Tuesday, 03 August 2021 17:11

በየዓመቱ የሚደገም ...

Written by  እሱባለው አማረ የሻነው
Rate this item
(0 votes)

 መክፈቻ፡-
ቻርለስ ዲከንስ (ነፍስ ይማር!) “A Tale of Two Cities” የተባለውን ዝነኛ መጻሕፉን፣ በዚህ ዝነኛ አንቀፅ ይጀምረዋል (ይከፍተዋል)፡፡
“It was the best of times, it was the worst of times, it was the age of wisdom, it was the age of foolishness, it was the epoch of belief, it was the epoch of incredulity, it was the season of Light, it was the season of Darkness, it was the spring of hope, it was the winter of despair, we had everything before us, we had nothing before us . . .”
በምድር ቆይታዬ ከዚህ አንቀፅ በተሻለ የሰው ልጅን ሕይወት የሚወክል የቃል ስብስብ አላየሁም፡፡ የሕይወት ታሪክህ የትም መቼም ቢፈጭ፣ ዱቄቱ ከዚህ አንቀፅ የተለየ አይሆንም፡፡
ሕይወትህ በዚህ የመክፈቻ አንቀፅ ይከፈታል፣ በዚህ የመክፈቻ አንቀፅ ይጠረቀማል፡፡
መጠርቀሚያ፡-
ሌቭ ኒኮላየቪች ቶልስቶይ (ነፍስ ይማር!) “What Men Live By and Other Tales” በሚል ርዕስ ባሳተመው ክፍለ-ዘመን-ጠገብ የአጫጭር ታሪኮች ስብስብ ውስጥ “Three Questions” የተሰኘ ታሪክ ተካትቷል፡፡ የዚህ ታሪክ የመዝጊያ (የመጠርቀሚያ) አንቀፅ፣ የሕይወትህን የመሀል መልክ ያሳይሃል፡፡ የሕይወትህ የመሀል መልክ ይህ ነው፡-
“… There is only one important time and is Now. The present moment is the only time over which we have dominion. The most important person is always the person with whom you are, who is right before you, for who knows if you will have dealings with any other person in the future. The most important pursuit is making that person, the one standing at you side, happy, for that alone is the pursuit of life.”
ሕይወት በዲከንስና በቶልስቶይ ሜዳ ላይ ያለች ኳስ ናት፡፡ (ለአንዳንዱ የጨርቅ፣ ለአንዳንዱ የወርቅ ኳስ!) ሕይወታውያን ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ሕግና እረፍት አልባ የጽሞና ጨዋታ፡፡ አንዳንዶች ጽሞናውን ሰብረው ይጠይቃሉ፡፡ ለምሳሌ መንግሥቱ ለማ (ነፍስ ይማር!)
“ምንድነው ሰበቡ…
ለምንድነው አልኩኝ፤ ለምን ምክንያት፤
ይህ ዓለም መኖሩ አዱኛ ሕይወት፤
ህጻን መወለዱ አርጅቶ ሊሞት፤
ለምንድነው አልኩኝ
ለምን ምክንያት፡፡”
ደግነቱ!.... ደግነቱ!.... በዚህ ሜዳ ግብ የሚያስቆጥርም ሆነ የሚቆጠርበት የለም፡፡ በቃ!... በቃ!... ተጫውቶ… ተጫውቶ…
ተጫውቶ… ተዝለፍልፎ መውደቅ፡፡
ዛሬ ልደቴ ነው (ነፍስ ይማር!)

Read 1943 times