Saturday, 31 July 2021 00:00

አሜሪካ ድርድርና ሁሉን አካታች ፖለቲካዊ ውይይት እንዲደረግ ጥሪ አቀረበች

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(6 votes)


           - በትግራይ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የባንክና የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲጀመር ጠይቃለች
          - የህውኃት ታጣቂ ቡድን ተኩስ ለማቆም አዲስ ቅድመ ሁኔታ አቅርቧል
          - መንግስት ከወር በፊት ያደረገውን የተናጠል ተኩስ አቁም እያከበረ መሆኑን ገልጿል
                        
             በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለማስቆም ሁሉም ወገኖች አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደርጉና በሁለቱ ወገኖች መካከል ድርድርና ሁሉን አካታች ፖለቲካዊ ውይይት እንዲደረግ የአሜሪካ መንግስት ጥሪ አቀረበ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ትናንት በሰጡት መግለጫ፤ ሁሉም ወገኖች አስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲያደርጉና ግጭትን ከሚያባብሱ ንግግሮች እንዲቆጠቡ የጠየቁ ሲሆን ግጭት ውስጥ ያሉት ሁለቱም ወገኖች ልዩነቶቻቸውን ለመፍታት ተገቢው መንገድ ወታደራዊ ኃይል ሳይሆን ድርድር ነው ብለዋል።
በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ያሳሰቡት ቃል አቀባዩ፣ መንግስት ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲያመቻች፣ የኤሌክትሪክ የቴሌኮሙኒኬሽንና የባንክ አገልግሎቶች በአስቸኳይ እንዲጀምሩ ጠይቀዋል።
የፌደራል መንግስት ከአንድ ወር  በፊት ያወጀውን የተናጠል ተኩስ አቁም አዋጅ ተከትሎ፣ ሰራዊቱን ከትግራይ ካስወጣ በኋላ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎችና በአጎራባች ክልሎች፣ የህውሃት ሃይሎች ትንኮሳ መፈጸማቸውን ጠቁሞ፤ መንግስት ግን ያወጀውን የተናጠል ተኩስ አቁም እያከበረ እንደሚገኝ አስታውቋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክረተሪያት ቢልለኔ ስዩም ሰሞኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ የህውሃት ሃይሎች ትንኮሳ የትግራይ ክልልን አልፎ ወደ አጎራባች ሁለት ክልሎች (አማራና አፋር ክልል) መግባቱን ጠቁመው፤ የመከላከያ ሰራዊት ራሱን ከመከላከል የዘለለ እርምጃ እየወሰደ አለመሆኑን ተናግረዋል።
የፌደራል መንግስቱ የቀረበውን የተናጠል ተኩስ አቁም አዋጅ ተከትሎ፣  ባለ ሰባት ነጥብ ቅድመ ሁኔታዎችን አቅርበው የነበሩት የህወሃት ታጣቂዎች፤ አሁን ደግሞ በድርድር ላይ የተመሰረተ ተኩስ አቁም ለማድረግ የሚያስችል አዲስ ቅድመ ሁኔታ አቅርበዋል።  
የህውሃት ታጣቂዊች በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ባቀረቡት የመጀመሪያ የተኩስ አቁም ቅድመ ሁኔታ ጥያቄያቸው፤ የአማራ ልዩ ሃይልና የኤርትራ ወታደር ክልሉን ለቀው እንዲወጡ፣ ተቋረጡ መሰረተ ልማቶች መልስው ስራ እንዲጀምሩ፣ ዓለም አቀፍ በረራዎች ትግራይ ከሚገኝ አየር ማረፊያ ቀጥታ በረራ እንዲያደርጉ፣ ያለ ምንም ገደብ የሰብዓዊ እርዳታ የሚቀርብበት መንገድ እንዲመቻች፣ የክልሉ በጀት እንዲለቀቅና በክልሉ የተፈጸመው የመብት ጥሰት በገለልተኛ ተቋም እንዲመረመር የሚል ነበር።
የህወሃት ሃይሎች ከትናንት በስቲያ ባቀረቡት የተሻሻለ የተኩስ አቁም ቅድመ ሁኔታ፤ አሁን አገሪቱን በመምራት  ላይ ያለው መንግስት፣ አገሪቱን  መምራት የሚያስችል ህገ-መንግስታዊ መብት የሌለው በመሆኑ ዋና የፖለቲካ ተዋንያኖችን ያቀፈ አካታች ፖለቲካዊ ሂደትና የሽግግር ስርዓት እንዲከናወን፣ የተኩስ አቁሙን ለማድረግ የሚያስችል ድርድር እንዲካሄድ፣ በትግራይ ተቋርጠው የቆዩ የባንክ፣ ኢንተርኔት፣ መብራት፣ የስልክና ትራንስፖርት አቅርቦቶች በአስቸኳይ እንዲጀምሩ፣ የአገር መከላከያ አባላት የሆኑትን ጨምሮ የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፣ የትግራይ  ተወላጆች የጅምላ እስር እንዲቆምና የ2013 እና 2014 በጀት በፍጥነት እንዲለቀቅ ጠይቋል።
የህወኃት ታጣቂ ሃይሎች የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ቀደም ሲል ከጠየቁት ቅድመ ሁኔታ የተሻለ ነው ብለው ያስቀመጡትን አዲሱን ቅድመ ሁኔታ መንግስት በአፋጣኝ ተፈጻሚ በማድረግ፣ በአገር ውስጥና አለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ለህዝብ ይፋ ማድረግ እንደሚኖርበትም አዲሱ የቅድመ ሁኔታ ሰነድ ያመለክታል።

Read 8436 times