Wednesday, 11 August 2021 00:00

ከካህሊል ጅብራን ጋር እጅ ለእጅ ሽርሽር…

Written by  ብርሃኑ ያ
Rate this item
(4 votes)

ያለፈውን ዘመን እንድናፍቅ (nostalgic) ከሚያደርጉኝ አንዱ የደብዳቤ ልውውጦች ናቸው፡፡ እኛ ያለንበት ዘመን በአንድ ዐረፍተ ነገር እንዲህ ይገለጻል፡፡ ‹በአንድ እግራችን የባሪያ አሳዳሪ ስርዓተ ማህበር ላይ፣ በሌላኛው እግራችን የሥልጣኔው አስፈሪ ጫፍ (age of singularity) ላይ አድርገን አጓጉል አንፈራጠን ቆመናል፡፡› ከየትኛው መሆን እንዳለብን ግራ ተጋብተን እንድሞነሞናለን፡፡ ዘመኑ ቀድሞን ዘምኗል። የደብዳቤ ዘመን አክትሞ በምትኩ ከጥቅሻ የፈጠኑ እንደ ቴሌግራም፣ ፌስቡክ፣ ቫይበር፣ ትዊተር ዓይነት የምትሃት ሣጥኖች እንጠቀማለን፡፡ ግን የምናራምደው ዘመኑን ያልዋጀ ከፋፋይ አጀንዳ፣  ነውራችንን፣ ሀሜታችንን ብቻ ነው፡፡
ደብዳቤዎች ግን  የታሪክ፣ የሁነት፣ የማህበረሰብ ስሪት ቅጥን ለማጥናት እጅጉን ጠቃሚ ቅንጣት የተሸከሙ ሰነዶች ነበሩ፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ያለውን የኢየሱስን ዘመንና ሕይወት ለማጥናት ተመራማሪዎች በዘመኑ የተጻፉ ድንበር ተሻጋሪ ደብዳቤዎች ላይ አተኩረዋል፡፡ በተለይም ሮማውያኑ ገዥዎችና ወታደሮች የፃፏቸው ደብዳቤዎች ከተገኙ ጠቀሜታቸው የላቀ ነው፡፡ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ በተለይም የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትም በደብዳቤ መልክ የተጻፉ ናቸው፡፡
ቀረብ ባለው ዘመን የኖሩትን የታላላቆቹን ጠቢባን ሕይወት ለመመርመር ዋነኛ መሰላል የሆኑት እንዲሁ ደብዳቤዎች ነበሩ። የ19ኛው ክፍለ ዘመን አስደናቂውን ሰዓሊ ቪንሰንት ቫን ጎን ነፍስ በጥልቀት መመርምር የተቻለው ለወንድሙ ቲዎ የጻፋቸው ደብዳቤዎች ስለተገኙ ነው፡፡ ቪትሆቨን እና ናፖሊዮን ለፍቅረኞቻቸው፣ ካፍካ ለአባቱ፣ ለፍቅረኛው፣ ለጓደኛው፣ ቫን ጎ ለወንድሙ ቲዎ፣ ኒቼ ለወዳጆቹ… የጻፏቸው ደብዳቤዎች በብዙ መልኩ ከደብዳቤ በላይ የሚጠኑ ዘመን አይሽሬ የስነጽሑፍ ሥራዎች ሆነዋል፡፡
ቀጥሎ የማስነብባችሁን ደብዳቤዎች የወሰድኩት በቅርቡ መተርጎም ከጀመርኩት ካህሊል ጅብራንና ሜሪ ሐስከል የተለዋወጧቸው ደብዳቤዎችን ከያዘው ‹‹Beloved prophet›› የተሰኘ ጥንቅር ላይ ነው፡፡ ደብዳቤዎቹን ስመርጥ የተለየ ምክንያት የለኝም፡፡ ምናልባት አጠር አጠር ብለው የበለጠ ግላዊ ላልሆኑት አድልቼ ከሆነ አላውቅም፡፡ የካህሊል ጅብራን እያንዳንዷ ገለጻ ለብቻዋ ሕልውና ያላት ዘመናት የማይፈትኗት አስደናቂ ክፍልፋይ እሙን ነች፡፡ ካህሊል ጅብራንን መተርጎም ሌላ፣ የላቀ ፈታኝ ልምምድ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ በዚህም ሂደት የካህሊል የቋንቋ ዕምቅነትና ረቂቅ ውበት ልዕልናን ለመጠጋት ተፍጨርጭሬያለሁ፡፡
ካህሊል ለሕይወት ዘመን አጋሩ፣ ወዳጁ የነፍስ ጓደኛው ሜሪ በጻፈው አንድ ደብዳቤ ላይ ‹‹I talk to you, as I talk with my own heart. You and my destiny are inseparable… and what is there to hide from one’s own destiny?›› ይላል። እናም እነዚህ ደብዳቤዎችን ማንበብ የካህሊል ጅብራን ነፍስ እርቃኗን መስታወት ፊት ቆማ ከመመልከት በላይ ነው፡፡ በዚህ የደብዳቤዎች ስብስብ መጨረሻ ላይ ‹‹ከዕለታት የሆነ ቀን የተጻፈ›› በሚል ርዕስ ሥር ያቀረብኳት ከወራት በፊት የተጻፈች የእኔ ደብዳቤ ናት፡፡ ምናልባት እኔስ ለምን ይቅርብኝ ብዬ ይሆን? በመጨረሻ፣ ኦሾ ‹‹The prophet›› የተሰኘ የጅብራን መጽሐፍ ላይ በሰራው አንድ ሺህ ገጾች ያሉት ‹ኮሜንትሪ› ስለ ካህሊል በተናገራቸው አስደማሚ ገለጻዎች በኩል ወደ ደብዳቤዎቹ ላሻግራችሁ፡፡
"Kahlil Gibran… the very name brings so much ecstasy and joy that it is impossible to think of another name comparable to him. Just hearing the name, bells start ringing in the heart which doesn’t belong to the world. Kahlil Gibran is pure music, a mystery such that only poetry can grasp it, but only sometimes.
…[He] is a man who is the most of this beloved earth. Centuries have passed; there has been great name but khalil Gibran is a category in himself. I can’t conceive that even in the future there is a possibility of another man of such deep insight into the human heart, into the unknown that surrounds us."       
ኒውዮርክ
እሁድ ግንቦት 26፣ 1912 እ.ኤ.አ
መንፈሴ ዝግጁ ቢሆንም አካሌ ተዝለፍልፎልሻል፡፡
ውድ ሜሪ፤ ደህና አይደለሁም፡፡ መላ ህዋሴ፣ እግዜርን፣ ሕይወትን ምልዓቱን የምገናኝበት አረንጓዴ ከባቢ በመሻት እየቃተተ ነው፡፡ ጸደይ በኮረብቶች መካከል እየተርገበገበች እየደነሰች፣ ሰው የሆነች ጠባብ የጭለማ ክፍል ውስጥ መታጎር የለበትም። ውጭ የሚያስደንቅ አስደሳች ቀን ሆኗል። ሆኖም ለባብሼ ለእግር ጉዞ ለመውጣት የሚያበቃ አካላዊ ጥንካሬ የለኝም፡፡
መቼስ አንቺም በጥቂቱ እንኳን ደክሞሽ መሆን አለበት፡፡ አይ አይ… ለካ አንቺ መቼም ደክሞሽ አያውቅም! ህመም አያውቅሽም፡፡ አካልሽ እንደ መንፈስሽ ሁሉ ሁልጊዜ ንቁ፣ ዘወትር ዝግጁ፣ ምንጊዜም ጉጉ ነው፡፡ ልክ እንደ ሊባኖስ ዝግባ የተትረፈረፈ ጥንካሬ ባለቤት ነሽ፡፡
እነዚያ ሰዎች ዛሬ ከሰዓት እንዳይመጡ እመኛለሁ፡፡ እኔ እና አንቺ ብቻ በደኑ ውስጥ በዛፎች መካከል እየተመላለስን እንድናወራ፣ የእንጆሪ ፍሬዎች እንድንበላም ፍላጎቴ ነበር።   
ኒውዮርክ
ረቡዕ የካቲት 7፣ 1912 እ.ኤ.አ
ዛሬ ልቤ ምልዑ ሆኖልሻል፡፡ እንግዳነት፣ ስክነትና ጽሞና ያረበባቸው ጥላዎች አጥለቅልቀውታል፡፡ ለምን አትይም? ትናንት ማታ በሕልሜ ኢየሱስን አየሁታ፡፡ የተለመደ ወዳጃዊነት የሚነበብበት ፊት፣ ትላልቅ እና የእሳት ላንቃ የመሰሉ፣ እሳት የሚተፉ ጸጥተኛ ዓይኖች፣ አዳፋ ቡኒ ግራጫ መጎናጸፊያ፣ ረጂም የከዘራ ምርኩዝ፣ እና ደግሞ የተለመደ በአርምሞ፣ በአባባይ ልስልስ ስሜት ወደ ሕይወት የሚማትር ገር መንፈስ…
ኦ… ሜሪ ሜሪዬ ለምንድን ነው በየዕለቱ፣ በየምሽቱ ኢየሱስን በሕልሜ ደጋግሜ የማላየው? የእርሱን ግማሽ በሚያህል መሰጠትስ እንኳ ሕይወትን መገርመም የማልችለው ለምንድን ነው? በዚህ ዓለም ላይስ እንደ እርሱ በጣም ተርታ፣ ቀላልና ገር ሆኖ ግን ደግሞ መግነጢሳዊ የወዳጅነት የስበት ግለት ያለው አንድስ እንኳን ሰው ማግኘት ያልቻልኩት ለምንድን ነው?  
ኒውዮርክ
ቅዳሜ ጥር 6፣ 1912 እ.ኤ.አ
ከዛሬ ይልቅ ያለፈው ማክሰኞ እንደ ልደት ቀኔ ነበር፡፡ የእነዚያ የማክሰኞ ዕለት ጥቂት ሰዓታት እሙናዊነት ወደ ሆነ አዲስ የትህፍስት፣ የሕማም፣ የሕይወት አተያይ የንቃት ጽንፍ የሚመራ በር ነበር፡፡ ከዚያች የማክሰኞ አመሻሽ ጀምሮ ልጽፍልሽ ደጋግሜ መሞከሬ አልቀረም፡፡ ሆኖም ልጽፍልሽ በምቀመጥበት በእያንዳንዱ ቅጽበት ከጥልቅ ውቅያኖስ የሚመነጭ፣ ወይ ካልተደረሰባቸው፣ ካልታሰሱ ግዛቶች የሚነሳ አሊያም ባልታወቁ አማልክት የሚታዘዝ የሚመስል የሆነ ዓይነት እንደ አንዳች የሚጫን ክቡድ አርምሞ ይቆጣጠረኛል። ይህንን ደብዳቤ በምጽፍልሽ በዚህች አፍታ እንኳን በሕይወት ውስጥ እጅጉን አስደንጋጩ ቅንጣት ጭምትና ስዱድ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡
ከኃያሉ ማዕበል መነሳት በፊት ያሉት ሰዓታትም ሆነ ከአስደሳችም ሆነ ከአስከፊ ክስተቶች ቀጥለው የሚመጡት ቀናት ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ጭምት፣ ጥልቅ፣ በንቅናቄ አልባ ነበልባሎችና በተዘረጉ አክናፍ የተሞሉ …
ኒውዮርክ
እሁድ ጥር 21፣ 1912 እ.ኤ.አ
የአርምሞው ሰዓት ገና ስላላለቀ በትንሹ ስቱዲዮዬ መስኮት በኩል በገሃነምና መንግስተ ሰማያት መካከል በሚተላለፉ ጥላዎች ላይ አፍጥጬ ቆሜልሻለሁ። ሕይወትን ከዚህ በፊት ቀምሷት እንደማያውቅ እንግዳ ሰው እየኖርኳት እገኛለሁ፡፡ ቀናት በሚፋጁ ሀሳቦች፣ ሌሊቶች እንግዳ በሆኑ ህልቆ መሳፍርት ሕልሞች ተሞልተዋል፡፡ በቀኑ መጨረሻና በሌሊቱ መጀመሪያ መካከል የሚከሰተው የምሽቱ ጊዜ እንደ አይነርግብ ነው፡፡ ለዚያውም ሰባት እጥፋቶች ያሉት ጌጠኛ አይነርግብ…
በሕይወት ውስጥ ብዙ የሚያንገፈግፍ ደስታ አለ፤ ብዙ ጥዑም የሆነ ስቃይም እንደዚሁ… እናም ያንቺው ካህሊል የሆነችን ስዕል እንዴት መሳል፣ ወይ የሆነችን አንዲት መስመር ሀሳብ እንዴት ማስፈር እንዳለበት በቅጡ ይገነዘብ ዘንድ ወደ ሀሴትና ሰቆቃ ጥልቅ ያለማመንታት መዘፈቅ አለበት፡፡
ኒውዮርክ
ሐምሌ 8፣ 1914 እ.ኤ.አ
ውድ ሜሪ፤ አንቺ እጅግ የበዛ ሰዎችን የመረዳት መክሊት የተሰጠሽ ሰው ነሽ። ሕይወትን አዳይ ነሽ፡፡ አንቺ ለመጋራት ሳይሆን ሕይወቱን ለማበልጸግ የሆነን ሰው እንደሚወዳጅ ታላቅ መልዓክ ነሽ፡፡ በኑረት ዘመኔ ከአንቺ ጋር መተዋወቄ ከምልዓተ ዓለሙ ተፈጥሯዊ ስልተ ምትና ስልተ ስሪት ውጪ የሆነ አስደናቂ ተዓምር ነው፡፡
‹‹ዘ ማድማን› በተሰኘ መጽሐፌ እንደገለጽኩት፣ የሚረዱን ሰዎች ከሕይወታችን ውስጥ የሆነውን ነገር በቁጥጥራቸው ሥር ያደርጉብናል፡፡ አንቺ ጋ ይሄ የለም፡፡ የአንቺ እኔን መረዳት ከማውቃቸው ሁሉ በተለየ ነጻነትን የሚያጎናጽፍ ሰላማዊ ነው፡፡ ባለፈው የመጨረሻ ጉብኝትሽ ልቤን በመዳፍሽ ይዘሽ ከላዩዋ ላይ ነቁጥ የምታክል ጥቁር ነገር አገኘሽ፡፡ በዚያችው ቅጽበት ጥቁሯ ነጥብ ለዘለዓለም ከልቤ ላይ ተፋቀች፤ እኔም ሙሉ ለሙሉ ከእስራቴ ነጻ ወጣሁ፡፡
ይሄው አሁን ደግሞ የተራራ ላይ ብህትውና ላይ ነሽ፡፡ በበኩሌ በረቂቅ፣ ስውር፣ ውብ መሬቶች ላይ መናኝ ከመሆን በላይ የሚያስደስት ምንም ነገር እንደሌለ አምናለሁ፡፡ ሆኖም ተወዳጇ ሆይ፤ ምልዓቱን ሀሰሳን የተራበች ነፍስሽ በአንድ ሰሞን ጀብድ ብቻ እንደማትረካ አውቃለሁና አጉል መዳፈርን ተጠንቀቂ፡፡ ምክንያቱም ለዳግም የሀሰሳ ጉዞ ወደ ተራራ መውጣት ትችይ ዘንድ ደኅንነትሽ መረጋገጥ አለበት፡፡ ቤቴ በላክሻቸው አሪቲና ጠጅ ሳር መልካም መዓዛ ታውዶልሻል፡፡ ስለላክሽልኝ እግዚአብሔር ይባርክሽ፡፡  
ኒውዮርክ
ሐሙስ የካቲት 8፣ 1912 እ.ኤ.አ
የሚካኤል አንጀሎ ሶኔቶች(በአስራ አራት ስንኞች የሚቀነበብ የግጥም አንድ ቅርጽ) ከሌላ ከማንኛውም ነገር ይልቅ መንፈሴን የሚያርበተብት አንዳች ነገር አላቸው፡፡ ሚካኤል አንጀሎ ሰውዬውን ከሥራዎቹ መለየት በእጅጉ አዳጋች ነው፡፡ በሚካኤል አንጀሎ ነፍስ ላይ የታተመው ትልቁ ሀቲት በድን፣ ግዑዝና ንቅናቄ አልባ ይመስላል። ወደ መቃብር ጉድጓዱ ያዘገመው እንኳን ራሱም በቅጡ የማያውቀውን የተለጎመ ጉልበት፣ ኃይል (silent power) በልቡ ተሸክሞ ነው፡፡ ሕይወቱን በሙሉ ሊገልጹት የሚያስቸግር ጠጣር ሀዘን ተሸካሚ ሆኖ ያለፈውስ ምናልባት ለዚህ ይሆን?
ኒውየርክ
አርብ ህዳር 10፣ 1911 እ.ኤ.አ
በአረብኛ ‹‹በልቤ ያለውን የምናውቀው አላህና እኔ ነን፡፡›› የሚል አንድ የቆየ መዝሙር አለ፡፡ እናልሽ ዛሬ የመጨረሻዎቹን ሦስት ደብዳቤዎችሽን ደግሜ ካነበብኩ በኋላ  ጮክ ብዬ ‹በልቤ ያለውን የምናውቀው አምላክ፣ ሜሪና እኔ ነን፡፡› ብያለሁ፡፡ ቢሆንልኝ ሌሎች ሰዎች በቀላሉ ይገነዘቡኝ ዘንድ ልቤን አውጥቼ በመዳፎቼ ይዤ ብዘዋወር እወዳለሁ፡፡ ምክንያቱም እኛ ሰብዓዊያን መሰሎቻችን እንዲረዱን እንዲያውቁን ከመፈለግ ይልቅ ሌላ ጥልቅ መሻት የለንም፡፡ ሁላችንም በጋን ውስጥ እንደሚያድር ኩራዝ፣ በውስጣችን የታፈነው ብርሃን ለዓለም ወጥቶ ቢታይ ምኞታችን ነው፡፡
የመጀመሪያው ገጣሚ የዕብድ በሚመስሉ ቃላቱ፣ በሚያላግጡ የዋሻ ውስጥ ነዋሪዎች የፌዝ ሳቅ ስላቅ በእጅጉ ተሰቃይቶ መሆን አለበት፡፡ ምናልባት የፀሐይ ግባቱ አስደናቂ የብርሃን ድግምት በነፍሱ ጥልቅ ሥርቻ የፈጠረውን መደነቅ መሰሎቹ ይረዱለት ዘንድ ለማግባባት ደጋኑን፣ ቀስቶቹን፣ የአንበሳ ቆዳውን ያለውን ነገር ሁሉ ለማባበያነት በስጦታ አቅርቦም ይሆናል፡፡
እናስ ኪናዊ ለፈጠራ የመቅበጥበጥ ስሜት የሚለኩሰው ይህ ያለመታወቅ፣ ልብ ያለመባል፣ ያለመደመጥ ቁጭት አይደለምን? ጥበብ ለጥበብነቱ ብቻ ይከወን ማለት በእርግጥም የከበረ አባባል ነው፡፡ ሆኖም የመዓልትና የሌሊትን ንብርብር ጸጥተኛ ትህፍስትን ይጋራን ዘንድ የሆነን ሰው ስሁት የመንፈስ ብርሃን ማንቃት፣ ማብራት የበለጠ ክቡርና አስደናቂ አይሆንምን? እውነተኛ ጥበብ እምቅ ውበቱን ለሰዎች መግለጽ የሚችል ተጨባጭ ሊሆን ይገባላ፡፡
ስቱዲዮዬ በእጅጉ ማራኪ ናት፡፡ ከዚህች ስቱዲዮ ውጪ በሌላ የትም ቦታ በቤቴ የሆንሁ ያህል ተሰምቶኝ አያውቅም። እና ደግሞ እየሰራሁ ነበር፡፡ ለእኛ ዘወትር ምልዓቱን በማደን ተቅበዝባዥነት ለተሰለፍን፣ ንጡልነታችን እንደ ሽርሽር ለሚቆጠርብን ኪነታዊያን፣ ዘለዓለም ከማይረካ የመፈለግ ጥማታችን ውጭ ሌላ ምን አለን?  
ከዕለታት የሆነ ቀን የተፃፈ
ለእኔ እንግዳ ከሆነ ከማላውቀው ክልል ስትበሪ የመጣሽ የገነት ወፍ ሆይ፤ አሁን ሰዓቱ ለእብደት ሜዲቴሽን ሩብ ጉዳይ ሆኗል።
በጃፓን አንድ ንጉሥ ነበረ። ይህ ንጉሥ አንድ ቀን በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ሁሉንም ሰዓሊያን ሰብስቦ ከመካከላችሁ ‹‹የሚመስል ሳይሆን እውነተኛ (real) የሆነ ስዕል የሚስል አንድ ሰው እፈልጋለሁ፡፡›› አለ።
ሁሉም ሰዓሊያን ከባዱን ኃላፊነት ለመሸከም ሲያመነቱ፣ አንድ ሰዓሊ ግን ‹‹ጊዜ ያለ ገደብ ከተሰጠኝ እውነተኛ (real) የሆነ ስዕል እኔ መስራት እችላለሁ። ነገር ግን ሠርቼ እስክጨርስ ድረስ ማንም ሰው እንዲያይብኝ አልፈልግም›› አለ።
ተፈቅዶለት ስራውን ጀመረ። አንድ፣ ሁለት፣ ስድስት ዓመታት ተቆጠሩ። ንጉሡ ጅጅት ብሎ ጃጀ። በመጨረሻ ሰዓሊው ስዕሉ መጠናቀቁን አብስሮ ንጉሡን ብቻ ይዞ ወደ ስዕሉ አዳራሽ ገባ።
የሳለው በር እና መንገድ ነበር። ንጉሡና ሰዓሊው ያንን የስዕል በር ከፍተው ከገቡ በኋላ ይሄው እስከ ዛሬ አልተመለሱም።
እኔም እንደ ንጉሡና ሰዓሊው የምትሃቱን በር ከፍቼ ወደ ምንም መሄድ ያምረኛል። ብናኝ፣ ፍናኝ አንዳች ሆኜ እስክከስም መጓዝ ያምረኛል። ካንቺ ጋ ቢሆን ደግሞ…
ይህ መስኮት ከአንቺ  ጋር  ካልሆነ በድን ኦና ነው እሚሆንብኝ። ከሌሎች መስኮቶች በምን እለየዋለሁ? ለሁሉም ነገር ትርጉም የምትሰጪልኝ አንቺ ነሻ! አስቀድሞ ድንጋይ የነበረ እሱ፣ አንቺና እኔ ከተቀመጥንበት በኋላ ግን ቅርስ፣ ትዝታ ይሆናል። አስቀድሞ በቡና ቤትነት ብቻ የማውቀው የሆነ ቤት፣ አንቺን ለአንድ ቀን ብቻ ከቀጠርኩበት በኋላ ግን ቤተ መቅደሴ ነው። የነቃች ነፍስ ስላለችሽ ጥላሽ ያረፈበትን ሁሉ ታሻግሪዋለሽ (your very existence transcendes everything)- አንድ ቀን ጣቶችሽ ጣቶቼን የነኳቸው ዕለት፣ ያኔ ለዘለዓለም እንዳልተኛ ሆኜ ለምባትት ለእኔ ወዮልኝ…
በይ የገነት ወፍ ሆይ፤ ልሰናበትሽ… አሁን ለእብደት ሜዲቴሽን ሙሉ ሰዓት ሆነ…

Read 447 times