Saturday, 07 August 2021 13:56

የዶላር ምንዛሬ በአምስት እጥፍ ማሻቀቡ ተገለፀ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(5 votes)


            የዶላር ዋጋ ከዚህ ቀደም በአገሪቱ ታይቶ በማይታወቅበት ሁኔታ በከፍተኛ መጠን ጨምሯል፡ በትላንትናው እለት በባንክ የአንድ ዶላር የምንዛሪ ዋጋ  44.ብር 93 ሣንቲም የነበረ ሲሆን በጥቁር ገበያ አንዱ ዶላር እስከ ከ69 ብር በሚደርስ ዋጋ ሲመነዘር ውሏል፡፡  
በከተማው  መደበኛ ባልሆነው የውጭ ምንዛሬ መስመር በሕገወጥ መንዛሪዎች የሚመራው ጥቁር ገበያ ባለፉት ጥቂት ቀናት ከዚህ ቀደም በአገሪቱ ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል፡፡
የጥቁር ገበያው የዶላር ምንዛሪ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ የሄደ ሲሆን በተለይም  በትግራይ ክልል ከተጀመረው ህግ የማስከበር ሂደት ጋር በተያያዘ ጭማሪው በከፍተኛ መጠን በመናር ካለፈው ሳምንት ጀምሮ አንድ ዶላር  ከ69 ብር እስከ 71 ብር  በመመንዘር ላይ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡
የአገሪቱ የዓመታት  አንገብጋቢ ችግር ሆኖ የዘለቀው የውጭ ምንዛሪ እጥረት  በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ በማሳረፉ የኑሮ ውድነቱን ያባባሰው ሲሆን በተጨማሪም በርካታ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው እንዳያመርቱ የዶላር ምንዛሪ ዋጋ በትግራይ ክልል ከተቀሰቀሰው ጦርነት ወዲህ በአገሪቱ እስካሁን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በከፍተኛ መጠን ማሻቀቡ የውጭ ምንዛሪ ዋጋውን የማናሩ ተግባር በህውአት ታጣቂዎች እና ደጋፊዎቻቸው በኩል ሊደረግ የሚችል የአገሪቱን ኢኮኖሚ የማዳከሙ ጦርነት አንዱ አካል ሊሆን እንደሚችል የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት  በጥቁር ገበያውና  በመደበኛው የባንክ  ገበያ  መካከል ያለው ልዩነት ከ25 ብር በላይ መሆኑ አብዛኛው ሰው የጥቁር ገበያ ምንዛሪውን እንዲመርጥ እያደረገው መሆኑን ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ።  በመደበኛው የባንክ ምንዛሪ ገበያው ላይም ቢሆን ቀላል የማይባል ማሻቀብ ታይቶበታል። ከሰባት ወራት በፊት ከ40 ብር ያልተሻገረው የመደበኛው ገበያ ምንዛሪ፤ አሁን የአምስት ብር ጭማሪ አሳይቷል።  በ13 ዓመታት ውስጥ ደግሞ የአምስት እጥፍ ጭማሪ ማሳየቱ ታውቋል። ዶላር እንደ ማንኛውም የሚገዛና የሚለወጥ ሸቀጥ ቢታይ፤ የዶላር ተመንም እንደ ማንኛውም ሸቀጥ በገበያ ዋጋ የሚተመን ይሆን እንደነበር የሚገልጹት  የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎቹ፤ የዶላር በገበያው ውስጥ እንደ ልብ አለመገኘቱ ዋጋውን በእጅጉ ሊያንረው እንደሚችል ገልጸዋል፡፡  መሰረታዊ በሆነው የምጣኔ ሃብት እሳቤ መሰረት፤ ፍላጎትና አቅርቦት በማይመጣጠኑበት ወቅት እንደ ማንኛውም ሸቀጥ መናር ሊፈጠር የሚችል ሲሆን፤ የዶላር እጥረት በገበያው ውስጥ ካጋጠመ የዶላር ዋጋ ሊንር እንደሚችልም ያስረዳሉ።
ትሬዲንግ ኢኮኖሚክስ ከተሰኘ ድረ-ገጽ የተገኘ መረጃን ዋቢ አድርጎ ቢቢሲ እንደዘገበው ባለፉት 10 ዓመታት በባንኮች የዶላር ዋጋ በ28 ብር ገዳማ ጭማሪ አሳይቷል።  በ2003 ዓ.ም ላይ በባንክ አንድ ዶላር በ16  ብር ይመነዘር ነበር።
በኢትዮጵያ የዶላር ምንዛሪ ዋጋ መናር አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ መሆኑን የጠቆመው የቢቢሲ ዘገባ፤ ትንበያዎች እንደሚያሳዩት እ.ኤ.አ በ2022 መደበኛው የባንክ የዶላር  ምንዛሪ ወደ 47̂ ነጥብ 7 ብር እንደሚደርስና፣  በ2023፤ ወደ 54 ነጥብ 1 ብር ሊያሻቅብ እንደሚችል ጠቁሟል።


Read 13026 times