈራረስ መሆኑን ያሰመሩት ፓርቲዎቹ፤ እስካሁን በጦርነቱ የፈጸማቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶችንም የአለም ህብረተሰብ ሊገነዘብ ይገባል ብለዋል።
ይህን ሃይል ለማጥፋት በሚደረገው ትግል ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ተሳታፊ እንዲሆኑና በሃገሪቱ አንድነት ላይ የተጋፈጠውን አደጋ እንዲመክቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ጥሪ አቅርበዋል።
በተመሳሳይ የመላው ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በበኩሉ፤ የተጀመረው ትግል የትህነግን መቃብር አረጋግጦ የሚጠናቀቅ ይሆናል፤ ለዚህም መኢአድ እና አባላቱ በሙሉ አቅማቸው ከመንግስት ጎን ተሰልፈው እንደሚታገሉ አስታውቋል።
ትህነግ ካልጠፋ ሃገራዊ አንድነትና ሰላምን ማረጋገጥ እንደማይችል ያስገነዘበው መኢአድ፤ ትህነግ ከእነ አስተሳሰቡ መቀበር አለበት” ሲል መላው ህዝብ በህልውና ዘመቻው በየፊናው እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርቧል።
በደቡብ ክልል የሚንቀሳቀሱ 17 የፖለቲካ ድርጅቶች በወቅታዊ የሃገሪቱ ሁኔታ ላይ በጋራ ባወጡት የአቋም መግለጫ፤ በአሸባሪነት የተፈረጀው ህውኃት የደቀነውን ሀገር የመበታተን አደጋ ለመቀልበስ በሚደረገው ትግል በሙሉ አቅማችን እንሳተፋለን፤ ከመንግስትም ጎን ቆመን የሃገራችንን ህልውና እናረጋግጣለን ብለዋል።
የሃገርን ህልውና ለማስጠበቅ ከመንግስት የሚሰጠንን ተልዕኮ ለመቀበልና የተቃጣውን የሃገር ብተና ጥቃት ለመከላከል በተጠንቀቅ እንቆማለን ያሉት ፓርቲዎቹ፤ የአሸባሪውን ቡድን የቀጥታም ሆነ የተዘዋዋሪ የእጅ አዙር ጥቃት ለመመከት ዝግጁ ነን ብለዋል።
መላው የደቡብ ክልል ህዝብም ፀረ ሃገር የሆነው ህወኃት ሴራ የደቀነውን የህልውና አደጋ በመገንዘብ ትግሉን በድል አድራጊነት ለመወጣት የሚደረገውን ጥረት ያለማመንታት እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።

Read 14688 times