Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 08 September 2012 11:49

የማየት ፍሬ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

“ድህነት ጠፍንጐ ይዞን ነው እንጂ አበላሉንስ እናውቅበት ነበር”

ሁለት

ለንደን እንደ ገባሁ ራሴን ከብልቃጥ ወደ ባሕር የተሸጋገረ አሣ አድርጌ ቆጠርሁት፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ አንድ ቦታ ከጠፋኝ የመንደሩ ሰው “ደርሰሃል ከስልክ ግንዱ ወደ ግራ እጥፍ ስትል ታገኘዋለህ!” እያለ ተግቶ ይመራኛል፡፡ በለንደን የገጠመኝ ግን አገሬ ማሪኝ የሚያስብል ነው፡፡አንዴ ሁሉ ነገር የአይን አዋጅ ሆኖብኝ ግራና ቀኙን እየሾፍሁ ስገሰግስ፣ ሳላውቀው ከሆቴሌ በጣም ርቄ ኖሮ መመለሻው ግራ ገባኝ፡፡ ወደ አንድመጽሐፍት ሱቅ ገብቼ በይሉኝታ ውድ መጽሐፍ ገዝቼ ሳበቃ፣ ሻጩን Travel Lodge የተባለው ሆቴል የት እንደሚገኝ ጠየኩት፡፡ ሻጩ ምንም ሳይል ከመሳቢያው ውስጥ እንደ ጃክሰን ፓሎክ የአብስትራክት ሥዕል የተወሳሰበ ካርታ አውጥቶ አቀበለኝ፡፡ በካርታው ላይ ለግማሽ ሰዓት ያክል እንደ ምሥር ለቃሚ አቀርቅሬ ቀና ስል ዞረብኝ፡፡ የሆቴሌን አድራሻ ማግኘት ቀርቶ የገባሁበት ሱቅ በር ራሱ ጠፋኝ፡፡

“የሸዋ ክፍለሀገርን በሰሜን ወሎ፣ በደቡብ ሲዳሞ ያዋስኑታል” ከሚል ያለፈ የካርታ ንባብ ያላስተማሩኝን የጥንት መምህሮቼን በልቤ እየረገምኩ፣ እንደወጣሁ መቅረቴን በስልክ ለወዳጆቼ አስታወቅሁ፡፡

በለንደን ባቡሩ፣ አውቶብሱ፣ ፈረንጁ ሁሉም በተቀጠረበት ሰዓት ከተፍ ይላል፡፡ ባልተቀጠረበት ሰዓት የሚመጣው ዝናባቸው ብቻ ነው፡፡ ያገራችን ዝናብ ቢያንስ የተሰጣ ብቅል እስክናስገባ ድረስ ይታገሣል፡፡ የለንደኑ ግን ይሉኝታ ቢስ ነው፡፡ እኔ በደረስኩበት ወቅት ባውሮፓ ጥቢ ገብቷል፡፡ ሴቶቹ እንደ ዓይነ ርግብ ውበታቸውን ሸሽጐባቸው የቆየውን ክረምት ለመበቀል ተገላልጠው የሚወጡበት ወቅት ነው፡፡ ልጃገረዲቱ ፀጉሯንተተኩሣ፣ ግልገል ቀሚሷን ለብሣ፣ ጡቷን እንደ ቸርችል ሃውልት ሁሉ ሰው በሚያየው ቦታ ላይ አቁማ እየተውረገረገች ትወጣለች፡፡ ይኼኔ ከጠራ ሰማይ ላይ አድፍጦ የቆየ ባለጌ ዝናብ፣ እንደ ወፍ አይነምድር ሿ ብሎ ከላይ እስከታች ያለብሳታል፡፡ እየተነጫነጨች ጥግ ለመያዝ ትገደዳለች፡፡

ከዝናባቸው ቀጥሎ ብሽቅ ሆኖ ያገኘሁት ቁርሣቸው ነው፡፡ አንድ እፍኝ የባቄላ ንፍሮ፣ አንድ ጭልፋ እንቁላል ጥብስ እና አንድ ለብ ያለ ድፍን ቲማቲም ካቀረቡልኝ በኋላ ከምግቡ ጋር የማይመጣጠን ደንዳና ፈገግታ ቦግ አርገው enjoy your breakfast ይሉኛል፡፡ እንደሰማሁት ከሆነ እንግሊዞች የራሳቸውን ቁርስ አይወዱትም፡፡ ታሪክ መሥራት ብቻ ሳይሆን ቁርስ መሥራትም እንችላለን ለማለት ያህል ንፍሮአቸውን ለኔ ካቀረቡ በኋላ ለራሳቸው በጓሮ በር በኩል ወደ ጣልያን ሬስቶራንት ጐራ እንደሚሉ ገመትሁ፡፡

ሁሌም በቁርስ ሰዓት ሹካና ቢላዋዬን አመሳቅዬ ሰሀኔ ላይ እንዳቀረቀርሁ ትዝ የሚለኝ “ድህነት ጠፍንጐ ይዞን ነውንጂ አበላሉንስ እናውቅበት ነበር” የሚለውን የጊዮን አለምሰገድን አባባል ነው፡፡ (ጊዮን ባንድ ክረምት ለጓደኞቹ ስለ በቆሎ አጠባበስ ማብራሪያ ይሰጣል “አሁን አንድ ጥሩ በቆሎ ቢገኝ ትሸለቅቀውና ወተት ትቀባዋለህ፤ ከዚያ ትንሽ ማር ታልሰዋለህ፡፡ ትቀጥልና የተፈጨ ጨው ነስነስ ነስነስ ታደርግበታለህ፣ ከዚያ በወይራ ፍም ላይ ታገላብጠዋለህ፡፡ ተወኝ ባክህ ድህነት ጠፍንጐ ይዞን ነውንጂ አበላሉንስ እናውቅበት ነበር” ሲል ተከዘ)

የመቅመስ እድል ባይኖረኝም እንግሊዞች ሹካ የሚያስቆረጥም የጥንቸል ሥጋ ጥብስ እንደሚሠሩ ሰምቻለሁ፡፡ የጥንቸል ሥጋ ጣዕሙ ክሽን ብላ እንደተሠራች ዶሮ ነው ብሎኛል አንዱ፡፡ አንባቢዬ እዚህ መስመር ላይ ሲደርስ ምራቁን እንደሚውጥ አውቃለሁ፡፡

ታዲያ ፍላጐቱ ካለ ጥንቸል አምርተን የማንመገበው ለምንድነው? ጥንቸል መብላት ኢትዮጵያዊ ባህል ስላልሆነ ነው የሚል ምላሽ እጠብቃለሁ፡፡ ግን’ኮ አቮካዶ መብላትም ባንድ ወቅት ኢትዮጵያዊ ባህል አልነበረም፡፡ እናቶቻችን ብዙ የጥራጥሬና የፍራፍሬ አይነቶችን ከሌሎች ሕዝቦች ወስደዋል፡፡ ምሥርን ከግብፃውያን፣ ቲማቲም ከጣልያኖች ተቀብለዋል፡፡ አቮካዶ ቀይ ባህርን የተሻገረው በልጅ ኢያሱ ዘመን በበጀሮንድ ተክለሃዋርያት ቦርሣ ነው፡፡

ከብርቱካን ጋር ያስተዋወቁን የፖርቱጋል ቄሶች ናቸው ይባላል፡፡ የጥንቱ አበሻ ፖርቱጋል ለማለት ብርቱጋል ይል ነበር፡፡ ብርቱካን ከዚያ የወጣ ቃል ነው፡፡ በቆሎ ዛሬ ቤተኛ ቢመስልም በቅርብ መቶ ዓመታት ከምድረ አሜሪካ የመጣ መፃተኛ ነው፡፡ የእንግድነት ስሙ “የባህር ማሽላ” ይባላል፡፡ በሁሉም ረገድ ስናያት ኢትዮጵያ “በጐደለ ሙላ” ስልት የተፈጠረች አገር ናት፡፡

አባቶቻችን አዳዲስ ፍራፍሬና ጥራጥሬ ከውጭ ለመቀበል ፈጣን የሆኑትን ያህል የሥጋ ምርጫዎቻቸውን ለማብዛት አልጣሩም፡፡ የዚህ ምክንያት በባህላችን ላይ የገነነው ኦሪታዊነት ይመስለኛል፡፡

ከኦሪት በፊት የነበረችው ኢትዮጵያ ሰፋ ያለ የሥጋ ምርጫ እንደነበራት የምናውቀው የሙሴ ድምጽ በማይደርስበት ቦታ ተሸሽገው የኖሩ፣ እንደ ነገደ ወይጦ ያሉ ጥንታዊ ሕዝቦችን አመጋገብ ስንመለከት ነው፡፡ ብዙዎቻችን እንደምናውቀው ሙሴ እንስሳትን እርኩስና ቅዱስ ብሎ መድቧል፡፡ እንደ ሙሴ ምደባ ጥንቸል የሚያመሰኳ እንስሳ ቢሆንም ሸሆናው ክፍት ስላልሆነ እርኩስ ነው፡፡ ልንመገበው አይገባም፡፡ ዘመናይ የእንስሳት ተመራማሪዎች ጥንቸልን ቀርበው ሲመለከቱት ሙሴ እንደ ተሳሳተ ገባቸው፡፡ ጥንቸል አያመሰኳም፡፡

ሙሴ በድንጋይ ዘመን የገነነ አንድ የአይሁድ እረኛ በመሆኑ ቢሣሣት አይገርምም፡፡ የሚገርመው የእርሱ ኢ - ሳይንሳዊ የሥጋ ምድባ የአመጋገብ ባህላችንን ለሺህ ዓመታት ያህል መምራቱ ነው፡፡ ሥጋን ስናስብ አስቀድሞ ወደ ሐሳባችን የሚመጣው፤ ገበሬ ሊሆን “ገ” የቀረው በሬአችን ነው፡፡

አንዲት ላም አንድ ጥጃ ለመስጠት 286 ቀን ያላነሰ ጊዜ ታስጠብቀናለች፡፡

አንዲት ጥንቸል ግን ከባለቤቷ ጋር በተሣረረች በሰላሳ ቀኗ አንድ ደርዘን ግልገሎች ለእንግሊዙ አርብቶ አደር ታበረክታለች፡፡ የጥንቸል ግልገል እንደ ሰው ልጅ ጡጦ አጉርሱኝ አይል፣ የምሳ እቃዬን ሙሉልኝ አይል በተወለደ በአሥራ አራት ቀኑ በግጦሽ ራሱን ይችላል፡፡ በተወለደ ባንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለአቅመ መሶብ ይደርሳል፡፡

ጥቂት ለፍቶ ብዙ ሥጋ ማምረት የሚፈልግ ሰው ነገሩን ቢያጤነው ጥሩ ነው፡፡

አሁን ደግሞ ስለለንደን እርፍና ልናገር፡፡ ለንደን የምር ስልጡን አገር ናት፡፡ እንደ ሱልጡን አገሮች ሁሉ በውስጧ ላሉት ሁሉ ነፃነት እና ዕድል እንደ ቢጤይቱ ትሰጣለች፡፡ ጳውሎስ ኞኞ ባንድ ወቅት “ነፃነት ማለት የሌላውን ነፃነት ሳይነኩ ነፃ መሆን ነው” ብሎ የፃፈውን በመዲናይቱ ቆይታዬ ተገንዝቤዋለሁ፡፡

ዕድል መስጠት የሚለውን ሐረግ የሚያብራራልኝ ገጠመኝ ልጥቀስ፡፡ አንድ ቀን፣ እኔና አንጋፋው ደራሲ ጃርሶ ኩሩቤል ወደ ማዕከላዊ ለንደን የሚወስደንን ባቡር እንጠብቃለን፡፡ በባቡሩ ጣቢያ የሕዝብ የጋራ ንብረት የሆነ ፒያኖ ተቀምጧል፡፡

ችሎታ አለኝ የሚል ሁሉ መጥቶ ችሎታውን ሊያሳይ ይችላል፡፡ እኛ በጥበቃ ላይ በነበርንበት ጊዜ አንዲት ባለወርቃማ ፀጉር ሴትዮ ከዋናው መንገዷ ተዘንጥላ መጣችና ዘንቢሏን አስቀምጣ፣ ቀሚሷን ሰብሰብ አድርጋ ከፒያኖው ፊት ለፊት ተቀመጠች፡፡ የኖታ ደብተሮችን ገለጥ ገለጥ እያደረገች አንድ ዜማ ተጫወተች፡፡ ስትጨርስ፣ ዘንቢሏን ብድግ አድርጋ ያቋረጠችውን መንገድ ቀጠለች፡፡ ባቡር ጠባቂው ሁሉ ሞቅ ባለ ጭብጨባ ሸኛት፡፡ እኔ “አንድ አለብሽ” የሚል ዘፈን ስቅም ስላደግሁ ረቂቅ ሙዚቃ የሚመዝን ጆሮ የለኝም፡፡ ጃርሶ ግን አይኖቹን ጨፍኖ፣ አንገቱን ወደ ፒያኖው አቅጣጫ ዘመም አርጐ ገብስማ ረጅም ጢሙን እየዳበሰ ሲያዳምጥ ነበር፡፡ ጃርሶ ከደራሲነቱ ያልተናነሰ ፒያኒስት መሆኑን ስለምሰማ፡-

“…እንዴት ነው?...ስል ጠየኩት፡፡

“ግሩም አድርጋ ትጫወታለች…” አለ፡፡

አገሬ ከተመለስሁ በኋላ ላንዱ ተራቢ ጓደኛዬ ይህንን ገጠመኝ አወጋሁትና “ገንዘብ ቢኖረኝ አንድ ፒያኖ ገዝቼ መሀል ፒያሳ አስቀምጠው ነበር፡፡ ችሎታ ያላቸው ዕድሉ የሌላቸው ያገሬ ልጆች ይጫወቱበታል” አልሁት፡፡

“የማይሆን ነገር ነው!” አለኝ ጓደኛዬ

“ምነው?” አልሁት፡፡

“ጠዋት መሀል ፒያሳ ያስቀመጥከውን ፒያኖ ከሠዓት መርካቶ ልታገኘው ትችላለህ!”

***

በሌላ ቀን የቴምዝን ወንዝ ድልድይ ሳቋርጥ አንድ አንድ የፈረንጅ ለማኝ አየሁ፡፡ (በነገራችን ላይ የተጋባዥ ገጣሚያን ጊዜያዊ ሠፈር የተመሠረተው ከለንደን ኩራቶች አንዱ በሆነው ቴምዝ ወንዝ ዳርቻ ላይ ነው፡፡ ቴምዝ ቅልጥ ባለ ከተማ እምብርት መሐል የሚፈስ በመሆኑ ጀልባዎች ከመኪናዎቹ ጋር እየተጋፉ ይሄዱበታል፡፡ እኔ ያዋሽ ልጅ፣ እኔ የተከዜ ልጅ፣ እኔ የባሮ ልጅ፣ ቴምዝ ወንዝ ነው ብዬ ለመቀበል ብዙ ጊዜ ወሰደብኝ፡፡ አንድ ወንዝ ሐቀኛ ወንዝ የሚሆነው ከራስጌው ውሃ የምትቀዳ ሴት ከግርጌው ውሃ የሚጠጣ ወይፈን ሲያካትት ነው፡፡ እንግዲህ ይሄ የገጠር ልጅነቴ ወይም ያፈወርቅ ተክሌ ሥዕል ተፅእኖ ያመጣው ሳይሆን አይቀርም፡፡)

ታዲያ አንድ ቀን የቴምዝን ድልድይ ሳቋርጥ አንድ የፈረንጅ ለማኝ አገኘሁ፡፡ ከእግሩ ሥር አሮጌ ጊታር አጋድሞ፣ የልመና ሰሌዳ ደረቱ ላይ አንጠልጥሎ ሳየው የሆነ ባለጌ ደስታ ወረረኝ፡፡ ወደ ፈረንጁ ለማኝ ቀርቤ እንደ ሁዳዴ አውራ ዶሮ ጅንን ብዬ አንድ ባውንድ ወረወርኩለት፡፡ ወረወርኩለትና በእርካታ እጄን አራግፌ፣ ደረቴን ነፍቼ ለአምስት ደቂቃ አጠገቡ ቆምኩ፡፡ ፎቶ ለመነሣትም ቃጥቶኝ ነበር፡፡ ያ ባለጌ ደስታ ከየት መነጨ? በኔ ቤት በዚያች ቅፅበት ኢትዮጵያ እንግሊዝ እየመፀወተች ነው፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት ሃያ ሁለት ማዞሪያ መንገድ ላይ የተመለከትሁት ትርኢት መጣብኝ፡፡ ቀን የጣለው ጃማይካዊ ጐልማሣ የቀዳማዊ ሃይለ ሥላሴን ፎቶ እንደ ጠልሰም አንጠልጥሎ በእንግሊዝኛ ሲለምን ነበር፡፡ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ድፍን ድፍን አሥር ብቻ ከጃማይካዊው ጭን ሥር ይራገፍ ጀመር፡፡ አልፎ ሂያጁን ሁላ እንዲህ ለጋስ ያደረገው ምን ነበር? እንደ ኤሊ በድንጋይዋ ሥር ተሸሽጋ የምትኖር ኢትዮጵያዊ Superiority Complex አለች፡፡ ለካስ አዲስ አበቤ የሚለግስ መስሎ በውጭ አገሩ ሰውዬ ላይ የበላይነቱን ለማረጋገጥ እየተሽቀዳደመ ኖሯል፡፡

(ይቀጥላል)

 

 

Read 2780 times Last modified on Saturday, 08 September 2012 12:17