Tuesday, 03 August 2021 17:07

“እኛ መንግስት ነን” አያዋጣም!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

 በጥር 1982 ዓ.ም በኩታ በርና በሐይቅ ግንባር ጦርነት እየተካሄደ ነበር፡፡ የሕወኃት/ ኢሕአዴግ ጦር ሐይቅ መስጊድ ሚናራ ላይ ዶሽቃ ጠምዶ፣ በጦሩ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ መንግስት በሶስተኛ ቀኑ ሚናራው እንዲመታ ፈቀደ፡፡ የሕወኃት/ኢሕአዴግ ጦር ወደ ኋላው ለመመለስ ተገደደ፡፡ ጦርነቱ ካበቃ በኋላ እኔና የስራ ባልደረባዬ ፎቶግራፍ አንሽው ጌቱ  (ነፍሱን ይማረውና)፤ በወያኔ ተኩስ በአካባቢው የደረሰውን ጉዳት ለማየት  ከቦታ ቦታ መዘዋወር ጀመርን፡፡ ተቃጥሎ ሙሉ ለሙሉ አመድ ከሆነ አንድ ቤት ደረስን፡፡ በእድሜ ጠና ያሉ አንድ ሴት ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ያለቅሳሉ፡፡ ቤታቸው እንደተቃጠለባቸው፣ የነበረቻቸው አንድ ላም እንደተገደለችና ከዚያን እለት ጀምሮ መውደቂያ እንዳጡ እያለቀሱ ነገሩን፡፡ ጦርነትን ሳስብ ሁሌም ወደ አዕምሮዬ የሚመጡት እኒህ ሴት ናቸው፡፡ በግንባር እየተፋለሙ ከሚገኙ ወገኖች እኩል ዛሬም በጦርነቱ ሳቢያ ለተለያዩ ችግሮች ለሚጋለጡቱ ወገኖች ልቤ ይደማል፡፡
ወደ ጦር ግንባር ከመንቀሳቀሳችን በፊት በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር የነበሩት አቶ አብዱል አዚዝ ሪፖርት ማድረግ ያለብንንና የሌለብንን ጉዳይ በመግለጽ፣ መመሪያ ሰጥተውን ነበር፡፡ በዚያ መመሪያቸው ውስጥ “የምንዋጋው ከራሳችን ወገኖች ጋር ነው፡፡ ይህን ያህል ሰው ተገደለ ብላችሁ እንዳትጽፉ” የሚል ማስጠንቀቂያ እንደነበረው አስታውሳለሁ፡፡ “እነሱ  የገደሉትንና የማረኩትን ሁሉ በዝርዝር እየተናገሩ ናቸው፡፡ ለምንድን ነው እኛ የማንገልጸው?" የሚል ጥያቄ አቅርቤላቸው ነበር፡፡ የእሳቸው መልስ፤ "እኛ መንግስት ነን” የሚል ነበር፡፡
 እኔ ግን ከጦሩ የማገኛቸውን መረጃዎች በመያዝ፣ የሞተ የተማረከና የቆሰለውን የህወሓት ወታደር ቁጥር ከመግለጽ አልቦዘንኩም ነበር፡፡ አዘጋጆቹ ከአንድ ቀን በስተቀር ቁጥሩን እያስቀሩ ሲያትሙ እንደነበርም አስታውሳለሁ፡፡ “እኛ መንግስት ነን” የሚለው መርህ ዛሬም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ዘመን እየሰራ ይመስለኛል፡፡ በአሸባሪነት የተፈረጀው ሕወኃት፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አባል ሆነው በየወረዳውና በየዞኑ ሲያገለግሉ የነበሩ ከሰማኒያ ያላነሱ ሰዎችን ሲገድል፣ መንግስት ለትግራይ ሕዝብም ሆነ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰማዕትነታቸውን በይፋ ከመግለጽ የተቆጠበው “ህወኃት ወንበዴ፣ እሱ መንግስት” በመሆኑ ይመስለኛል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ  ራሳቸው  በጥገና ሥራ ላይ የነበሩ ሰላሳ ስድስት ቴክኒሽያኖች በህወኃት ቡድን  መገደላቸውን የነገሩን አስበውትና የመረጃውን አስፈላጊነት አምነውበት ሳይሆን፣ ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ ለመስጠት ማስረጃ ማቅረብ ግድ ስለሆነባቸው መሆኑን እገምታለሁ፡፡   
ደርግ የሰራዊቱን ድልና ተጋድሎ በሚደብቅበት በዚያ ዘመን፣ ጦሩም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ በመረጃ ምንጭነት የሚጠቀሙት የአሜሪካንና የጀርመን ድምፅ ራዲዮ ጣቢያዎችን ነበር፡፡ ጣቢያዎቹ በየቀኑ የሚዘግቡት ደግሞ ከትህነግና ሻቢያ የሚያገኙትን መረጃ ነበር፡፡ ያልተያዘ አካባቢ ተያዘ፣ ያልተማረከ የጦር አዛዥ ተማረከ ብለው ሲዋሹ፣ ከመንግስት ወገን  "ቅጥፈት ነው" ብሎ የሚያስተባብል አልነበረም፡፡
አሁን ያሉት የመረጃ ምንጮች የአሜሪካና የጀርመን ድምጽ ራዲዮ ጣቢያዎች ብቻ አይደሉም፡፡ በሀገራችን ከአምስት ደርዘን በላይ የሚሆኑ የራዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አሉ፡፡ በዚያ ላይ ከአንድ የቴሌቪዥን ወይም የሬዲዮ ጣቢያ ያልተናነሰ መረጃ የማሰራጨት አቅም ያላቸው በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ማህበራዊ ሚዲያዎች፡- ፌስቡክ፣ ዩቲዩብ፣ ቴሌግራም፣ ትዊተር -- ወዘተ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እያንዳንዳቸውም በአማካይ ከ50 ሺ እስከ 100 ሺ የሚገመቱ ተከታዮች ያሏቸው ናቸው፡፡ ሆኖም መንግስት ግን እኒህን የመገናኛ መንገዶች ሲጠቀምባቸው አይታይም፡፡
መንግስት የሚወቀሰውና የሚተቸው መረጃ ባለመስጠቱ ብቻ ሳይሆን መረጃ ባለመቀበሉም  ጭምር ነው፡፡  በዶክተር ሙሉ ነጋ ይመራ የነበረው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ "የሕወኃትን መወገድ የሚፈልጉትን ሃላፊዎች እያገለለ፣ ለቡድኑ ዳግም ማንሰራራት የሚሰሩትን እያቀፈ ነው" የሚል ተደጋጋሚ ስሞታ ቢደርሰውም ምላሽ ያልሰጠው የፌደራል መንግስቱ፤ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ባለስልጣናት ወደ አዲስ አበባ በመጡ ጊዜ፣ ከፊሎቹ መቀሌ ቀርተው ጉዱን በአይኑ በብሌኑ እንዲያይ አስገድደውታል፡፡  
አሁንም መንግስት ለመረጃዎች ጆሮውን መዝጋቱን የሚያረጋግጥልን ደግሞ ከአንድ ወር በፊት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ከአቶ ጌታቸው ረዳ ጎን ቆሞ የታየው፣ በኢትዮጵያ የአለም ምግብ ድርጅት ተወካይ ሚስተር ቶማስ ብሪየን ቶምስን፣ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ፈቃዱን ነጥቆ ከአገር ማባረሩን ስናይ ነው፡፡ እዚህ ላይ መነሳት ያለባቸው ጥቂት ጥያቄዎች አሉ፡፡ ለአሸባሪው ቡድን በልዩ ልዩ መንገዶች ድጋፍ እያደረጉ የሚገኙ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማትንና ሠራተኞቻቸውን ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ በማጋለጥ ረገድ በመንግስት በኩል ምን እየተሰራ ነው? በፍጥነት ሕጋዊ እርምጃስ የማይወሰደው ለምንድን ነው? ማባበሉ እስከ መቼ ይቀጥላል?
 ወደ ጦር ግንባር ለመግባትም ሆነ በጦር ሜዳ አሸንፎ ለመውጣት በሁለቱም ጊዜ የመንፈስ ዝግጁነት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንጻር ሠራዊቱን ከጠላት ፕሮፓጋንዳ መጠበቅ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ መንግስት በዚህ በኩል ያለበትን ድክመት ፈጥኖ ማረም አለበት፡፡ “ኢትዮጵያን ለማፍረስ እስከ እንጦሮጦስ ድረስ እንወርዳለን” የሚሉት እነ ጌታቸው ረዳ፤ ትግራይን እራሷን እያፈረሷት እንደሚገኙ መንግስት ለትግራይ ሕዝብ በቋንቋው ደጋግሞ ሊነግረው ይገባል። መብራትና ስልክ በሌሉባት፣ ከትግራይ ሬዲዮና ትግራይ ቴሌቪዝን በስተቀር ሌሎች ጣቢያዎች በማይደመጥባት ትግራይ፤ ከአዲስ አበባ በሬዲዮና ቴሌቪዥን ቅስቀሳ ለውጥ አመጣለሁ ብሎ ማሰብ ከንቱ ድካም እንደሆነ መታወቅ ይገባዋል፡፡  
በአፋጣኝ ሌላ አማራጭ መፈለግ አለበት። የትግራይን ሕዝብ አሸባሪው ሕወኃት፣ አንድ ለአምስት አደራጅቶ የፕሮፓጋንዳው ሰለባ አድርጎታል፡፡ ይህን ህዝብ በተናጥል ማግኘት የሚያስችል ስልት በመዘርጋት መታደግ ያስፈልጋል፡፡
በፕሮፓጋንዳ አሸናፊ መሆን በጦር ሜዳ አሸናፊ ለመሆን ያለውን ቦታ ያህል፣ በጦር ሜዳ ማሸነፍም ለፕሮፓጋንዳ  የበላይነት በእጅጉ እንደሚጠቅም ይታመናል፡፡ እንደ ደርግ “እኛ መንግስት ነን” የሚለው መርህ መንግስትን መልሶ ዋጋ ሊያስከፍለው እንደሚችል ሊታወቅ ይገባል፡፡
መንግስት በችግሩ አያያዝም ሆነ በችግሩ አፈታት ላይ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡ ለአሸባሪው ሕወኃት በሚመጥን መንገድ መራመድ የግድ እንጂ ምርጫ አይደለም፡፡ እደግመዋለሁ፡- "እኛ መንግስት ነን" ብሎ ነገር አያዋጣም፡፡




Read 2384 times