Monday, 02 August 2021 20:16

በXXXII ኦሎምፒያድ የኢትዮጵያውያን የኦሎምፒክ ገድል የመጀመርያው ምእራፍ ከ1956 እስከ 1980 እኤአ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 ፈረንሳዊው  ፒዬር ደኩበርቲን ባመነጩት ሃሳብ የመጀመርያው ኦሎምፒያድ በ1896 እኤአ ላይ በግሪኳ ከተማ አቴንስ ተጀመረ። በዚያን ወቅት ጣሊያን በቅኝ አገዛዝ ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር ጦርነት አውጃ በአድዋ ግንባር ላይ መራሩን ሽንፈት ቀመሰች፡፡ የአድዋ ድልም ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስተዋወቀና ለመላው የጥቁር ህዝብ  ተምሳሌት ለመሆን የበቃ የታሪክ ክስተት ነበር፡፡ አፍሪካ  በአብዛኛው በቅኝ ገዢዎች ስር ነበረች፡፡ አድዋ ለአፍሪካ የመጀመርያ የኦሎምፒክ ተሳትፎ ምንም አይነት ተጽእኖ ሊፈጥር ግን አልቻለም።  ድሉ ከተመዘገበ 37 ዓመታት በኋላም 9 የተለያዩ ኦሎምፒያዶች በተለያዩ የዓለም አገራት የተካሄዱ ቢሆንም  አፍሪካ ለመሳተፍ አልበቃችም፡፡ የኦሎምፒኩ ፈርቀዳጅ  ፒዬር ደኩበርቲን  በታላቁ የስፖርት መድረክ ሁሉንም  ሁሉንም አህጉራት ለማሳተፍ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ በተለይ  በሮም ተካሂዶ ለነበረው የዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ጠቅላላ ጉባኤ በቅኝ ገዢዎች ስር ለነበረችው የአፍሪካ ተሳትፎ በድጋሚ ሃሳብ ቢያቀርቡም ከአባል አገራት በቂ ድጋፍ ሊያገኝላቸው አልቻለም። በወቅቱ  የደኩበርቲንን ሃሳብ በመደገፍ በግብፅ አሌክሳንድሪያ የሚኖሩ ግሪካዊ ባለሃብት የኦሎምፒክ ስታድዬም ለማሰራት ቃል ገብተው ነበር፡፡ ይህን ተከትሎ ግብፅ በሚገነባው ስታድዬም ኦሎምፒክን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗን ብታሳውቅም አውሮፓውያን በመቃወማቸው ሳይሳካ ቀረ፡፡ ከግብፅ በኋላም በፈረንሳይ ቅኝ  ስር የነበረችው አልጄርያ ኦሎምፒክን እንድታስተናግድ ሃሳብ ቀርቦ ሰሚ አላገኘም፡፡  አፍሪካ የኦሎምፒክ መስተንግዶ እንድታደርግና እንድትሳተፍ ከተደረጉት ሁለቱ ሙከራዎች በኋላ ቀጣዩ ጥረት የኢትዮጵያ ሆነ፡፡ በ1924 እኤአ ላይ ልዑል አልጋ ወራሽ የነበሩት ተፈሪ መኮንን በአውሮፓ የስድስት ወራት ጉብኝት ነበራቸው፡፡ በ8ኛው ኦሎምፒያድ አዘጋጅ የፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ በፒየር ደኩበርቲን ግብዣ በእንግድነት ተጋብዘው ነበር፡፡ ከአውሮፓ ጉብኝታቸው ሲመለሱ የመጀመርያው ተግባራቸው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል እንድትሆንና በ1928 እኤአ በሆላንድ አምስተርዳም በሚካሄደው 9ኛው ኦሎምፒያድ እንድትሳተፍ ጥያቄ ማቅረብ ነበር፡፡ በወቅቱ የዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት የነበሩት  ቤልጅማዊው ሄነሪ ደባይላቱር ነበሩ፡፡ በዘውድ ስርዓት ትመራ የነበረችው ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ አገራት በኦሎምፒክ ጨዋታዎች ተሳትፎ ለማድረግና ለማስተናገድ ብቃት የላቸውም በሚል አቋማቸው በመፅናት ጥያቄውን ሳይቀበሉት ቀርተዋል፡፡ ከዚህ በኋላ  በ1940 እኤአ ላይ የኢትዮጵያ የስፖርት ኮንፌደሬሽን ቢመሰረትም በቀጣይ ስምንት ዓመታት በአገሪቱ ዘመናዊ   ስፖርት ያን ያህል ሳይስፋፋ በመቆየቱ በኦሎምፒክ ለመሳተፍ የሚደረጉ ጥረቶች አልነበሩም፡፡ በ1956 እኤአ ላይ የኦሎምፒክ ጨዋታዎቹን የምታስተናግደው የአውስትራሊያዋ ከተማ ሜልቦርን ስትሆን ኢትዮጵያ በዚህ ኦሎምፒክ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ለመሳተፍ በመወሰን መንቀሳቀስ ጀመረች። በዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል ለመሆንና በኦሎምፒክ ለመሳተፍ በአምስት አለም አቀፍ የስፖርት ፌደሬሽኖች አባል መሆኗ በማረጋገጥ መስራት ያስፈልግ ነበር። ስለሆነም በስፖርት ኮንፌደሬሽኑ አማካኝነት የእግር ኳስ፤ የአትሌቲክስ፤ የቦክስ፤ የብስክሌት፤ እና የቅርጫት ኳስ ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽኖች አባል ለመሆን ማመልከቻ ገባ፡፡  ለኦሎምፒክ ተሳትፎ የተቀመጠውን መስፈርቶች ባታሟላም ዓለም አቀፍ የኦሎምፒክ ኮሚቴ አባልነቱን አፅድቆላት ኢትዮጵያ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በ1956 እኤአ ሜልቦርን ከተማ ባዘጋጀችው ኦሎምፒክ የመሳተፍ እድል አገኘች፡፡
ከዚህ በታች የቀረበው ኢትዮጵያ በ1956 እኤአ በሜልቦርን፤ አውስትራሊያ  ከተሳተፈችበት 16ኛው ኦሎምፒያድ  አንስቶ በ1980 እኤአ ላይ በራሽያ ሞስኮ  እስከ ተከናወነው 22ኛው ኦሎምፒያድ ድረስ የኢትዮጵያውያን የኦሎምፒክ ገድል  የሚያወሳ ነው፡፡ ከ1956 እስከ 1980 እኤአ ኢትየጵያ በተከታታይ በተካፈለችባቸው  6 ኦሎምፒያዶች በርካታ ፈርቀዳጅ ታሪኮች ተመዝግበዋል፡፡ በአምስቱ ኦሎምፒያዶች ኢትዮጵያን በመወከል የሚሳተፉት ወንድ ኦሎምፒያኖች ብቻ ነበሩ፡፡ ሴት ኦሎምፒያኖች ለመጀመርያ ጊዜ ለመሳተፍ የበቁት በ1980 እኤአ በሞስኮ ኦሎምፒክ ነበር። በአጠቃላይ በ6ቱ ኦሎምፒያዶች  5 የወርቅ፤ 1 የብርና 4 የነሐስ ሜዳልያዎች ተገኝተዋል። በዚህ ምዕራፍ ከረጅም ርቀት የአትሌቲክስ ውድድሮች ባሻገር በአጭር እና በመካከለኛ ርቀትም ተሳትፎዎች ነበሩ፡፡ በብስክሌትና የቦክስ ስፖርት ውድድሮችም ተከታታይ ተሳትፎዎች የነበሩ ሲሆን በዝላይ፤ በጦር ውርወራ እና በርምጃ ውድድሮች ለመካፈል ተችሏል፡፡
የመጀመርያው የኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ተሳትፎ
በ16ኛው ኦሎምፒያድ አውስትራሊያ፤ ሜልቦርን (1956 እኤአ)
ኢትዮጵያ የመጀርያውን ኦሎምፒክ ተሳትፎ በአውስትራሊያዋ ከተማ ሜልቦርን ላይ በ1956 እኤአ በተካሄደው 16ኛው ኦሎምፒያድ አድርጋለች። በሁለት የስፖርት ዓይነቶች አትሌቲክስ እና ብስክሌት 12 ኦሎምፒያኖች 10 የኦሎምፒክ ውድድሮችን ተካፍለዋል፡፡ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት የመሩት ካፒቴን ላርሰን ይባላሉ፡፡ በመጀመርያው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ተሳትፎ በአትሌቲክስ በተለይ በአጭር እና መካከለኛ ርቀት ያተኮረ ሲሆን ጠንካራው ተሳትፎም በማራቶን ነበር፡፡ በ100 ሜትር፤ 200 ሜትር፤ በ4  በ100 ሜትር ፤ በ4 በ400 ሜትር ዱላ ቅብብልና  በ800 ሜትር በ1500 ሜትር የተሳተፉት ኃይሉ አበበ፤ ለገሰ በየነ፤ ንጉሴ ሮባ፤ ሃይሌ በቀለና በየነ አየኖ ማሞ ወልዴ ነበሩ፡፡ በመካከለኛ ርቀት ደግሞ በ1500 ሜትር  ማሞ ወልዴ ተሳትፏል፡፡ በአጭርና በመካከለኛ ርቀት በመጀመርያው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ተሳትፎ በእነዚህ ኦሎምፒያኖች ፈር የተቀደደ ሲሆን ሁሉም በማጣርያ ውድድሮች ላይ ተሳትፈው ከግማሽ ፍፃሜ ሳያልፉ ቀርተዋል፡፡ በማራቶን  ውድድር የተሳተፉት ኦሎምፒያኖች  2፡53.37 በሆነ ጊዜ 29ኛ ደረጃ ያገኙት ባሻዬ ፈለቀ እና 2፡58.49  በሆነ ሰዓት በ32ኛ ደረጃ የጨረሱት ገብሬ ብርቄ ናቸው፡፡
በኦሎምፒክ ብስክሌት ውድድሮች ደግሞ 4 ኦሎምፒያኖች በቡድን እና በግል በመሳተፍ የኢትዮጵያን የኦሎምፒክ የመጀመርያ ተሳትፎ አድምቀውታል፡፡ ገረመው ደንቦባ፤ መስፍን ታዬ እና ዘሃዬ ባህታ በቡድን በነበራቸው ተሳትፎ በ99 ነጥብ በ9ኛ ደረጃ ለመጨረስ መቻላቸው  በመጀመርያው የኦሎምፒክ ተሳትፎ ከፍተኛ ውጤት ነበር፡፡  በግል ውድድር ገረመው ደንቦባ በ25ኛ ደረጃ፤ መስፍን ታዬ በ36ኛ ደረጃ፤ ዘሃዬ ባህታ በ38ኛ ደረጃ ውድድራቸውን ሲያጠናቅቁ ንጉሴ መንግስቱ ቢሳተፍም ውድድሩን አቋርጦ ወጥቷል፡፡
የአበበ ቢቂላ ፈርቀዳጅ ውጤት
ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ
በ17ኛው ኦሎምፒያድ ጣሊያን፤ ሮም
(1960 እኤአ)
በሮም ከተማ በሚገኘው ኦሎምፒክ ስታድዬም የተካሄደው 17ኛው ኦሎምፒያድ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የቲቪ ስርጭት በሰሜን አሜሪካ ሊያገኝ የበቃ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ እና በብስክሌት  12 ኦሎምፒያኖች በ9 ውድድሮች ያሳተፈችበትን ይህን ኦሎምፒክ በዋና አሰልጣኝነት ያገለገሉት ሜጀር ኦኒ ኒስካነን ነበሩ፡፡ በማራቶን ውድድር አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ሮጦ በማሸነፍ የመጀመርያውን ወርቅ ሜዳልያ ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ሲጎናፀፍ፤ አበበ  ዋቅጅራ ደግሞ በሰባተኛ ደረጃ ዲፕሎማ አግኝቷል፡፡ በሌሎች የአትሌቲክስ ውድድሮች ንጉሴ ሮባ በ100 ሜትር፤ ሰይድ ሙሴ በ400 እና በ800 ሜትር፤ ሰይድ መሃመድ በ5ሺ እና በ10ሺ ሜትር ተሳትፈው ከግማሽ ፍጻሜ ሳያልፉ ቀርተዋል፡፡ በብስክሌት  በግልና በቡድን በተካሄዱ  ውድድሮች  ክፍሉ አላዛር፤ ገረመው ደንቦባ፤ አሙሴ ተሰማ እና መርጊያ አድማሱ ተሳትፈዋል፡፡ 17ኛው ኦሎምፒያድ ኢትዮጵያ በ1 የወርቅ ሜዳልያ እና በ1 ሰባተኛ ደረጃ 10 ነጥብ በማስመዝገብ ከአፍሪካ 1ኛ ደረጃ  ከዓለም 18ኛ ደረጃ ይዛ ያጠናቀቀችበት ነው፡፡
የአበበ ቢቂላ ዳግማዊ ድል
በ18ኛው ኦሎምፒያድ  ጃፓን፤ ቶኪዮ
 (1964 እኤአ)
በ1964 እኤአ የጃፓኗ ቶኪዮ ከተማ ያስተናገደችው ይህ ኦሎምፒክ በ64 አገራት በሳተላይት የቴሌቭዥን ስርጭት  ያገኘ ነበር። በቶኪዮ ብሄራዊ  ስታድዬም በተካሄደው በዚህ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ በ3 የስፖርት አይነቶች በአትሌቲክስ፤ በብስክሌት እና በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በቦክስ ውድድሮች ላይ በ12 ኦሎምፒያኖቿ 11 ውድድሮችን አድርጋለች። በማራቶን አበበ ቢቂላ የዓለምና የኦሎምፒክ ሪከርድን በማስመዝገብ ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳልያ ክብር ሊያገኝ ችሏል። በሁለት  ኦሎምፒኮች በማራቶን ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን አከታትሎ በመውሰድ  ክብረወስን ያስመዘገበበት ነው፡፡ ማሞ ወልዴ ደግሞ በ10ሺ ሜትር በመወዳደር 4ኛ ደረጃ ለማግኘት በቅቷል፡፡ በ18ኛው ኦሎምፒያድ ኢትዮጵያ በቦክስ ስፖርት ለመጀመርያ ጊዜ ለመሳተፍ የቻለችበት ከመሆኑም በላይ በብስክሌትም ለሶስተኛ ተከታታይ ኦሎምፒክ ተወዳድራለች፡፡ በኦሎምፒክ የብስክሌት   በግል እና በቡድን ውድድሮች ለመካፈል የበቁት 4  ኦሎምፒያኖች ሚካኤል ሳጊምቤልኒ፤ ፍስሐ ፅዮን ገብረእየሱስ፤ ሱሌማን አምባዬ እና የማነ ነጋሲ ነበሩ፡፡  ኢትዮጵያ በ18ኛው ኦሎምፒያድ ቶኪዮ ላይ በ1 የወርቅ ሜዳልያ እና በ1 የአራተኛ  ደረጃ ውጤቶች 13 ነጥብ በማስመዝገብ ከአፍሪካ 1ኛ ከዓለም 18ኛ ደረጃ ነበራት፡፡
የማሞ ወልዴ ጀግንነት
19ኛው ኦሎምፒያድ ሜክሲኮ፤ ሜክሲኮ ሲቲ (1968 እኤአ)    
ሜክሲኮ በግዙፉ የአዝቴካ ስታድዬም ያስተናገደችው 19ኛው ኦሎምፒያድ ላይ ኢትዮጵያ በ3 የስፖርት አይነቶች በአትሌቲክስ፤ በብስክሌት እና በቦክስ 13 የኦሎምፒክ ውድድሮችን ስታደርግ 18 የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች ለመሰለፍ በቅተዋል፡፡
በዚህ ኦሎምፒክ በዋና አሰልጣኞች ሜጀር ኦኒ ኒስካነንና   ንጉሴ ሮባ መሪነት 10 ኢትዮጵያውያን በሰባት የአትሌቲክስ ውድድሮች የተሳተፉ ሲሆን ለኢትዮጵያ ትልቁን ውጤት  ያስመዘገበው በሶስት የውድድር ተግባራት ተካፍሎ አንድ የወርቅና አንድ የብር ሜዳልያ ያስመዘገበው ማሞ ወልዴ ነው፡፡ በማራቶን የወርቅ ሜዳልያ 10ሺ እና ማራቶን ውድድሮች ሁለት ሜዳልያዎች በማግኘቱ ነበር፡፡ በማራቶን ለራሱ የመጀመርያውን ለአገሩ ደግሞ በ3 ተከታታይ ኦሎምፒኮች 3ኛው የማራቶን ድል በማስመዝገብ የወርቅ ሜዳልያውን ከመውሰዱም በላይ በ10ሺ ሜትር ደግሞ በታሪክ የመጀመርያውን የብር ሜዳልያ ክብር ማስመዝገብ  ችሏል፡፡ በቦክስ ስፖርት ለሁለተኛ ተከታታይ ኦሎምፒክ ተሳትፎ ሲደረግ፤ በብስክሌት ለአራተኛ ተከታታይ ኦሎምፒክ መሳተፍ ተችሏል፡፡ በብስክሌት በግል እና በቡድን ማጣርያ ውድድሮች የተሳተፉት ኦሎምፒያኖች ተከስተ ወልዱ፤ የማነ ነጋሲ ፤ ማሃሪ እቁባሚካኤል እና ሚካኤል ሳጊምቤልኒ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በ1968 እኤአ በሜክሲኮ በተካሄደው 19ኛው ኦሎምፒያድ ላይ ኢትዮጵያ 1 የወርቅና 1 የብር ሜዳልያዎች እንዲሁም 3 ስድስተኛ ደረጃ እና 2 የስምንተኛ ደረጃ ውጤቶች በማስመዝገብ በ26 ነጥብ ከዓለም 13ኛ ደረጃ አግኝታ ጨርሳለች፡፡
የማሞ እና የምሩፅ ነሐሶች
በ20ኛው ኦሎምፒያድ በፌደራል ሪፖብሊክ ጀርመን፤ ሙኒክ (1972 እኤአ)
በሙኒክ  ኦሎምፒክ ስታድዬም በተካሄደው 20ኛው ኦሎምፒያድ ኢትዮጵያ በ3 የስፖርት አይነቶች በአትሌቲክስ፤ በብስክሌት እና በቦክስ 31  ኦሎምፒያኖች በማድረግ በ20 የኦሎምፒክ ውድድሮች ተሳትፋለች፡፡ ሁለት የነሐስ ሜዳልያዎችን ያስመዘገቡት ደግሞ በማራቶን  ማሞ ወልዴ እና በ10ሺ ሜትር ምሩፅ ይፍጠር ነበሩ፡፡
በዚህ ኦሎምፒክ ከማራቶን እና 10ሺ ሜትርተሳትፎ ባሻገር በአጭር ርቀት እና በመካከለኛ ርቀት ውድድሮች በነበረው ተሳትፎ ካለፉት ኦሎምፒያዶች የተሻሉ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡
በ100 ሜትር ማጣርያ እግዚ ገብሬ በ10.89 ሰከንዶች ሲሳተፍ፤ በ800 ሜትር ሙሉጌታ ከበደ እስከ ግማሽ ፍፃሜ ሽብሩ ረጋሳ ደግሞ በማጣርያ መሳተፍ ችለዋል፡፡ በ4 በ100 ሜትር የዱላ ቅብብል ሲሳይ ፈለቀ፤ ሰለሞን በላይ ከበደ በዳሶ እና እግዚ ገብሬ ቢሳተፉም ውድድሩን አልጨረሱም፡፡ በ1500 ሜትር ሃይሉ ኤባ እና ሽብሩ ረጋሳ እስከ ግማሽ ፍፃሜ የተወዳደሩ ሲሆን፤ በ5000 ሜትር አሁን አሰልጣኝ የሆኑት እና ኦሎምፒያኖችን ውጤታማ ማድረግ የቻሉት ቶሎሳ ቆቱ በማጣርያ ተወዳድረዋል፡፡
በቦክስ ስፖርት በተከታታይ በ3 ኦሎምፒኮች በመሳተፍ  በ54 ኪ ግ የቀላል ሚዛን መሃመድ አየለ በኮርያ ቦክሰኛ፤ በ65 ኪግ ደግሞ ፈቃዱ ገብረስላሴ በጃፓን ቦክሰኛ በመጀመርያ ዙር ተሸንፈው ከውድድር ውጭ ሆነዋል፡፡ በብስክሌት  በቡድን የማጣርያ እና በግል ዋና ውድድሮች 4 የቦክስ ኦሎምፒያኖች ተሳትፈዋል። በግል ጥሩ ውጤት ያስመዘገበው በ53ኛ ደረጃ የጨረሰው ተከስተ ወልዱ ሲሆን ፍስሃ ፅዮን ገብረእየሱስ፤ ርእሶም ገብረመስቀል እና ሱሌማን አብዱልራህማን ቢሳተፉም አልጨረሱም፡፡ በፌደራል ሪፖብሊክ ኦፍ ጀርመን በ1972 እኤአ በተከናወነው የሙኒክ ኦሎምፒክ በአጠቃላይ በ2 የነሐስ ሜዳልያዎች 12 ነጥብ በማስመዝገብ ከዓለም 18ኛ ደረጃ ይዛ አጠናቅቃለች፡፡
የምሩፅ ይፍጠር ድርብ ድሎች
በ22ኛው ኦሎምፒያድ ሶቪዬት ህብረት፤ ሞስኮ (1980 እኤአ)
የሞስኮ ከተማ ካስተናገደችው 21ኛው ኦሎምፒያድ በፊት ኢትዮጵያ  በ1976 በካናዳ ሞንትሪያል የተካሄደውን ኦሎምፒያድ እልተሳተፈችም ነበር፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ወደ ውድድር ስፍራው ለመጓዝ አትሌቶችን መርጦ ዝግጅታቸውን አጠናቅቀው ነበር፡፡ በደቡብ አፍሪካ  በነበረው የአፓርታይድ ስርዓት በጥቁሮች ላይ የሚደርሰውን በደል በመቃወም ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ኦሎምፒኩን ላለመሳተፍ ወስናለች፡፡
በ1980 እኤአ ላይ  የሌኒን ስታድዬም ተብሎ በሚጠራው እና አሁን ሉዝሂንኪ በሚባለው ስታድዬም በተካሄደው 21ኛው አፖሎምፒያድ ላይ ኢትዮጵያ እና ሌሎች የአፍሪካ አገራት ወደ ኦሎምፒክ መድረክ ተመለሱ፡፡ ይሄው የኦሎምፒክ ተሳትፎም በተሳታፊ ኦሎምፒያኖች ብዛት፤ በሴት ኦሎምፒያኖች የመጀመርያ ተሳትፎ እንዲሁም በተገኙት ሜዳልያዎች ብዛት ካለፉት ሁሉ የተሻለ ነበር፡፡ በ3 የስፖርት አይነቶች 41 ኦሎምፒያኖች 39 ወንድ እንዲሁም ለመጀመርያ ጊዜ ሁለት ሴት ኦሎምፒያኖችን በማካተት በ26 የኦሎምፒክ ውድድሮች ተካፍለዋል፡፡ በተለይ በርዝመት ዝላይ፤ በሱሉስ ዝላይ እንዲሁም በጦር ውርወራ  የሜዳ ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያ ለመሳተፍ መብቃቷ ልዩ ታሪክ ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
በሞስኮው 22ኛው ኦሎምፒያድ ከፍተኛውን ውጤት ለማመዝገብ የበቃው በሙኒክ ኦሎምፒክ በ10ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳልያ አግኝቶ የነበረው ምሩፅ ይፍጠር ሲሆን በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር ድርብ የወርቅ ሜዳልያዎችን በመጎናፀፍ አዲስ ታሪክ ሊሰራ ችሏል፡፡
በ5ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያውን ምሩፅ ሲወስድ ሁለት የማጣርያ ውድድሮችን አድርገው በፍፃሜው አብረው የሮጡት መሃመድ ከድር እና  ዮሃንስ መሃመድ በ3ኛ እና በ10ኛ ደረጃ ጨርሰዋል፡፡ በ10ሺ ሜትር ደግሞ ማጣርያ አልፈው መሃመድ ከድር በነሐስ ሜዳልያ እንዲሁም ቶሎሳ ቆቱ በ7ኛ ደረጃ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል። በሌላ በኩል በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ አገሩ ተሳትፎ ባደረገችበት የ3ሺ ሜትር መሰናክል ውድድር እሸቱ ቱራ የነሐስ ሜዳልያ በማግኘት ፈርቀዳጅ ውጤት ሲያስመዘግብ በተመሳሳይ ውድድርሃይሉ ወልደፃዲቅ እና ግርማ ወልደሃና ተሳትፎ ቢያደርጉም ውድድሩን አልጨረሱም፡፡
በወንዶች ማራቶን  ከተሳተፉት  ኦሎምፒያኖች ደረጀ ነዲ በ7ኛ ደረጃ እንዲሁም መላኩ ደዱብጄ በ24ኛ ደረጃ ሲጨርሱ ከበደ ባልቻ ውድድሩን አልጨረሰም፡፡ በ100 ሜትር በሻ ቱፋ  በሁለት ፤ በ800 ሜትር አበበ ዘሪሁን፤ ንጉሴ በቀለ እና አጥሬ በዛብህ፤ በ1500 ሜትር ባልቻ ካሳ፤ ሃይሌ ዘሩ እና ንጉሴ በቀለ የማጣርያ ውድድሮች ተሳትፈዋል፡፡ በ4 በ400 ሜትር የዱላ ቅብብል የተሳተፉት አራት ኦሎምፒያኖች በሻ ቱፋ፣ ኩመላ ፉቱማ፣ አስፋው ደበሌ እና አጥሬ በዛብህ ውድድራቸውን አልጨረሱም፡፡
በወንዶች የረጅም ዝላይ 6.66 ሜትር በማጣርያው በመዝለል የተሳተፈው አበበ ገሰሰ ሲሆን፤ በሱሉስ ዝላይ ደግሞ ያደሳ ኩማ በማጣርያው 13.60 ሜትር በመዝለል ተሳትፏል፡፡ በጦር ውርወራ ሚሊኬሳ ቻልቺሳ በማጣርያው 51.04 ሜትር በመወርወር 18ኛ ደረጃ ያገኘ ሲሆን በ20 ኪሎ ሜትር የርምጃ ውድድር ደግሞ ተከስተ ምትኩ በፍፃሜው ውድድር በመካፈል 23ኛ ደረጃ አስመዝግቧል፡፡
በኦሎምፒክ መድረክ ኢትዮጵያ በሴት ኦሎምፒያኖች ለመጀመርያ ጊዜ የተሳተፈችው የመካከለኛ ርቀት 800 ሜትር እና 1500 ሜትር የአትሌቲክስ ውድድሮች  ነበሩ፡፡ በ800 ሜትር ፋንታዬ ሲራክ እንዲሁም በ1500 ሜትር ደግሞ አምሳለ ወልደገብሬል ኢትዮጵያን ለመጀመርያ ጊዜ በኦሎምፒክ መድረክ ለመወከል የበቁ ኦሎምፒያኖች ሲሆኑ ተሳትፏቸው በማጣርያ ውድድሮች የተወሰነ ነበር፡፡
በቦክስ ስፖርት 4ኛው የኦሎምፒክ ተሳትፎ ሲደረግ በ48 ኪሎ ግራም ብሩክ አስፋው በመጀመርያው ዙር በፊንላንድ ቦክሰኛ ሲሸነፍ፤ በ51 ኪሎ ግራም ሃሰን ሸሪፍ በመጀመርያ ዙር የጊኒን ቦክሰኛ በማሸነፍ ሁለተኛው ዙር ገብቶ በቡልጋርያው ቦክሰኛ ተሸንፏል፡፡ በ54 ኪሎግራም ደግሞ  አየለ ማሀመድ የመጀመርያ ማጣርያውን በፎርፌ ካለፈ በኋላ በሁለተኛ ማጣርያ የአፍጋኒስታን ቦክሰኛን አሸንፎ በሶስተኛው ማጣርያ በኩባ ቦክሰኛ ተሸንፏል። በ57 ኪሎግራም የመጀመርያ ማጣርያውን በፎርፌ ካለፈ በኋላ በሁለተኛ ማጣርያ የሲሸልስ ቦክሰኛን አሸንፎ በሶስተኛው ማጣርያ በብራዚል ቦክሰኛ ተሸንፏል፡፡ በ60 ኪግ ታደሰ ኃይሌ፤ በ63.5 ኪግ ኢብራሂም ሴዲ በሮማኒያ እና በፖርተሪኮ ቦክሰኞች በመጀመርያ ማጣርያ ተሸንፈው ከውድድር ውጭ ሆነዋል፡፡
በብስክሌት የተሳተፉት 8 ኦሎምፒያኖች ሲሆኑ በግል ውድድር ዘርጋበር ገብረህይወት፤ ጀማል ሮጎራ፤ ጥላሁን ወልደሰንበት እና ሙሴ ዮሃንስ ሲሆን በቡድን የማጣርያ ውድድር ደግሞ ሃይለሚካኤል ከድር፤ አየለ መኮንን፤ ታደሰ መኮንን እና ጥላሁን አለማየሁ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ በአጠቃላይ በ2 የወርቅ፤ 2 የነሐስ ሜዳልያዎች እና በ1 አራተኛ እና በ1 የሰባተኛ ደረጃ ውጤቶች ኢትዮያ በ22ኛው ኦሎምፒያድ ላይ 35 ነጥብ በማስመዝገብ ከዓለም 8ኛ ደረጃ አግኝታ ጨርሳለች፡፡
ይቀጥላል…..

Read 218 times