Print this page
Saturday, 07 August 2021 14:06

ባለመመረቃችን ብናዝንም ከሁሉም ሰላም ይቀድማል

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(7 votes)

ከአክሱም ዩኒቨርሲቲ የመጣችው ተማሪ ኢየሩሳሌም ታደሰ


           መንግስት ከህወኃት ጋር የተገባውን ጦርነት ተከትሎ ሰኔ ወር ላይ የተናጠል ተኩስ አቁም ሥምምነት ማወጁ ይታወሳል፡፡  የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት ከታወጀ በኋላ መከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ክልል ለቆ ሲወጣ ተማሪዎች በአክሱምና በመቀሌ ዩኒቨርስቲዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ ነበሩ። በዚህም ከሰኔ 24 ቀን ጀምሮ የተማሪዎቹ ወላጆች በጭንቀት ላይ ነበሩ፡፡ መንግስት ልጆቻችውን ከክልሉ እንዲያወጣላቸው ሲማጸኑም ነበር፡፡ አዲስ አድማስ ጋዜጣም በሰኔ 26 ቀን 2013 ዓ.ም እትሙ ከነዚህ ወላጆች የጥቂቶቹን አቤቱታ ይዞ መውጣቱ የሚታወስ ሲሆን ከአንድ ወር የጭንቀትና የስጋት ጊዜ በኋላ ከመቀሌና ከአክሱም ተማሪዎቹ በሰላም ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተቀላቅለዋል፡፡ ከነዚህ ተማሪዎች መካከል እናቷ ወ/ሮ ሙሉ ታሪኩን ከአንድ ወር በፊት በጋዜጣችን ላይ ስለ አንድና ብቸኛ ልጃቸው በጎዳና ላይ እንዴት እንዳሳደጓት በእንባ ታጅበው ነግረውን ነበር። ልጃቸው ተማሪ ኢየሩሳሌም ታደሰ ባለፈው አንድ ወር ተማሪው ያሳለፈበትን ሁኔታ ከራሷ ተሞክሮ ተነስታ ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ እንደሚከተለው አጫውታታለች እነሆ፡፡


         እንኳን በሰላም ከቤተሰብሽ  ጋር ለመቀላቀል አበቃሽ
አሜን! አሜን! አመሰግናሁ።
የመከላከያ ሰራዊት መውጣቱን ስትሰሙ ምን ተሰማችሁ?
ያው መከላከያ እንደወጣ እነሱ ወዲያው ገቡ፡፡
እነሱ ማን ናቸው?
የትግራይ ሀይሎች ማለቴ ነው፡፡ እነሱ እንደገቡም “በጀት የለም አለቀ” ተባለና ማስተማር አቆሙ። ከዚያም ሰኔ 21  ተሰብስበን “የበጀት ችግሩ፤ እስኪስተካከል በየቤታችሁ ቆዩ” ተብለን ነው እንግዲህ የመጣነው፡፡
መከላከያ ከትግራይ በወጣበትና እናንተ ወደ ቤተሰብ በመጣችሁበት መካከል በትንሹ የአንድ ወር ልዩነት ነበር። ያንን ጊዜ በምን ሁኔታ ነው ያሳለፋችሁት? ምንስ ችግር ገጠማችሁ?
በእርግጥ ያን ያህል የተጋነነ ችግር አልገጠመንም፤ ነገር ግን ባንክ ዝግ ስለነበር ተማሪው ከባንክ ገንዘብ ማውጣት ባለመቻሉ ችግር ገጥሞት ነበር፡፡ በዚህም ልብሱን የሸጠ ተማሪ ሁሉ ነበር።  የዩኒቨርስቲው ካፌ ለእኛ ማድረግ የሚችለውን ያቅሙን ያህል አድርጓል፡፡ በቀን ሁለት ጊዜ እየተመገብን ችግሩን ለመቋቋም ሞክረናል፡፡
የፀጥታ ችግርስ አልገጠማችሁም…?
ገና መከላከያ እንደወጣ አንዳንድ ተማሪዎች በየዶርሙ እየገቡ የሌሎች ተማሪዎችን የሞባይል ሥልኮችና ሌሎች እቃዎችን መስረቅ ጀምረው ነበር፡፡ ተማሪው ሌላውን ተማሪ መስረቅ ጀምሮ ነበር፡፡ ከዚያም ወዲያው የትግራይ የፀጥታ ሀይሎች መጡና መጠበቅ ጀመሩ። ወዲያውኑ ሰላም ሆነ፡፡
የትግራይ የፅጥታ ሀይሎች ተማሪውን ለመተናኮል አልሞከሩም?
አይ አልተተናኮሉንም፤ የገጠመን ችግር የለም።
የአክሱም ህዝብ ለእናንተ የነበረው ስሜት እንዴት ነበር?
የአክሱም ህዝብ በጣም ደስ የሚል ህዝብ ነው፤ የቻለውን ሁሉ ሲያደርግልን ነበር። በተለይ የእኛ ወላጆች ከየክፍለ ሀገሩና ከአዲስ አበባ  መጨነቃቸውና መላቀሳቸው ሲሰማ፣ የአክሱም ህዝብ ደግሞ “ወላጅ ለምን ይጨነቃል? እነዚህ ልጆች ወደ የወላጆቻቸው መላክ ነው ያለባቸው” እያሉ ሲከራከሩልን ነበር። በመጨረሻም ለእኛ ወደ ቤተሰብ በሰላም መላክ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገውልናል፡፡ እናም በጣም ደስ የሚሉ ናቸው። በዚህ አጋጣሚ ስላደረጉልን ሁሉ ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡
ምን ያህል ተማሪ ነው ከአክሱም ዩኒቨርስቲ ወደ የቤተሰቡ የተላከው?
እርጠኛ ባልሆንም ከ3 ሺህ 600 በላይ ተማሪ ነው ሲባል ሰምቻለሁ፡፡
ከአክሱም ተነስታችሁ አዲስ አበባ እስክትደርሱ የነበረው የጉዞ ሁኔታ ምን ይመስላል?
መጀመሪያ ከአክሱም ወደ መቀሌ መጣን፤ ከዚያም ከመቀሌ አፋር ነው የገባነው፡፡ አፋር ስንደርስ የትምህርት ሚኒስቴር ተቀብሎ እስከ ወላጆቻችን አደረሰን። አሁን በሰላም ከቤተሰብ ጋር ተገናኝተን ደስ ብሎናል፡፡
ከአፋር በፊት የነበረውን ጎዟችሁን በማን አማካኝነት ነው የመጣችሁት?
እስከ አፋር በቀይ  መስቀል ማህበርና በተባበሩት መንግስታ (UN) ድጋፍ ይመስለኛል የተጓዝ ነው፡፡ አፋር ስንደርስ ግን ትምህር ሚኒስቴር ተቀብሎንና ሰመራ ዩኒቨርስቲ አድረን ትላንት ጠዋት ተነሳን በነጋታው ጠዋ ተነስተን (ማክሰኞ ማለት ነው) ማታ አዲስ አበባ ገባን፡፡
በሜካኒካል ምህንድስና ዘንድሮ ተመራቂ ነበርሽ አይደል?
ትክክል ነው፤ ሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ነው የተማርኩት። ዘንድሮ  ተመራቂ ነበርኩ። ሶስት ሳምንት አካባቢ ነበር የቀረን´ኮ ኮርሱን ለመጨረስ ማለቴ ነው፡፡ አምስት ዓመት ነው የፈጀብን።
ዘንድሮ ለመመረቅ በጉጉት ስትጠብቁ ነበርና… የተፈጠረው ሁኔታ ምን ስሜት ፈጠረባችሁ?
ይሄ በጣም የሚያሳዝን አጋጣሚ ነው። በዚህ ሰዓት ሁሉም ዩኒቨርስቲ ተማሪዎቹን እያስመረቀ እያስወጣ ነው። ይህን በጉጉት በምንጠብቅበት ሰዓት ሌላ ችገር ውስጥ መግባት ያሳዝናል፤ ደክመሽ ደክመሽ ለውጤት ልደርስ ነው ስትይ፣ ይሄ መሰናክል ሲፈጠር፣ ሞራል ይነካል። በሌላ በኩል፤ ነገር ግን ችግሩ ከተከሰተ በኋላ በጣም ስንጨነቅ ስናስብ የነበረው ስለመመረቁ መሆኑ ቀረና እንዴት ነው ወደ ቤተሰቦቻችን ሰላም የምንገባው የሚለው ጉዳይ ሆነ፡፡ ይሄው ከስንት ጭንቅና  ሰቀቀን በኋላ ደግሞ ከቤተሰቦቻችን በሰላም ተቀላቅለናል ቀጣዩን የሚያውቀው ደግሞ ፈጣሪ ነው፡፡
መንግስት “በዚህ ጊዜ ትመረቃችሁ፤ ይሄ ይደረግላችኋል” ያላችሁ ነገር አለ?
እስካሁን ምንም የተባልነው ነገር የለም፤  ቃል የተገባልንም ጉዳይ የለም፡፡ አንደኛ፤   እኛ እዛ እያለን ምንም ኔትወርክ ስላልነበረ ምን እንደሚባልና እንደሚደረግ የምንሰማው ነገር አልነበረም፡፡ ዋናው አሁን ከቤተሰባችን መገናኘታችን ነው። ቀጣዩን አብረን የምናየው ይሆናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ አንቺንም የምትሰሪበትንም ጋዜጣ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ ወላጆቻችን በተለይ እናቴ እንደዛ በምታለቅስብና በምትጨነቅበት ጊዜ ድምጽ ስለሆናችሁን እናመሰግናለን፡፡


Read 5442 times