Saturday, 31 July 2021 00:00

ቴዲ አፍሮ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬቱን ዛሬ ይቀበላል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ (ከጎንደር)
Rate this item
(3 votes)

 ከባለቤቱ፣ ከሴት ልጁና ከማናጀሩ ጋር ትላንት ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል
                           
                 ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) ትላንት ረፋድ ላይ ጎንደር ከተማ የገባ ሲሆን በአፄ ቴዎድሮስ አየር ማረፊያ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል። ዛሬ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የሚሰጠው የሰላሙ ዩኒቨርስቲ ጎንደር ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን፣ የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ፣ የጎንደር ባህል ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ገ/ማርያም ይርጋ፣ የፋሲለደስ ባህል ቡድንና ሌሎችም የከተማዋ ተዋቂ ሰዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ቴዲ አፍሮ ከባለቤቱ አርቲስት ሀምለሰት ሙጬና ከማናጀሩ አቶ ጌታቸው ማንደፍ ጋር በጎንደር ዩኒቨርስቲ ቴዎድሮስና ማራኪ ካምፓሶችን የጎበኘ ሲሆን፤ የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን፣ በአጠቃላይ ስለ ዩኒቨርስቲው እንቅስቃሴና ስኬት ገለጻ ያደረጉለት ሲሆን የዩኒቨርቲቲው ተማሪዎችም በፉጨትና በጭብጨባ አድናቆታቸውን ገልጸውለታል።
ከዩኒቨርስቲው ጉብኝት በኋላ ወደ መሃል ከተማ ያቀናው አርቲስቱ፤ ቴዎድሮስ አደባባይ ሲደርስ ህዝቡ የአጼውን ሃውልት ዙሪውን ከቦ ደማቅ አቀባበል ያደረገለት ሲሆን እርሱም ለአጼ ቴዎድሮስ የአበባ ጉንጉን ካስቀመጠና የክብር ሰላምታ ከሰጠ በኋላ ተሰናብቶ ወደማረፊያው አቅንቷል።
ጎንደር ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ትውልድ ከሚባሉት ዩኒቨርስቲዎች አንዱ ሲሆን  ወደ ሰባ ዓመት እድሜ ያስቆጠረ ዩኒቨርሲቲው በተለያየ ዘርፍ ያስተማራቸውን ተማሪዎች የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የተማሪ ወላጆችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በሚገኙበት በድምቀት የሚያስመርቅ ሲሆን ለእውቁና ተወዳጁ የፍቅርና አንድነት አቀንቃኝ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ያበረክታል።
ዩኒቨርስቲው ከዚህ ቀደም፣ ለአንጋፋው ድምጻዊ የክብር ዶክተር ማህሙድ አህመድና ለቀድሞው ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ተፈራ ዋልዋ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ መስጠቱ አይዘነጋም።


Read 8082 times