Tuesday, 03 August 2021 16:55

የኤርትራውያን ስደተኞች መከራ በትግራይ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

ኢትዮጵያን መጠጊያ ያደረጉ ኤርትራውያን ስደተኞች ቁጥር ከ150 ሺ በላይ እንደሚሆን የዓለም ስደተኞች ድርጅት መረጃ ያመለክታል፡፡ ከእነዚህ ስደተኞች መካከል ከ100 ሺ ያላነሱት በትግራይ ጦርነት ከመፈጠሩ በፊት በክልሉ በሚገኙ አራት የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ተመዝግበው አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገላቸው ይኖሩ እንደነበረም የድርጅቱ ሪፖርት ያትታል፡፡
በአሸባሪነት በተፈረጀው የህወኃት ቡድንና በፌደራል መንግስት መካከል ጦርነት ከመከሰቱ ከ8 ወራት በፊት ህፃፅ፣ ሽመልባ፣ ማይአይኒ፣ አዲሃሩሽ በተባሉ ካምፖች ውስጥ  ከ100 ሺህ በላይ ስደተኞች ይኖሩ እንደነበር ያመለከተው  ሪፖርቱ፤ የጦርነቱን መቀስቀስ ተከትሎ በተለይ ህጻጽ እና ሽመልባ ውስጥ የነበሩ ስደተኞች አብዛኞቹ የት እንደደረሱ እንደማይታወቅ፣ ጥቂቶቹ ደግሞ የኤርትራ ወታደሮችን ጥቃት ሽሽት ወደ ተቀሩት ማይአይኒ  እና አዲሃሩሽ ካምፖች መቀላቀላቸውን ጠቁሟል፡፡
የኤርትራ ወታደሮች በጦርነቱ ተሳታፊ በነበሩባቸው ጊዜያትም ስደተኞች ካምፕ ውስጥ እየገቡ የሚፈልጓቸው ሰዎች ላይ ጥቃት ይፈጽሙ እንደነበር  የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ ሪፖርት ይገልጻል፡፡ በተለይ ሴቶች የመደፈር  ወንዶችም ቢሆኑ ድብደባና የተለያዩ አካላዊ ጥቃቶች ይፈፅምባቸው እንደነበር በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡
በተለይ ወደ ኤርትራ ድንበር ተጠግተው የተቋቋሙት ሽመልባ እና ህጻፅ የስደተኛ ካምፖች ውስጥ ይገኙ የነበሩ ስደተኞች ግድያም እንደተፈፀመባቸው፣ ጥቂት የማይባሉትም ታፍነው ወደ ኤርትራ መወሰዳቸውን ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
ነገር ግን ይሄን የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ ውንጀላ የኤርትራ መንግስትም ሆነ የኢትዮጵያ መንግስት አይቀበሉትም፡፡ የአሜሪካ መንግስት የስደተኞቹን ሁኔታ አስመልክቶ ከሰሞኑ ባወጣው ሪፖርት፤ በእርግጥም በትግራይ በሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ላይ የከፋ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ስለመፈፀሙ በቂ ማረጋገጫ አግኝቻለሁ ብሏል፡፡
“በጥቃቱም በተለይ የኤርትራ ወታደሮች ጦርነቱ የተጀመረ ሰሞን ሴቶችን ደፍረዋል፤ ወንዶችንም ገድለዋል፤ ድብደባና የአፈና  ተግባር ፈጽመዋል” ይላል፤ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሪፖርት፡፡
የኤርትራ ወታደሮች ህፃፅ የስደተኞች ጣቢያን ማጥቃት በጀመሩበት በጥር 2013 ዓ.ም 3ሺህ ያህል በካምፑ ውስጥ የነበሩ ስደተኞች እግሬ አውጭኝ ብለው በእግራቸው በመጓዝ ወደ ማይአይኒ ጣቢያ መግባታቸውን የሚያትተው ሪፖርቱ፤ በማይአይኒ ካምፕም ውስጥ ቢሆን ለስደተኞቹ መከራው አልቀረላቸውም ይላል፡፡
በአሁኑ ወቅት ህፃፅ እና ሽመልባ የተሰኙት የስደተኞች ካምፖች በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ፤ በውስጣቸው ምን  እንዳለ፣ በስደተኞች ጉዳይ የሚሰሩ አለማቀፍ ተቋማት ምንም አይነት መረጃ እንደሌላቸው ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡
በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በኤርትራ ሠራዊት እንዲሁም በአሸባሪነት በተፈረጀው ህወኃት መካከል ለ8 ወራት የተካሄደው ደም አፋሳሽ ግጭት ጋብ ብሎ፣ የፌደራል መንግስት የተናጥል ተኩስ አቁም እርምጃ በመውሰድ መከላከያ ሠራዊቱን ከትግራይ ማስወጣቱን ተከትሎ፣ ህወኃት ትግራይን ከተቆጣጠረ በኋላም  ኤርትራውያን ስደተኞች የከፋ ጥቃት እያጋጠማቸው መሆኑን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኤጀንሲ ሪፖርት ያመለክታል፡፡
ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በአጠቃላይ ከ100 ሺህ ይልቅ የነበረው የኤርትራውያን ስደተኞች ቁጥር ተመናምኖ አሁን ላይ በሁለት ካምፕ ብቻ ኑሮአቸውን ያደረጉ 24 ሺህ ያህል ስደተኞች ተጠልለው እንደሚገኙ ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ ቀሪዎች 76 ሺህ ያህል ስደተኞች ባለፉት ስምንት ወራት ወዴት እንደገቡ እንኳ በውል አይታወቅም፡፡
በአሸባሪነት በተፈረጀው ህወኃት እጅ ያሉት 24 ሺህ ያህል ኤርትራውያን ስደተኞች አሁንም ከቀድሞ የባሰ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እየተፈፀመባቸው ነው ብሏል-የመንግስታቱ ድርጅት፡፡
በማይአይኒ እና አዲሃሩሽ ካምፖች ውስጥ የሚገኙ እነዚህ ስደተኞች #ከኤርትራ ወታደሮች ጋር አብራችኋል; በሚል ግድያን ጨምሮ የተለያዩ ኢ-ሰብአዊ ተግባራት በህወኃት ሃይሎች እየተፈፀመባቸው መሆኑን የስደተኞች ጉዳይ ኤጀንሲ ማክሰኞ ዕለት ያወጣው ሪፖርት ያመለክታል፡፡ ለስደተኞቹ እርዳታና ድጋፍ የሚቀርብባቸውን መንገዶችና አማራጮች ህወኃት ሆን ብሎ መዝጋቱንና ስደተኞቹን በረሃብ ሊፈጃቸው እንዳሰበም በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡
በእርግጥ ህወኃት ለኤርትራውያን ስደተኞች ቀርቶ እዋጋለታለሁ ለሚለው የትግራይ ህዝብም እርዳታ የሚቀርብባቸውን መንገዶች መዝጋቱንና እርዳታ ማቅረብ አለመቻሉን የኢትዮጵያ መንግስት ሰሞኑን ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ 170 ያህል ከባድ ተሽከርካሪዎች መተላለፊያ አጥተው ለቀናት እርዳታውን እንደጫኑ በአፋር መስመር በየመንገዱ ቆመው እንደሚገኙ የትራንስፖርት ሚኒስቴር መግለጹ ይታወቃል፡፡
በዚህ እኩይ ተግባር 1.2 ሚሊዮን ያህል የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ለረሃብ መጋለጣቸውን የጠቆመው  የመንግስታቱ ድርጅት፤ ህወኃት የዘጋውን መንገድ ከፍቶ እርዳታው ለተጎጂዎቹ ሊደርስ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡ በረሃብ እንዲያልቁ በህወኃት የተፈረደባቸው ኤርትራውያን ስደተኞች ጉዳይም በእጅጉ እንደሚያሳስባቸው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤትና የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ኤጀንሲ ከሰሞኑ ባወጡት መግለጫ ጠቁመዋል፡፡
በጦርነት ቀጠና ውስጥ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች መከራቸው የተራዘመው በትግራይ ክልል ብቻ አይደለም፤ በቅርቡ ህወኃት የግጭት ቀጠና ባደረጋቸው የአፋር አካባቢዎችም ከ55 ሺህ በላይ ኤርትራውያን ስደተኞች ከበባ ውስጥ መውደቃቸው ተጠቁሟል፡፡ እነዚህ የከበባ ወጥመድ ውስጥ ገብተዋል የተባሉ ስደተኞች፣ ለቀናት እንኳ የሚያቆይ የምግብ ክምችት እንደሌላቸው ነው የተገለጸው፡፡
ስደተኞቹ በህወኃት ከበባ ምክንያት የንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ የምግብና የህክምና አቅርቦት ሙሉ ለሙሉ ተቋርጦባቸው፤ በከፋ የረሃብ አደጋ ላይ መውደቃቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ኤጀንሲ በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
አካባቢውን በጦርነት እያመሱ የሚገኙት የህወኃት ሃይሎች ተደራራቢ የጦር ወንጀሎችን እየፈፀሙ እንደሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ለተለያዩ አለማቀፍ ተቋማት እያመለከተ ሲሆን፤ ስድስት ኤርትራውያን ስደተኞች በህወኃት መገደላቸውንም  አስታውቋል።
የአሜሪካ መንግስትም ሆነ የተባበሩት መንግስታት በተለይ ከ1.7 ሚሊዮን በላይ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ለረሃብ አደጋ መጋለጣቸ፣ ከ75 ሺህ ያላነሱ ኤርትራውያን ስደተኞች በጦርነት ቀጠናው ለከፋ ስቃይ መዳረጋቸው በእጅጉ እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል፡፡


Read 1287 times