Saturday, 31 July 2021 00:00

ቢጂአይ ኢትዮጵያ ከ1500 በላይ ሰዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ድጋፍ አደረገ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 ቢጂአይ ኢትዮጵያ፤ በጉራጌ ዞን የጋሶሬ ቀፍ 1 እና 2 ከተማን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ የሚስችል ድጋፍ አደረገ፡፡
ድርጅቱ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ባለስልጣን ሆሳዕና ቅርንጫፍ ቢሮ የጋሶሬቀፍ 1 እና 2 ከተማ ነዋሪዎች ያለባቸውን የኤለክትሪክ ኃይል ችግር ለመቅረፍ የሚያስችልና ከ1500 በላይ አባውራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የሁለት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡
በወልቂጤ ከተማ በተካሄደው በዚሁ የድጋፍ አሰጣጥ ፕሮግራም ላይ  የተገኙት የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ እንዳለ ገ/መስቀል እንደተናገሩት፤ ድርጅቱ ማህበረሰቡ በተደጋጋሚ የሚያነሳውን የኤሌክተሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር ለመፍታት የሚያስችል ድጋፍ በማድረጉና አፋጣኝ ምላሽ በመስጠቱ  መመስገን ይገባዋል ብለዋል፡፡
የወልቂጤ ከተማ ፀጥታ ቢሮ ሀላፊው አቶ ክንፈ ሀብቴ በበኩላቸው፤ ሕብረተሰቡ ችግሮቹን ለመንግስት ቢያሳውቅም መንግስት ባለበት የአቅም ውስንነት  ምክንያት፣ ጥያቄው ምላሽ ሳያገኝ ቆይቷል። ቢጂአይ ኢትዮጵያ፤ ይህንን የህብረተሰቡን ተደጋጋሚ ጥያቄ ተቀብሎ ችግሩ እንዲፈታና ማህበረሰቡ የኤሌክተሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረጉ ከፍተኛ ደስታ ይሰማናል፡፡ በዚህ ድጋፍ በርካታ እናቶችና አባቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ በተለይም ልጆቻችን  ራሳቸውን ከወቅቱ ቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር፣ ውጤታማ ለመሆን እንዲችሉ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የቢጂአይ ኢትዮጵያ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ገብረስላሴ ስፍር በዚህ የድጋፍ አሠጣጥ ፕሮግራም ላይ እንደተናገሩት፤ ድርጅቱ ፋብሪካዎቹ በሚገኙባቸው አካባቢዎች ሁሉ  የነዋሪዎቹን ህይወት ለመለወጥና ለማሻሻል የሚቻለውን ሁሉ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው የጋሶሬ  ቀፍ 1 እና 2 ከተማ ነዋሪዎችን  የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል የትራንስፎርመር መግዣና ማስተከያ 2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል። ይህ ድጋፍ ድርጅቱ በተለያዩ አካባቢዎች እየተወጣ ያለው የማህበራዊ ኃላፊነት ተግባር እንዱ አካል እንደሆነም አመልክተዋል፡፡
በሆሳዕና ከተማ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ባለስልጣን ዳሬክተር አቶ ዘመነ ዳንኤል እንደተናገሩት ከወልቂጤ ከተማ በ50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የጋሶሬ ቀፍ 1 እና 2 ከተማ የመብራት ችግርን ለማስወገድ ባለስልጣን መ/ቤቱ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በመደገፍ አስፈላጊ የሆነውን ትራንስፎርመር ለመግዛትና ለማስተከል ብሎም ህብረተሰቡ የተመኘውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት እንዲችል ቢጂአይ ኢትዮጵያ ያደረገልን የ2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል ብለዋል፡፡ የትራንስፎርመሩ ግዢና ተከላ ስራ በአፋጣኝ ተጠናቆ ህብረተሰቡን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ቀን ከሌሊት እንሰራለን ሲሉም ቃል ገብተዋል፡፡

Read 1793 times