Monday, 09 August 2021 00:00

“ዋናው የፍልስፍና ጥያቄ የሕይወት ትርጉም ነው”

Written by  ተፈሪ ዘ ካዛንቺስ
Rate this item
(3 votes)

    ደራሲና ፈላስፋውን በጨረፍታ
                                 

           አልበርት ካሙ ፈረንሳዊ ደራሲ፣ ፈላስፋ፣ ጋዜጠኛ፣ ጸሐፌ-ተውኔትና ተዋናይ ነው። የተወለደው ጥቅምት 7 ቀን 1913 ዓ.ም ሞንዶቪ አልጀሪያ ውስጥ ነው፡፡ ገና ጨቅላ ሳለ አባቱን በሞት በማጣቱ ያደገው በእናቱ እጅ ነው፡፡ የልጅነት ጊዜውን ያሳለፈው በአስከፊ ድህነት ውስጥ ነበር፡፡ በአልጀርስ ዩኒቨርሲቲ ፍልስፍናን ተምሯል፡፡ በ1934 ዓ.ም የአስራ ዘጠኝ አመት ጎረምሳ ሳለ፣ የመጀመሪያ የትዳር አጋሩን ሲሞን ሃይን አገባ፡፡ ሆኖም በሚስቱ አመንዝራነት ምክንያት ከአንድ አመት በኋላ ትዳራቸው በፍች ተቋጭቷል፡፡ በ1940 ዓ.ም ሁለተኛ ሚስቱን ፒያኒስትና የሒሳብ ሊቋን ፍራንሲን ፋውርን በ26 አመቱ አገባ፡፡ ከእሷ ሁለት መንታ ልጆችን አፍርቷል፡፡
ካሙ በ1957 ዓ.ም ታላቁን የኖቤል ሽልማት በሥነ-ጽሑፍ ተሸልሟል፡፡ ገና በጎልማሳነት እድሜው በመኪና አደጋ ቢቀጭም፣ እጅግ ታላላቅ የሥነ-ጽሑፍና የፍልስፍና ሥራዎችን ለዓለም አበርክቷል። በ1942 ዓ.ም “ዘ ስትሬንጀር” የተሰኘ የልብወለድ ሥራውን አሳትሟል፡፡ የዚህ ሥራ ዐቢይ ጭብጥ አብዘርዲዝም ነው፡፡ በዚሁ ዓመት ያሳተመው ታላቅ የፍልስፍና ሥራው "ዘ ሚዝ ኦፍ ሲዝፈስ ኤንድ አዘር ኢሴይስ” ይሰኛል፡፡ የዚህ ሥራ ዐቢይ ግብ ራስን የመግደል (suicide) ተግዳሮትን መቅረፍ ነው፡፡
 ካሙ ወደ ሥነ-ጽሑፉ ዓለም እንዲቀላቀል በጎ ተፅእኖውን ያሳረፈበት የፍልስፍና መምህሩ የነበረው ዣን ግረነር ነው፡፡ ካሙ የእውቁ ፈረንሳዊ ኤግዚስቴንሻሊስት ዣን-ፖል ሳርተር የቅርብ ወዳጅ ነበር። ሆኖም ወዳጅነታቸው ከዘጠኝ አመት በኋላ በ1952 ዓ.ም ተቋጭቷል፡፡ በሁለቱ መካከል መቃቃር እንዲፈጠር ያደረገው ዐቢይ ምክንያት፣ ካሙ በኮሚኒዝም ላይ ያንፀባርቀው የነበረው ፅኑ ታቃውሞ ነው። ምንም እንኳ ካሙ ፈረንሳዊ ቢሆንም፣ አገሩ በአልጀሪያውያን ላይ የምታደርሰውን የቅኝ አገዛዝ ቀንበር አጥብቆ ይቃወም ነበር፡፡ ሳርተር፤ ካሙ ኤግዚስቴንሻሊስት መሆኑን ቢያውጅም፣ እሱ ግን የሳርተር ስያሜ ፍፁም የተሳሳተ መሆኑን ገልጿል፡፡ አንዳንድ ጸሐፊዎች ደግሞ፤ ካሙ ኤግዚስቴንሻሊስት ሳይሆን አብዘርዲስት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ካሙ የኖቤል ሽልማቱን ከተቀበለ ከሦስት ዓመት በኋላ ከጓደኛው ሚሸል ጋሊማርድ ጋር በመኪና ወደ ፓሪስ ከተማ እየሄዱ ሳለ፣ በመኪና አደጋ፣ በተወለደ በ47 አመቱ አረፈ፡፡
***
ካሙ ቀደምቱን የአውሮፓ ፍልስፍና በፅኑ ከተቹ ፈላስፎች አንዱ ነው፡፡ እንደ እሱ እሳቤ፣ ቀደምቱ የአውሮፓ ፍልስፍና ትኩረቱን ከሰው ልጅ ተጨባጭ ህልውና እጅግ በራቁ (abstract) ጉዳዮች ላይ ያደረገ ነው፡፡ ካሙ እንደሚለው፤እጅግ አንገብጋቢው የፍልስፍና ተግዳሮት #ራስን ማጥፋት; ነው፡፡ በተቃራኒው፤የቀደምት ፈላስፎች ትኩረት ግን ከዚህ መሠረታዊ ተግዳሮት እጅግ በራቁ ጉዳዮች ላይ (በሜታፊዚክስ ጥናት) ያደረገ ነበር፡፡ ካሙ “ዘ ሚዝ ኦፍ ሲስፈዝ” በተሰኘው ሥራው ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ብሏል፡    
There is but one truly serious philosophical problem, and that is suicide. Judging whether life is or is not worth living amounts to answering the fundamental question of philosophy. All the rest—whether or not the world has three dimensions, whether the mind has nine or twelve categories—comes afterwards. These are games; one must first answer. And if it is true, as Nietzsche claims, that a philosopher, to deserve our respect, must preach by example, you can appreciate the importance of that reply, for it will precede the definitive act. These are facts the heart can feel; yet they call for careful study before they become clear to the intellect. If I ask myself how to judge that this question is more urgent than that, I reply that one judges by the actions it entails. I have never seen anyone die for the ontological argument (Camus, 1955:11)
ፈጣሪ የለም የሚለው ካሙ እንደሚነግረን፤ በዚህ ፈጣሪ አልባ ፅንፈ-ዓለም (universe) ውስጥ የሰው ልጅ ሕይወት ፋይዳ ቢስ (meaningless) ነው፡፡ ነገር ግን ካሙ ኢ-አማኝ  አይደለም፡፡ ይህን በተመለከተ "ኖትቡክስ" በተሰኘ ሥራው እንዲህ ጽፏል፡
“I often read that I am atheistic; I hear people speak of my atheism. Yet these words say nothing to me; for me they have no meaning. I do not believe in God and I am not an atheist.”
ካሙ ይህን ቢልም እንደ ኤሚሊ ሚሃይ ቾራን፤ ኒሂሊስት ግን አይደለም፡፡ ቾራን ዐቢይ የኒሂሊዝም አቀንቃኝ ፈላስፋ ነው፡፡ ለቾራን ሕይወት ሙሉ በሙሉ ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ በመሆኑም፣ በጎው ነገር ሁሉ ከእኩዩ፣ ሞራላዊው ተግባር ከኢ-ሞራላዊው ጋር እኩል ነው፡፡ በጎውም ሆነ እኩዩ ነገር ትርጉም አልባና ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ "ዘ ስትሬንጀር" የተሰኘው የካሙ የልብወለድ ሥራም  ተመሳሳይ የግብረገብ አቋምን የሚሰብክ ነው፡፡ በዚህ ልብወለዱ ውስጥ ለተሳለው ዋናው ገጸ-ባሕርይ (protagonist) ሜርሳልት፤ በእኩይና ሰናይ ተግባር መካከል መሠረታዊ ልዩነት የለም፣ ሁሉም ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ ገጸ-ባሕርዩ አረቡን ሰው በመግደሉም ሲፀፀት አናገኘውም፡፡
ምንም እንኳ የኒሂሊስቶች አቋም ቀቢፀ-ተስፋ ያጠለበት ቢሆንም፣ ሕይወት በጠቅላላ ትርጉም አልባ ሊሆን አይችልም፣ ምክንያቱም እያንዳንዱ ሰው ሕይወቱ ውስጥ ጥቂት ትርጉም ያላቸው ነገሮች አይጠፉም፡፡
አንዳንድ ግለሰቦች በሕይወት ውስጥ ዐቢይ ትርጉም በማጣታቸው ራሳቸውን አጥፍተዋል፡፡ ነገር ግን ለካሙ ራስን መግደል እጅግ የሚወገዝ ተግባር ነው። እንደ እሱ እሳቤ፤ ራስን መግደል ለወለፈንዲነት (absurdity) ፈፅሞ መፍትሄ መሆን አይችልም፡፡ በኑሮአችን ትርጉም እንድናጣ ዐቢይ ምክንያት ከሆኑት አንዱ በተመሳሳይ ሁኔታ የሚነጉደው ግብ አልባው ዘወትራዊው ኑሮአችን ነው፡፡ ይህን በተመለከተ #ዘ ሚዝ ኦፍ ሲስፈዝ; በተሰኘው ሥራው እንዲህ ይላል፡
“the stage sets collapse. Rising, streetcar, four hours in the office or the factory, meal, streetcar, four hours of work, meal, sleep, and Monday Tuesday wednesday Thursday Friday Saturday and Sunday according to the same rhythm.”
ካሙ እንደሚለው፣ ትክክኛው የወለፈንዲነት መፍትሄ አመፅ (revolt) ነው፡፡ በመሆኑም፣ ምንም እንኳ ሕይወት ፍፁማዊ የሆነ ፋይዳ የሌለው ቢሆንም፣ የሰው ልጅ ይህን ሕቅ ተቀብሎ ግላዊ ትርጉምን በመፍጠር የመኖር ኃላፊነት አለበት፡፡ እንዲህ አይነቱ ሕይወት ለእሱ ትክክለኛ (authentic) ሕይወት ነው፡፡ ለካሙ ትክክለኛ ሕይወት የሲስፈዝ አይነት ነው፡፡ ሲስፈዝ በግሪኮች አፈ-ታሪክ ውስጥ የሚገኝ አማልክት ነው፡፡ ይህ አማልክት እጅግ ከባድ ጥፋት በመፈፀሙ፣ ኃያላን አማልክት፣ ተራራ ጫፍ ሲደርስ መልሶ ቁልቁል የሚንከባለል ግዙፍ ቋጥኝ፣ ለዘላለም እያመላለሰ እንዲኖር ፈረዱበት። ይህ ልፋቱ ግን ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ አይነት ከንቱ ነበር። ሲስፈዝ የሚወክለው የእያንዳንዳችንን ሕይወትና ዕጣ ነው፡፡ ቋጥኙ የሕይወታችን ሸክም ምሳሌ ነው፡፡ ሁላችንም ይህን ሸክም ተሸክመን  ዘወትር ተመሳሳይ ጉዞ እንጓዛለን፡፡ መኖር ዕዳ ነውና ዕጣችንን ከመቀጠል ውጪ ሌላ አማራጭ  የለንም፡፡ ካሙ እንደሚነገረን፣ ምንም እንኳን የሲስፈዝ የኑሮ ዕጣ ፋታ በሌለው ድግግሞሽ የተሞላ ቢሆንም፣ ይህን በድግግሞሽ የተሞላ ፋይዳ ቢስ ዕጣውን በፀጋ ተቀብሎ በጀግንነት በመጋደል ሕይወቱ ፋይዳ ያለው እንዲሆን አድርጓል፡፡ እንደ ካሙ እሳቤ፣ በኑሮ ሂደት ውስጥ አብዘርዲቲን መጋፈጥ በራሱ ታላቅ (ultimate) ፋይዳ ነው፡፡ ለኒሂሊስቶቹ ግን በሕይወት ውስጥ ጨርሶ ፋይዳ ያለው ነገር የለም፡፡ ይህ አይነቱ አቋም ነው ኒሂሊስቶችን ከአብዘርዲስቱ ካሙ ጋር የሚያቃርናቸው፡፡       


Read 3035 times