Saturday, 07 August 2021 14:22

"ፊቱን ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ-"

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)


            እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ!
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ፣ ዛሬ በምን ትዝ አልኩህ?
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ! እኔ ጠዋት ማታ ከአንተ ሀሳብ መቼ ተለይቼ አውቃለሁና! ከአንተ ሌላ ምን ቀረኝና ነው እንድዬ!
አንድዬ፡- እንደሱ ሳይሆን በሬን ካንኳኳህ ሰነበትክ ብዬ ነው፡፡ ነው ወይስ ተመቸህ?
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ተው እንደሱ እያልክ ሆዴን አታባባኝ! ምን ይመቸኛል አንድዬ! ለራሴ ሁሉም ነገር ግራ ግብት ብሎኝ ምን ምቾት አለ!
አንድዬ፡- ግራ ገባኝ ካልከኝ እኮ ከረምክ። በመጣህ ቁጥር እንደዛ ሳትል ተመልሰህ አታውቅም እኮ! ግራ መጋባትህ ለእኔ አዲስ ነገር አይደለም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- እንደሱ አይደለም አንድዬ፣ እንደሱ አይደለም፡፡ የአሁኑ ግራ መጋባት ከበፊቱ በጣም የተለየ ነው፡፡ ሌላ ቃል ስላጣሁ ግራ መጋባት አልኩኝ እንጂ ነገሩስ ከዛም በጣም የባሰ ነው፡፡
አንድዬ፡- ቃላት ስላጣሁ ነው ያልከኝ!?
ምስኪን ሀበሻ፡- አዎ፣ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡- ተው እንጂ፣ ምስኪኑ ሀበሻ፣ ስስቅ ትን ቢለኝ ምን ትጠቀማለህ?
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ! አንድዬ...
አንድዬ፡- እሺ በቃ፡፡ እንደዚህ እያልኩ ሆድህን አላባባውም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ አንዳንድ ነገር ስሜቱ እየተሰማን ምን በሚል ቃል ሊገለጽ እንደሚችል ግራ የሚገባ ነገር አለ አይደል...እንዴት ብዬ ላስረዳህ እንደምችል ቸግሮኝ እኮ ነው፡፡
አንድዬ፡- አሁን ደግሞ ጭራሽ ባስረዳህም አይገባህም እያልከኝ ነው!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ!
አንድዬ፡- ረጋ በል እንጂ፡፡ አንድ ቃል በተናገርኩ ቁጥር እየተርበተበትክ እኔንም እንደ ልቤ እንዳላወራ አደረግኸኝ እኮ!
ምስኪን ሀበሻ፡- ይቅርታ አንድዬ፣ ይቅርታ፡፡
አንድዬ፡- እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ።
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ አንድ ብቻ ሳይሆን የፈለግኸውን ያህል ጠይቀኝ፡፡
አንድዬ፡- እኔ ዘንድ ስትመጡ ትህትናችሁ፣ መሽቆጥቆጣችሁ፣ ሁሉ ነገራችሁ ይለይብኛል፡፡ እኔ የፈጠርኳችሁ እንኳን "እነሱ ናቸው ወይስ ከሌሎች ጋር አሳስቻቸው ነው" እላለሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- ይህን ያህል እየጠፋንብህ አንድዬ!
አንድዬ፡- ቆይ እንጂ ልጨርስ፡፡ ከአፍ ከአፌ እየነጠቅህ ምኑን ተናገርኩት!
ምስኪን ሀበሻ፡- ይቅርታ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡- አሁን እንድትመልስልኝ የምፈልገው፣ ምድር ላይ እያላችሁ ለምንድነው የዚህን ግማሽ ያህል እንኳን የማታከብሩኝ፣ ትህትና የማታሳዩኝ?
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ተው እንደሱ አትበል፡፡ አንተን ካላከበርን ማንን እናከብራለን?
አንድዬ፡- እኔስ ግራ ያጋባኝ ይኸው አይደል!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እንደውም በአሁኑ ጊዜ ድፍን ሀገር በለው፣ ሁሉም ወደ አንተ እያንጋጠጠ ነው፡፡  የቀረኸን እኮ አንተ ነህ!
አንድዬ፡- እንደዛ ከሆነ ለምንድነው በስሜ የምትቀልዱት፣ የምትነግዱት?
ምስኪን ሀበሻ፡- አ...አንድዬ፣ ምን እያልከኝ እንደሆነ አልገባኝም፡፡ ደግሞ አንድዬ፣ ተ...ተቆጥተሀል?
አንድዬ፡- አዎ ተቆጥቻለሁ፣ አንዳንዴ በተራዬ ብቆጣ ምናለበት!
ምስኪን ሀበሻ፡- ምንም፣ ምንም የለበት አንድዬ፡፡ የአንተ ቁጣ እኮ ቡራኬ ነው፡፡ 
አንድዬ፡- ይሄን አላውቅም ነበር፣ ስለነገርኸኝ ተባረክ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አሜን አንድዬ! ግን...
አንድዬ፡- ግን ምን፡፡ አታልጎምጉማ...
ምስኪን ሀበሻ፡- እሺ አንድዬ፣ እሺ። አሁን እኛ የቸገረን ነገር ቢኖር ምድር ላይ ተቆጪ በዛብን፡፡ እንደውም አንድዬ...  አንዳንዶቹማ ከመቆጣት አልፈው ጭናችሁ ስር ገብተን በቁንጥጫ እንመዝልጋችሁ ሊሉን ምን አልቀራቸው፡፡
አንድዬ፡- ታዲያ ምናለበት! የባሰውን ከሚያመጡባችሁ በቁንጥጫ መገላገል አይሻልም?
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ አንተም እንዲህ ትላለህ?
አንድዬ፡- ለምን አልልም፣ እንቆንጥጣችሁ ቢሉም፣ እንናዳችሁ ቢሉም፣ እንጋልባችሁ ቢሉም -- ራሳችሁ ያመጣችሁት ጣጣ ነው።
ምስኪን ሀበሻ፡- ምን አጠፋንና አንድዬ፣ እኛ ምን አጠፋንና! አልደረስንባቸው፣ አጥራቸውን አልነቀነቅንባቸው፣ ጎረቤቶቻቸው አይደለን! ባህርና ውቅያኖስ መሀላችን እያለ ያን ሁሉ ተሻግረው እኮ ነው አድራጊ ፈጣሪ ካልሆንን የሚሉት!
አንድዬ፡- ስማኝ ምስኪኑ ሀበሻ...ገና ከጅምሩ አንድ ሁለት ማለት ሲጀምሩ፣ "ወዲህ ውጡ፣ ወዲያ ውረዱ" ማለት ሲጀምሩ፣ ያኔ ቆፍጠን ብላችሁ “እዛው በጠበላችሁ፣ ስለ እኛ ጉዳይ ከእኛ የተሻለ የሚያውቅ የለም!” ብትሏቸው ኖሮ፣ አሁን የደረሳችሁበት ደረጃ አትደርሱም ነበር፡፡ እስቲ እንደናንተ ተረት እንድተርት ፍቀድልኝ።
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ሆነ ብለህ ነው አይደል እንደዛ የምትለኝ!
አንድዬ፡- የእናንተን ተረት ለመተረት ፈቃድ ብጠይቅ ምን ችግር አለበት? እንዲሁ እኮ እጃችሁን አጣጥፋችሁ ተቀምጣችሁ ነው ማዶ ያሉት ጤፉን እንኳን የእኛ ነው ሲሏችሁ የነበረው፡፡ አሁን ትፈቅድልኛለህ ወይስ አትፈቅድልኝም?
ምስኪን ሀበሻ፡- እሺ አንድዬ፣ እ...ሲ!
"ፊቱን ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ
አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ"
አንድዬ፡- የምትሉት እናንተው አይደላችሁም እንዴ! በል ንገረኛ...  እንዲህ የሚል ተረት የላችሁም?
ምስኪን ሀበሻ፡- እሱማ አለን፡፡
አንድዬ፡- እኮ ፊቱን መጥናችሁ ሳትደቁሱ ቀርታችሁ አሁን ቤተኛውም፣ ጎረቤቱም አላፊ አግዳሚውም፣ በእናንተ ጉዳይ ያገባኛል ባይ ቢሆን ምን ይገርማል!
ምስኪን ሀበሻ፡-  አንድዬ፣ ሁሉም እኮ ከጥንት ጀምሮ እኛ ላይ....
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ፣ መቼም ብዙዎቻችሁ ጉተታ ይሆንላችኋል...እኔንም ጎትተህ ፖለቲካችሁ ውስጥ  ልታስገባኝ ነው!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ!
አንድዬ፡- አትደንግጥ! ከእኔ ጋር አይደለህም እንዴ ያለኸው! እንደው በምኑም በምናኑም፣ በወሬውም በአሉባልታውም እየደነገጥክ እስከ መቼ!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እሱም እኮ አንድ ግራ የመጋባቴ ምልክት ነው፡፡ ብቻ የሆነ ክብድ የሚል ነገር እንዲህ ራሴ ላይ የሚሽከረከር ነው የሚመስለኝ፡፡
አንድዬ፡- ማርስ ከምትሉት ቦታ የመጡ እንዳይሆኑ!
ምስኪን ሀበሻ፡- እየቀለድክብኝ ነው፣ አይደል አንድዬ?
አንድዬ፡- ብቀልድብህስ! ቅድም የአንተ ቁጣ ቡራኬ ነው ብለኽ አልነበር?
ምስኪን ሀበሻ፡- አዎ፣ ብዬ ነበር፡፡
አንድዬ፡- እኮ አሁን እየቀለድክብኝ ነው ከማለት ቀልድህ ቡራኬ ነው ለምን አጽለኝም!...ተወው፣ ተወው በቃ ፊትህ ቀላብኝ፡፡ ቅድም ስጠይቅህ የነበረውን ግን አልመለስክልኝም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- ምኑን አንድዬ?
አንድዬ፡- ምድር ላይ ስትሆኑ ለምን እንደማታከብሩኝ ጠይቄህ ነበር፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ኸረ እያከበርንህ ነው!
አንድዬ፡- ለዚህ ነዋ ሀገር ጉድ ሊፈላበት ነው፤ ከዳር ዳር ዋይታ ሊሆን ነው፣ ህዝቡ መከራውን ሊበላ ነው፣ እሪታ ይሆናል ለቅሶ ይሆናል፣ ምናምን ይሆናል... እያላችሁ በእኔ ስም ህዝቡን የምታሸብሩት ብታከብሩኝ ነው!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ...
አንድዬ፡- ቆይ አንድ የመጨረሻ ነገር ልጠይቅህ፡፡ እኔ የጥፋት አምላክ ነኝ?
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ..
አንድዬ፡- ስማ ሌላው ሌላው ይቅርና ለወገኖችህ ይህን ንገርልኝ፡፡ እኔ የጥፋት አምላክ አይደለሁም ብሏል በላቸው። ጥፋት ካለ፣ መከራ ካለ፣ ችግር ካለ፣ ራሳችሁ በራሳችሁ ላይ የምታመጡት እንጂ የእኔን ስም ከዚህ ውስጥ አውጡልኝ ብሏል በልልኝ፡፡ በል ደህና ግባ!
ምስኪን ሀበሻ፡- አሜን አንድዬ፣ አሜን!
ደህና ሰንበቱልኝማ!

Read 901 times