Monday, 02 August 2021 20:10

ተዓምረኛው ሰው በኦሎምፒክ

Written by 
Rate this item
(0 votes)


               የማራቶን ርቀት፣ ለብርቱ ሰው፣ ቀን ጉዞ ነው።
ለባለሪከርድ አትሌት፣ የሁለት ሰዓት ሩጫ ነው።
ለመኪና፣ የግማሽ ሰዓት መንገድ ነው።
ለቦይንግ 787 አውሮፕላን፣ የ3 ደቂቃ በረራ ነው።
በሮኬት አፍንጫ ላይ ተገጥሞ ወደ አለማቀፍ የጠፈር ማዕከል ለመጠቀው መንኮራኩርስ፣ የ6 ሴኮንድ እፍታ ነው። በደቂቃ ውስጥ፣ 10 ማራቶን ይጨርሳል።
 የማራቶን ርቀት ለመንኮራኩሩ፣
ከአዲስ አበባ ተነስቶ፣ በየትኛውም አቅጣጫ፣ የአገር ጥግ ድረስ ለመጓዝ፣ ሁለት ደቂቃ አይፈጅበትም። በአንድ ደቂቃ፣ ወደ አዋሳ ሄዶ እንደ መመለስ ነው-ፍጥነቱ።
የሰው ስራ፣ እውነትም ተዓምር ነው። ታዲያ፣ የሰው ስራ፣ በአንዳች ተዓምር የሚከሰት አይደለም- ከተዓምረኛ የሰው ብቃት ይመነጫል እንጂ።
እዚህ ላይ ነው፣ የኦሎምፒክ ክብረ በዓል በግርማ ሞገስ የሚገለጠው።
በ50 ወይም በ100 ሜትር ርቀት፣ ኢላማውን አስተካክሎ የሚመታ ተኳሽ፣ በየመንደሩ አይገኝም። ወደ ላይ የተወረወረውን ኢላማ አየር ላይ መምታት ደግሞ አለ። እንግዲህ አይነት ብቃት፣በይትኛውም መስክ መንፈስን በአድናቆት ያፈካል፡፡ የብቃትን ምጥቀት፣ አብዝቶና አድምቆ የሚጋብዝ ኦሎምፒክን የመሰለ ድግስ ላይ መታደል ነው? ከብቃት የልህቀት ጋር የሚስተካከል ትልቅ ክብር  የለምና።
የሁሉም ስኬት መነሻ፣ የሁሉም ድንቅ ታሪክ መፍለቂያ፣ የክቡር ሕይወት ሁሉ አለኝታ፣  የሰው ልጅ ብቃት ነው፡፡ ሌላ አይደለም፡፡ በሌላ አነጋገር፣ የሰውን ብቃት ልህቀት ማድነቅና ማክበር፣ ከምር ሰው መሆንና ያለመሆን ጉዳይ ነው፡፡ የሕይወትን ትርጉም ለማጣጣም የመቻልና ያለመቻል ጉዳይ ነው። ለዚህም ነው፤ ኦሎምፒክ የበዓል መንፈስ የሚጎናጸፈው። መጎናፀፍም የሚገባው።




Read 1252 times