Monday, 09 August 2021 20:20

የትኛው ጎናችንን እየቀለብን ይሆን?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

ሁለት ናቸው - በዱሩ በጫካው የገነኑ ብርቱ ባላንጦች።
ባላንጦቹ ሁልጊዜ ጦርነት ላይ ናቸው። አንዱ ጥቁር ነው። ጨለማን ያመለክታል - የተስፋ ቢስነት ምሳሌ።
አንዱ ነጭ ነው። ብርሃንን ያመለክታል - የተስፋ ምሳሌ።
ጥያቄው፤ “የትኛው ያሸንፋል?” የሚል ነው። የትኛው ያሸንፋል? ጨለማ ወይስ ብርሃን?
“እንዴት ማወቅ ይቻላል? ማወቅ አይቻልም” እንበል - ለጨዋታ ያህል።
ነገር ግን፣ መልስ አለው። መልሱም እናንተው ዘንድ ነው። እና ምን ትላላችሁ? የትኛው ያሸንፋ? የትኛው ይነግሳል?.... ትክክል። ትክክል።
“አብዝታችሁ የቀለባችሁት፣ እሱ ያሸንፋል”።
ምርጥ እንቆቅልሽ፣ “የሃሳብ ባለፀጋ” እንቆቅልሽ እንደዚህ ነው።
እንዲሁ፣ እንቆቅልሽ በጥሬው፣ እንደ ጨዋታ ደስ ይላል። የአእምሮ አክሮባት ልንለው እንችላለን። ለፍቺ የሚከብድ፣ ጨርሶ መልስ የማይገኝለት ከባድ ፈተና ይመስላል። መልሱን ካገኘን በኋላ ግን፣ ለካ በጣም ቀላል ነው። ለካ መፍትሄ አለው እንላለን።
ያልጠበቅነው አይነት መልስ ቢሆንም፣ እጥር ምጥን ያለ አሳማኝ መልስ ከመሆኑ የተነሳ፣ “ድሮስ ሌላ ምን ሊሆን ኖሯል?” የሚያስብል ይሆናል።
የተዘጋና ያለቀለት፣ መውጫና መግቢያ የሌለው የሚመስል መንገድ ላይ፣... ድንገት ዞር ሲሉ፣ ባላዩት ቅያስ፣ እጥፍ ብሎ፣... ጥያቄውና መልሱ፣ ጥሬውና ብስሉ፣ ሁሉም ነገር ግጥምጥም ብሎ መልክ ሲይዝ፣... መደነቅን ይፈጥራል። “እንዴት አላሰብኩትም?” የሚል ስሜትንም ይጭራል። በሚያስቀይስ እጥፋት፣ ድንገት ድንቅር ብሎ ማስደነቅ፣... የምርጥ እንቆቅልሽ ተፈጥሮ ነው።
“እናትና ልጅ፣ እንዲሁም እናትና ልጅ፣ ሻይ ለመጠጣት ያመጡት ብርጭቆ 3 ብቻ ነው። ለምን?”
“ይሄማ፣ እንዴት ሊሆን ይችላል? 4 ሰዎች እና 3 ብርጭቆዎች? ይሄ፣ የተቃራኒ መልክቶች ግጭት ነው።  ምክንያቱስ ምን ሊሆን ይችላል?” እያልን፣ ጥያቄውን ትንሽ ብናካብደው፣ አይጎዳንም። እንዲያውም፣ “ማካበድ”፣ የእንቆቅልሽ ጨዋታውን ለማድመቅ ይረዳን ይሆናል።
ዋናው ቁም ነገር፣ እንቆቅልሹ፣ በተቃራኒ መልእክቶች የተቆላለፈ፣ መልስ የሌለው ወይም በጭራሽ መልስ ሊኖረው የማይችል ጥያቄ መምሰሉ ነው። ከዚያስ?
“ልጅ፣ እናት እና አያት” ማለት ነው፣ “እናትና ልጅ፣ እንዲሁም እናትና ልጅ” ማለት…
እንዲህ ብለው መልሱን የገለጡልን ጊዜ፣”ተዓምር ነው” ባንልም እንኳ፣… ኦህ… ኦህ… እንላለን። ምንም ባይጥመንም እንኳ፣… “እህ… እሺ ይሁንልህ” ማለታችን አይቀርም።
ያው፣ ይሄም የእንቆቅልሽ ባህርይ ነው። ጥያቄው፣ እርስ በርሱ የሚጣረስ በጣም ከባድ ጥያቄ መምሰል አለበት እንጂ፣ መልሱ ውስብስብ መሆን የለበትም። ትንታኔ፣ ማብራሪያ፣ መከራከሪያ፣ ማረጋገጫ የሚያስፈልገው ከሆነ፣ የእንቆቅልሽ ውበቱ ይቀንሳል። የፈተና (Challange) ገጽታው ከገነነ፣ እንደ ርችት ቦግ ብሎ ካልፈካ፣ ሙግት ይሆናል።
እንቆቅልሽ ግን ፈተናነቱ እስከ ምላሹ ድረስ ብቻ ነው።
ከባድ የመሰለውን ጥያቄ፣ ዞር ዞር፣ አጠፍ ዘርጋ ሲያደርጉት፣ ባልተጠበቀ አቅጣጫ፣ መልሱ ሲገለጥ፣ ድንገት ድንቅር ብሎ ሲያስደንቅ ነው - እንቆቅልሽ የሚያምረው። እዚያው ያልቃል ነገሩ።
እርስ በርስ የሚቃረንና መፍትሄ አልባ የመሰለው ጉዳይ፣ ፍቺ ሲያገኝ፣ ተቃራኒዎቹን ነገሮች የሚያስማማና በጋራ አዋህዶ የያዘ ምላሽ ሲመጣ፣ እንቆቅልሹ እልባት ላይ ይደርሳል። ተቃራኒ የሚመስሉ ሁለት ሶስት ነገሮችን አጣምሮ የማሰብ ዘዴ ላይ ያተኮረ ነው፣ የእንቆቅልሽ ቁምነገር።
አንዳንድ እንቆቅልሾች ግን፣ ከዚህም ይሻገራሉ።
“ከማሰቢያ ዘዴ” ጋር፣ “በሚታሰብ ፍሬ ነገር” የበለፀጉ እንቆቅልሾች አሉ። ከላይ ያነበብነው የሁለቱ ባላንጦች እንቆቅልሽ፣ እጅግ ምርጥ የሚባል ነው።  “በፍሬ ሃሳብ” የበለፀገ ምርጥ እንቆቅልሽ፣ ወደ ሁሉም አቅጣጫ የሚያበራ፣ ለማንኛውም ጉዳይና ለሁሉም ቦታ የሚያገለግል መብራት ነው ማለት ይቻላል። ባለብዙ ቅርንጫፍ ባለብዙ ፍሬ ነው- ፍሬ ሃሳቡ። ለሆነ ሰው ወይም ለሆነ ጉዳይ ብቻ አይደለም። ለሆነ አገር ወይም ለሆነ ዘመን ብቻ የሚሰራ አይደለም- በረከተ ብዙ ፍሬ ሃሳብ።
የባላንጦቹ እንቆቅልሽ፣ ለእያንዳንዱ ግለሰብ ይሰራል - በእያንዳንዱ ግለሰብ ውስጥ የብራሃንና የጨለማ፣ የማጥመምና የማቃናት ባላንጣ መንገዶች ይኖራሉ። እያንዳንዱ ሰው ውስጥ፣ ሁሌም፣ ተቃራኒ አማራጮች ይኖራሉ - ወደ ክብር ከፍታ ወይም ወደ ውርደት ዝቅታ የሚወስዱ።
እንቆቅልሹ፣ ለግለሰብ በተናጠል ብቻ ሳይሆን፣ የሰዎችን ግንኙነት ለማጤንም፣ ይጠቅማል።
የቡድኖች፣ የተቋማት፣ የአገራት ሁኔታን ለማገናዘብና ለመረዳትስ? መቼም፣ ቡድን ስንል፣ አንድ አይነት ሰዎች የተከማቹበት ስብስብ አይደለም። ሆኖ አያውቅም። ሊሆንም አይችልም።
የበርካታ አይነት ሰዎች  ስብስብ ነው -  ማንኛውም ቡድን፣ ተቋም ወይም አገር።
ደረጃውና መጠኑ ይለያያል እንጂ፣ ብርሃናማ የማቃናት ዝንባሌና ጨለማ የማጣመም ዝንባሌ… በሁሉም ቡድን በሁሉም አገር ውስጥ ይኖራል። ለዚያም ነው፤ ቅጣቶችና ሽልማቶች ጎን ለጎን መኖር የሚገባቸው። አይነቱና ክብደቱ ቢለያይም፣ በአንድ ወገን፣ ንግድና ፍቅር፣ በሌላ ወገን ደግሞ ፍርድ ቤትና ወህኒ ቤት፣ በሁሉም አገር ውስጥ ሁሌም ይኖራሉ።
ብርናማውንና የተቃናውን ዝንባሌ ለማለምለም ነው - ግብይትና ፍቅር።
ጨለማውንና የተጣመመውን መባታት ነው- ዳኝነትና እስር ቤት። ይኼኔ ነው ብርሃናማው መንገድ አሸነፈ የሚባለው።
ጨለማውን መንገድ መቀለብ ማለትስ ምን ማለት ይሆን?
የፍቅርና የቢዝነስ፣ የፍትህና የዳኝነት መንገድ አንዱ አማራጭ መንገድ ነው- የሰላምና የመከባበር ብርሃናማ መንገድ።
በደፈናውና በጭፍን፤ በዘርና በሃይማኖት ስንቧደን ምን ማለት እንደሆነ ደግሞ አስቡት። የእገሌ ብሔር የእከሊት ብሔር እያልን ስንቀሰቅስ፣ ስናወራና ስንቧደን፣ ማንን እንቀልባለን? የወዲህኛው የእገሌ ብሔር ከሆነ፣ ጨለማና ጠማማ ዝንባሌንም ጭምር እየቀለብን እናደልባለን። የወዲያኛው የእከሌ ብሔር ከሆነ ግን፣ ብርሃናማና የተቃኑ ዝንባሌዎችም ጭምር እንዲመነምኑና እንዲጠወልጉ በጥላቻ እንጠምዳቸዋለን።
ውጤቱስ ምን ይሆናል! ምን ይጠይቃል? ከጊዜ ወደ ጊዜ በጨለማውና በጠማማው ጉራንጉር ውስጥ የጥፋት አውሬ እየገነነ ሲያሸንፍ እናያለን። ለክፉም ለደጉም፣ ለጥፋትም ለልማትም፣ አብዝተን የቀለብነው አስተሳሰብና ዝንባሌ፣ ዞሮ ዞሮ ማሸነፉ አይቀርምና። የእንቆቅልሽ ፍሬ ነገር፣ ምን ያህል ሃሳበ ብዙ እንደሆነ፣ ከዚህ ምሳሌ ማየት ይቻላል።  የአገር ሰላምና የፖለቲካ አዝማሚያን ለማጤንም ይረዳል ማለት ነው።
በግለሰብ አእምሮ ውስጥ፣ እውነትን የመናገር ጥንካሬና የመዋሸት ድክመት ሲኖሩ ተስማሚ ደባሎች አይሆኑም። ሁለት ባላንጦች ናቸው። ተቃራኒ አማራጮች ናቸው። የሙያ ፍቅር የስራ ታታሪነትና ብኩን እንዝህላነት፣ ሐቅና ሸፍጥ፣ ቅንነትና ክፋት፣... እያንዳንዱን ዝንባሌ በየግላቸው በደጋገሙት ቁጥር አመልና ባህሪ እየሆነ፣ አብዝተው በቀለቡት መጠን እየገነነ ይወጣል - እያሸነፈ።
የሁለት ሰዎች ወይም የቡድኖች ግንኙነትም እንደዚያው ነው። አንዱ ሰው የራሱን ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ሰው ህልውና እያከበረ፣ ፍሬያማ ስራውን እያመሰገነ፣ የመልካምነት ዝንባሌን እያደነቀ፤ ስህተትና ጥፋትን ደግሞ እየተከላከለ፤ ሁለቱ ሰዎች በጋራ ወደ ሰመረ ግንኙነት መጓዝ ይችላሉ እየተመጋገቡ።
አለበለዚያም፣ አንዱ ሰው ባንጋደደው መንገድ፣ ሌላኛው ባፈናው አፀፋ ለመመለስ - እጥፍ ያጣምማል። የመጠፋፋት አዙሪት እንዲህ ነው። ጠማማነትን እየቀለቡ መጠፋፋት ጀመሩ ማለት ነው። በእርግጥ፣ “ይሄ ነገር አያዋጣም” ብለው ራሳቸውን የማስተካከል እድል ይኖራቸዋል። ግን ማባባስም አያቅታቸውም።
በብሽሽቅ የአጻፋ አጸፋ እየተገበያዩ፣ መጥመምን እየተመጋገቡ፣ አንዱ ሌላኛውን እየገነደሰ፣ ሌላኛው በአፀፋው ተቀናቃኙን እየሸረሸረ፣ የመፍረስ አዙሪቱን ማጦዝ ይችላሉ።
መንገዱ መጣመሙ ሳያንስ፣ አንዱ ተነስቶ በእልህ ያጨልመዋል። ባላንጣው በድርብ እልህ ድልድዩን አፍርሶ የእንጦርጦስ ገደል ያዘጋጃል። ታዲያ እየተጓተቱ እየተንሸራተቱ ተያይዘው ወደ ድቅድቁ ጨለማ ቢወርዱ ይገርማል? አንዱ የሌላውን ክፋት እየመገበ፣ የጨለማው የጠማማው መንገድ አውሬን እየቀለበ፣ ሌላ ማን ሊያሸንፍ ይችላል - የፅልመት አውሬ እንጂ።
ነገር ግን፣ አንዱ የሌላኛው ፈካ ያለ ጎን ላይ እያተኮረ፣ በትንሽ በትንሹም እየተቃኑ የማንሰራራት አማራጭ አላቸው- ብርሃናማውን መንገድ የመቀለብ አማራጭ።
 ሰላምን መፍጠር የፈለጉ 2 ሰዎች ወይም 2 ቡድኖች፣ ራሳቸውን እንደ ጥንድ እንደ ጥንድ መቁጠር አለባቸው ይላሉ- የታዋቂው ምሁር የሳሙኤል ሃቲንተን አድናቂዎች።
በአበበ ውስጥ ብሩህና ጨለማ ጎራዎች አሉ። በከበደ በኩልም ብሩህና ጨለማ ዝንባሌዎች አሉ። የመናቆር የመጥመም አዙሪት ውስጥ፣ የአበበ ጨለማና የከበደ ጨለማ እርስ በርስ እየተመጋገቡ እየገነኑ ያሸንፋሉ።
እዚህኛው አዙሪት ውስጥ ጥቁሩን አውሬ ነው የቀለብነው።
በሌላ በኩል፣ የአበበ ብሩህ ጎኖችና የከበደ ፈካ ያሉ ገፅታዎች ከበረከቱና አቅም ካገኙ፣ እርስ በርስ ይመጋገባሉ - እየደመቁ ወደተቃና መንገድ የመሄድ እድልን ይፍጥራሉ። ብርሃናማውን መንገድ ቀልበናል ማለት ነው።
There are two wolves. And they are always fighting.
One is darkness and despair.
The other is light and hope.
Which wolf wins?
whichever one you feed.
(Tomorrowland የተሰኘው ምርጥ ፊልም፣ ይህን አባባል አግዝፎና አድምቆ፣ ድንቅ ገፀ ባህርያትን ቀርፆ፣ በመሳጭና በአዝናኝ ታሪክ ታዳሚን የሚያስደምም ትልቅ የኪነጥበብ ስራ ነው። ለነገሩ፣ Brad Bird የሰራቸው ፊልሞች፤ ምን ይወጣላቸዋል?)


Read 3178 times