Monday, 09 August 2021 18:00

"አይሻልም ፍቅር!" - (ወግ)

Written by  መሳይ ደጉአለም
Rate this item
(0 votes)

  Hi ፍቅር...
ይቺን ቅይጥ ሀረግ መዝዤ የጀመርኩት ባለፈው አንዷ ቆንጅዬ ወዳጄ፤ “አሁን በዚህ ዘመን ማነው እንዲህ የሚል?” ብላ ስላሾፈችብኝ ይመስለኛል...
ያው የአንዱ lame ለሌላው ዐለምም አይደል?!”
ደግሞም ‘በነገር’ ስጀምርልሽ፣ ያው ደጋግመሽ ያሰመርሽበትን ነገረኝነቴን እንደማመን እያደረገኝም...
አይዞሽ... ንጭንጭ ብቻ አይደለም።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በተጠናቀቀው በጀት አመት፣ ከ15 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን አስመልክቶ ድክም ስላለው፣ ሰሞኑን ከኔ ቤት የስራ እረፍት ወስዷል ይኸውልሽ።
እኔ ወዳጅሽ ታድያ ይህንን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፣ በሻማ ካነበብኳቸው ጥያቄዎችሽ፣ አንድ ሁለቱን ለመመለስ መቀመጤ ነው...
‘ደብዳቤሽን’ አነበብኩት...
መቼም እንደ አጭሯ ወዳጄ፤ “አሁን በዚህ ዘመን ማን ደብዳቤ ይፅፋል?” ብዬ አልከፋብሽም።
ያንቺ መፃፍ ግን ትንሽ ትንሽ ይገርማል መሰል...
ያው እንደኔ ልሙጥ ሉክ ገዝቶ በቀይና ሰማያዊ እስክሪብቶ፣ ፅጌረዳ አበባ መሳል ከተለማመደው ትውልድ አይደለሽም ብዬ ነው...
“ልጅ አልከኝ” ብለሽ፤ ጓ እንዳትዪ አደራ።
ያው ያ መምህር እንዳለው፤ “ነጭ ነጩን” ነው...
እውነቴንም አይደል?!
ሰፊ ግቢ ውስጥ ተንጣሎ ከተሰራ አራት ምጣድ የሚደረድር ኩሽና ውስጥ ተንጠልጥሎ የከረመ ቋንጣ ሰርቀሻል?
አልሰረቅሽም!
ሹራብሽን በጣቶችሽ ወደፊት ወጥረሽ፣ በሁለት እጅሽ የተቀበልሽውን የሚፋጅ እንጀራ፣ በአረንጓዴ ጠርሙስ ከሚቀመጠው የተወቀጠ ጨው "ነስንሱልኝ" ብለሽ በልተሻል?
አልበላሽም!
ኧረ እንደውም ሳስበው ሳስበው፣ "አስር አረንጓዴ ጠርሙሶች"ን ሁላ አልዘመርሽም... ብትዘምሪም ብዙዎቹ ጨውና አረቄ እንደሚቀመጥባቸው አታውቂም... አየሽ ድንገት በየተራ ወድቀው ሲሰበሩ ቁጥር ብቻ ነው የሚሆኑት ላንቺ...
የአረቄውን ነገር...
የጨዉን መቸገር... የት ታውቂና?
እና ደብዳቤ መፃፍሽ ቢገርመኝ፣ ምንም አይገርምም።
“ልጅ” ብልሽም፤ አክብሬ የፃፍሽውን በሻማ ከማንበብ አልተመለስኩምና አታኩርፊ...
ለነገሩ የፃፍሽው ነገር ደብዳቤ ከመባል ድብድብ ቢባል ነው እሚሻል...
ብዙዎቹን “እንዲህ ነህ... እንዲያ ነህ...” የሚሉ ድምዳሜዎችሽን ወድጃቸዋለሁ። ሰዎች ስላንቺ ፍፁም እርግጠኛ ሲሆኑ እንዴት ደስ የሚል መዝናኛ መሰለሽ...
ደግሞም ልክ ነሽ!
በዚህ ዘመን የሰው እውነት፣ ከአባቱ ስም ነው እሚጀምር...
ከዛ ገፋ ቢል በሚወክለው ባርኔጣ ትለዪዋለሽ...
ነፍሱን ይማርና George Carlin የተባለ ነጭ ሽማግሌ፣ stand-up comedian ‘ሁሉም ኅይማኖት ባርኔጣ አለው... ጎራ ለይቶ የሚለጣለጠው በባርኔጣው አይነት ነው!’ ይል ነበር።
እሱ ነገር ግን አይገርምሽም?
እዚህ እኛ ሀገር ደግሞ... ገግሞ፤ “እኔ ኅይማኖቴ ጥበብ ነው!” ለሚለው እንኳን ከ’ስካርፉ ጋ አብራ የማትቀየር daddy cap አለችው...
እና የሰውን እውነት ከሩቁ ማወቅ እንደ ድሮው ጥንቆላ አይደለም። ልክ ነሽ!
ምን ያልተቀላቀለ አለ ብለሽ ነው ዘንድሮ?
ብቻ መቆም እብደት ነው።
ይታይሽ ሀገር የሚያስተዳድር ፓርቲ፤ “ምረጡልኝ...” ብሎ... ዲያቆን፣ ፓስተር፣ ዑስታዝና የፍልስፍና መምህር ይደረድርልሻል።
ሰው ኮፍያ እንደሚመርጥ የገባው ብልህ፣ በቀላሉ ነው እሚያሸንፍ እንግዲህ...
እና ያልሺኝን ሁሉ አምኜ፣ የጠየቅሺኝን ብቻ ልመልስ።
“ለምንድነው ካገኘኸው ሰው ጋ ከምትቧጨቅ... ብቻህንም ከምትብሰለሰል... ሙግትህን የማትፅፈው? ፍርሀት ነው?”
እውነትሽን ነው። ፍርሀት ነው!
የሌለ ነው እምፈራው።
አንደኛ፤ ሌሎችን እፈራለሁ!
ድሮ ድሮ “አንብብ... ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል...” ምናምን የሚሉኝን ሰዎች፣ ብዙ አከብራቸው ነበር ይኸውልሽ...
ወፋፍራም መፅሀፍት አቅፈው ሰፈር ውስጥ በሚንጎማለሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የምቀናውን ያክል፣ የልጅነት ፍቅረኛዬን ሚሊፎኒ ኬክ ቤት እየወሰደ በሚጋብዛት የሰፈራችን ሀብታም ልጅ እንኳን አልቀናም ነበር...
አድጌ ከነሱ ጋር ለክርክር ለመቀመጥ ስንት library ዳክሬያለሁ መሰለሽ...
Little did I know ለካ ለነሱ ማንበብ ማለት የራሺያ ትርጉም ልብወለድ፣ በስሜት መሸምደድ ነበር...
ዘንድሮም “ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል!” ካሉ አይመለሱም...
መወዳደርያው እሱ እያለ ይሻል ነበር መሰል ግን... አየሽ የሆነ ሰው ድንጋይ ሀሳብ ይዞ ሲመጣ “አይ ስለማታነብ ነው...” ተብሎ ኩም ይደረግና ዝም ይላል...
ራሽያ ስንቱ በልብወለድዎቿ ተመርቆ፣ ስንት ቀበሌ እንዳንቀጠቀጠ ብትሰማ፣ አሁንም ድረስ ለዘለቀው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነታችን ተጠናክሮ መቀጠል መልካም አስተዋፅኦ ይኖረዋል ባይ ነኝ።
ምንም እንኳ ወፋፍራሞቹን መጻሕፍት እንዳማረኝ ሳላነብ ብቀርም፣ ከዚህኛው ዘመን እንዳቅሚቲ ተጠቅሜያለሁ ባይ ነኝ...
እኩዮቼ የShaggy ዘፈን ‘ወዝሚ’ ነው እሚለው ብለው ሰጨቃጨቁ፣ “እንግሊዘኛ ያነብባል” ተብዬ ለዳኝነት ተጠርቼበታለሁ...
“It Wasn’t Me ነው የሚለው...” ብዬ “አንተ ደሞ... አወቅክ አወቅክ ስትባል...” ተብዬ ብሞለጭበትም። ለዳኝነት መጠራቱንስ ማን አየበት? እኔው ነበርኩ ያበዛሁት።
አሁን አሁን ሰው ብዙ ያነብባል...
አንቺ ያነበብሻቸውን መጻሕፍት ያላነበበ ከስንት አንድ ነው... መፅሐፉም በሽ ነው ያው...
ስንት የታሪክ መፅሐፍት አሉን... በቃ information ትጠያለሽ... ያው ሰው እሱን ሰብስቦም አይደል ሁሉን ወደ ጨረሰ ተንታኝነት የሚገባው?
አንድ አይነት ነገር አንብባችሁ ፍፁም ተቃራኒ ከሆነ ድምዳሜ ላይ ከደረሳችሁ ወዳጅሽ ጋ ማውራትን የሚያህል የሚያስፈራ ምን ነገር አለ በልደታ?
ጭራሽ ፅፎ መረጃ ማስቀረት...
ሆ... እፈራለሁ እንጂ። እንዴት ነው የማልፈራው ፍቅር?
“ባርኔጣህ እንዲህ ያለው አይነት ስለሆነ ነው እንደዚህ ያሰብከው...” ብለው ቢያለብሱኝስ?
ባርኔጣ ለኔ አይሆንም...
አንዴ ከደረብኩት ይቺ ስስት ያለች ፀጉሬን መልጦ፣ ጥገኛው ሆኜ መቅረቴ ነው...
ስለዚህ ሰውንና ባርኔጣውን አብዝቼ እፈራለሁ...
እናም ዝም... እላለሁ!
ሁለተኛም እራሴን እፈራለሁ!
ለምንድነው የማልፈራው?
አየሽ ድሮ ድሮ በአንባቢዎቹ በምቀናበት ዘመን አንድ ትልቅዬ ምኞት ነበረኝ...
physics አስተማሪዬ ጥቁር ሰሌዳ ላይ ሲጠበብ፣ የሚረብሸኝን የቾክ ፉጨት ችላ ብዬ፣ አፌን ከፍቼ ነበር የምሰማው...
እና “ሳድግ...” ለሚለው ምኞቴ ቅፅበት ሳልጠብቅ የምሰጠው መደምደሚያ፣ እሱን አስተማሪዬን የሚያኽል ፊዚክስን ማወቅ ብቻ ነበር...
የመጀመርያ ዐመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለሁ ነው፣ ፈላስፋው መምህሬ፣ እዛው ግቢ የማታ ተማሪ እንደሆነ የደረስኩበት...
ያው አንዳንድ የቁጥር ችግሮች ሲገጥሙት የሚደውልልኝ መልካም ወዳጄ ሆነ በስተመጨረሻ...
ይታይሽ---ይሄንን የሚያክል መፈንቅለ-ህልም የተፈፀመው፣ በአምስት በስድስት ዐመታት ውስጥ ብቻ ነው...
እርግጥ ነው፣ ያው አንቺም እንደምታውቂው፣ ላለፉት አስር ዓመታት ገደማ እንዲሁ ስዳክር ነው ያለሁት... ግን ደግሞ የዛሬ አምስት አመቴንስ በምን አውቃለሁ?
ዛሬ “ልኬ” ባልኩት፣ ያኔ ሽምቅቅ እልስ እንደሁ?
መቼስ ይኸው ሰሞኑን እንዳየሽው፣ ሀበሻ ሆኖ ‘መሳሳት’ ለማይወድ ሰው ኑሮ ውዝግብ ነው!
አባይ ቀን ወጥቶለት ቤት ለቤት በገመድ መምጣት ቢጀምር እንኳ፣ ይኼን ያክል ሰው በአምፖል ፍቅር ይወድቃል ብሎ ማን ጠረጠረ?
እና እራሴን እፈራለሁ...
ይኼኛው... ወዝጋባው ‘እኔ፣’ ምናልባት ተስፋ ሊኖረው የሚችለውን የነገውን ‘እኔን’ እንዳያሸማቅቀው አብዝቼ ነው እምፈራው...
“መብራት ማታም ባይመጣስ?” ብዬም እፈራለሁ...
ስለዚህ ስልኬ ተዘግታ የሌሊት መጀናጀኛ እንዳላጣም፣ ሌላ ሌላ ጥያቄሽን ሌላ ሌላ ጊዜ ልመልሰው...
አይሻልም ፍቅር...?

Read 1153 times