Monday, 02 August 2021 20:41

የ‘ምስር’ እና የ‘ቪትዝ’ ነገር!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ከብርዱ የጭጋጉ! “በጥቅምት አንድ አጥንት” በሚባልበት ወራት እንዲህ እንደ ሰሞኑ ይበርዳል እንዴ! ያን ጊዜ ቢያንስ በተረቷ ራሳችንን እናጽናና ነበር፡፡ “ገንዘብ ቢኖር ኖሮማ፣ ይሄኔ ነበር በጥቅምት አንድ አጥንት ማለት!”  ቢያንስ ‘አጥንት’ የሚለውን ቃል መጥራቱ እኮ ራቅ ያለ ቢሆንም ተስፋ ነገር አይጠፋውም። ከሐምሌና ከብርድ ጋር የተያያዘ፣ ደግሞም በዋነኛነት  ‘አጥንት’ የሚለው ቃል ያለበት ተረት ናፍቆት ሳይኖርብን አይቀርም፡፡ (“የምስር አምሮት አገር ጥሎ ሊያስወጣን ደርሷል፤ አንተ ስለ አጥንት ታወራለህ!” የምትሉ ወዳጆቼ፣ ህመማችሁ ህመሜ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ‘እገልጣለሁ!’)
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች እኮ ‘የሥጋ ብድር’ የሚሉት ነገር አለ ተብሎ የሚወራበት ወቅት ነበር፡፡
የምር ግን አሁን ባለንበት ጊዜ እንዲህ አይነት ‘ብድር’ የሚሰጥ መሥሪያ ቤት  ቢኖር ምን እንል እንደነበር ግምት ቢጤ ለመስጠት ከተፈቀደልን... “ይሄኔ ሥራ አሥኪያጁ ከሉካንዳ ቤቶች ጋር በፐርሰንት ኮሚሽን ሊበላ ተደራድሮ ይሆናል፡፡” ልክ ነዋ…በቃ በዲጂታል ዘመን የሥጋ ብድር ብሎ ነገር ሲመጣ የሆነ ‘ነገር’ ቢኖረው  ነዋ!
እኔ ምለው… የተመጣጠነ ምግብ የሚባለውን ነገር ለምን ‘አገርኛ’ አድርገን ‘አናስተካክለውም!’ (‘ፖለቲካ ነፍሱን የጠራችው’ አይነት ፖለቲከኛ ምን ሊል ይችላል መሰላችሁ…“መጀመሪያም የተመጣጠነ ምግብ ብለው ሲያስተምሩን የነበረው የኢምፔሪያሊስቶች ሴራ ነው!” አሪፍ አይደል! የምር ግን፣ እንግዲህ ጨዋታም አይደል... “ኮሚኒዝም ማለት ሁሉም ንብረት የሁሉ ስለሆነ መንገድ ላይ የቆመውን ማንኛውንም መኪና አስነስቶ መሄድ ይቻላል ማለት ነው፣” ለማለት ወደ ኋላ እንደማይል አይነት ‘ትኩስ’ ፖለቲከኛ የሚያዝናና አለ እንዴ! ጥያቄ አለን... የትኩስ ፖለቲከኞችን ቁጥር የሚጨምር ፕሮጀክት ይነደፍልንማ!)
እናላችሁ ዘንድሮ… “የመጣ ይምጣ፣ ከፈለጉ ከስልጣኔ ያንሱኝ!” ብሎ የሥጋ ብድር የሚፈቅድ ሥራ አስኪያጅ ቢኖር…አለ አይደል…የጥራጥሬ ነጋዴዎች እንትን በሚባለው ፋይቭ ስታር ሆቴል ተሰብስበው የአቋም መግለጫ ምናምን ማለታቸው አይቀርም ነበር! “የእንትን መሥሪያ ቤት ሥራ አስኪያጅ ለሠራተኞቹ የሥጋ ብድር እየሠጠ፣ ሰዉ ጥራጥሬ ላይ ጀርባውን እንዲያዞር እየቀሰቀሰ ስለሆነ የሚመለከተው አካል እርምጃ ይውሰድልን! በጥራጥሬ እህሎች ላይ የሚደረገውን ሴራ አጥብቀን እናወግዛለን!“ የሚል የአቋም መግለጫ ባያወጡ ነው!
የምር... አሁን ያለንበት ጊዜ እኮ... የጀርባ ምናምን የሆኑብንን ፈረንጆች ለመጥቀስ ያህል... ‘ዊይርድ’ ብሎ ጭጭ ነው። ስንታችን ነን...“ሠራተኞቹ ተመጣጣኝ ምግብ እንዲያገኙ ለማድረግ አስቦ ከመመሪያ ውጪ ያደረገው ነው! እንዴት አይነት የተባረከ ሰው መሰላችሁ!” ብለን የምናመሰግነው! የ‘ኮንስፒሬሲ ቲዬሪ’ ዘመን ነዋ!  ከሀሉም ጉዳይ ጀርባ የሆነ ‘የተደበቀ ነገር መኖር አለበታ!” ነገር  የነበረበት ጊዜ ነበር! “የሥጋው ቢቀር የዘይትና የምስር ብድር ይፈቀድልን!” ብሎ የሚጠይቅ ሰው ዘመኑ ገብቶታል ማለት ነው! ቂ...ቂ..ቂ...
ስሙኝማ...ኸረ ይቺ ብራችን ምን ይሻላታል! ኪሎ ምስር የኪሎ ሥጋን ዋጋ ነጠቀች እኮ! ቪትዝ! ቪትዝ ከአቅሟ ሰባትና ስምንት መቶ ሺህ ትግባ! ብንገረምም አይገርምም፡፡ (ቀሺም ግጥም መሰለች አይደል!) እነ እንትና እኮ…አለ አይደል… ለእንትናዬዎቻቸው በስጦታ መልክ ሳይሆን “የኮንትራት ታክሲ ሲበዛ ይደብርሻል ብዬ ነው ቪትዟን የገዛሁልሽ፣” ብለው ‘ወርወር’ የሚያደርጓት ነበረች እኮ፡፡ (ቂ…ቂ…ቂ…) ሌላው አንዲት ጫማ ለመስጠት ሦስት ዓመት ከምናምን ወር ይቆጥባል፣ እነ እንትና ቪትዟን እኮ ልክ…አለ አይደል…ኋላ ኪሳቸው የረሷትን ብር ወጣ አድርገው ለመኪና ሻጩ “ለዚች ነው፣ ያውልህ!” ብለው የሚወረውሩለት ነበር የሚመስለው። እናማ… ሊገዛላችሁ ቃል ተገብቶላችሁ የነበራችሁ… “ቪትዝን ያላችሁ እስቲ እንያችሁ!” ማለት አሁን ነው፡፡
“ስማ… ለእንትና  መኪና ገዛህላት ሲሉ ሰምቼ…”
“መኪና ገዛላት አሉ እንዴ! እንደኛ ሰው የሚያስቀኝ የለም እኮ!”
“ፈጥረው ነው እንዴ የሚያወሩት?”
“መኪና እኮ አይደለም፣ ቪትዝ ነው የገዛሁላት!”
“ሰዉ ግን በቃ ከመሬት ተነስቶ ነው የሚተረተረው! መኪና ገዛላት ነው እኮ ያሉኝ!”  (ስለ ቪትዝ እንዲህ የሚባልበት ዘመን ሳያልፍ አልቀረም ለማለት ያህል ነው። ቂ…ቂ…ቂ…)
ስሙኝማ…አንድ ነገር ትዝ አለኝማ! ሽክ ብላችሁ እናንተ “በዝነጣ ውድድር ቢኖር ከአፍሪካ አንደኛ፣ ከዓለም ሁለተኛ እሆን ነበር፣” እያላችሁ በውሀ ልክ ስትራመዱ፣ ከሳምንት በፊት እንዲሁ መንገድ ላይ ልባችሁን ሲያወልቃችሁ የነበረ ሰው ታገኛችላሁ። ገና ሰላም ልትሉት እያኮበኮባችሁ ሳለ ምን ቢላችሁ ጥሩ ነው…
“አንተ! ምን ሆነሃል?”
“ማለት?”
“ማለትማ ደህና አይደለህም እንዴ!” (ሰውየው ምን ነክቶታል!) “ፊትህ ሁሉ ጭፍግግ ብሏል፡፡”
“ኸረ እንደው የዛሬው ሰንበት…” ማለት ትጀምሩና ትተዉታላችሁ፡፡ ቆይ ከዚህ በላይ ምን እንድትሆኑለት ነው! ጠዋት ‘ጢማችሁን’ ስትላጩ “እንዲህ እኮ ሀንድሰም መሆኔን አላውቅም ነበር፣” ስትሉ አርፍዳችሁ አጨፍግጎት ይረፍ!
የምር ግን... አለ አይደል...ከመሬት ተነስቶ...“ምን ሆነሃል?” ሲል… አለ አይደል… ዲፕሎማሲ፣ ‘አብሮ መኖር በዓለም ዙሪያ’ ምናምን የሚባለውን ነገር ትቶ ‘ምን ስሆን አየህ!’ ብሎ እጢውን ዱብ ቢያደርገውስ! (ወጣቶቹ ቢሆኑ ‘ቀንዱን ማለት ነው!’ ይሉ ነበር! ለ‘ጨዋነቴ’ ላይክ ግጩልኛ!)
ደግሞ አለላችሁ… ካልጠፋ ነገር ስለምትበሉትና ስለምትጠጡት “ይኮነስረኛል” የሚል አይነት፡፡
“ስማ አሁንም ቁርጥ ትበላለህ እንዴ?!” ብሎ ጥያቄ ምንድን ነው! መጀመሪያ ነገር ይህ ምን ጥያቄ ነው፣ ስለላ ነው እንጂ! (ቂ...ቂ...ቂ...) ሁለተኛ ነገር “አሁንም” የምትለዋ ቃል አገባብ ጤነኛ አይደለም፡፡ አሀ…“ቁርጥ ትበላለህ እንዴ!” ምናምን ማለት እየተቻለ፣ የ“አሁንም” ጣልቃ ገብነት  ልክ አይደለማ! ለነገሩ በኋላ ለ‘ጎሲፕ’ ምናምን ለማመቻቸት የገባች ሳትሆን አትቀርም፡፡
“አዎ እበላለሁ፡፡”
“አትለኝም!”
“እልሀለሁ፡፡ ቢያንስ በሳምንት አንዴ አንድ ኪሎ ሳልበላ አላልፍም፡፡” በይሉኝታ ይሞታል እንዴ!
ከዛማ…ያው መረጃ ‘ሼር’ ማድረግ ነው፡፡
“ስማ… አጅሬው እኮ አሁንም ቁርጥ ይበላል።”
“እስቲ ሙት በለኝ!” የተዘረጋውን መዳፍ ግጥም!
“እኛ ኪሎ ምስር መቶ ሀያ ብር ገብቶብናል፣ እሱ በየሳምንቱ የአምስት መቶ ብር ኪሎ ቁርጥ ይበላል!”
ከዛ ደግሞ እዛኛው ሰፈር ‘ሼሩ’ ይዳረስና ቅብብሎሹ ይቀጥላል!
“ስሙ እናንተ፣ እንትና ዊክኤንድ ላይ ኪሎ ጥሬ ሥጋውን ይከሸክሻል አሉ!”
“እኔ እኮ ሁልጊዜ እሱን ሰውዬ አላምነውም፣ ገንዘብ የሚሠራበት የሆነ ድብቅ ነገር አለው ስላችሁ እናንተ አታምኑም ነበር፡፡”
“በየሳምንቱ ቁርጥ! እውነታችሁን ነው?”
“እሱ ራሱ ነው የተናገረው አሉ፡፡”
“ያኔ እኛ በምንገዛለት ድራፍት አልነበር እንዴ ሆዱን የሚቆዝረው! (አዎ፣ ‘የሚቆዝረው፣’ የሚል ቃል ከዕለታት አንድ ቀን ነበር። ለፈረንጂኛው ‘ኦቨርዌይት’ አቻ ትርጉም ነገር፡፡) አሁን ሰው ሆነና…” እያለ ይቀጥላል። እንግዲህ ለዚህ ሁሉ መነሻ ያቺ “አሁንም” ተብላ የተሰነቀረች ነገር ነች፡፡
እናላችሁ... ምስርም እዛ ላይ፣ ቪትዝም እዛ ላይ ስለወጡ ወይ መሰላል ይሰጠንና እኛ እንውጣ፣ ወይ እነሱ ይወረዱ! እነሱስ... ከእውነተኛ ወዳጆቻቸው ሲለያዩ ‘ህቅ’ አይላቸውም!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1470 times