Saturday, 31 July 2021 00:00

በመዲናዋ የኮሪደር ደኅንነት ማሻሻያና ሁለተኛ ዙር የፍጥነት አስተዳደር ፕሮጀክት መጠናቀቁ ተገለጸ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 አዲስ አበባ የዓለም ዓቀፍ ከተሞች መረብ አባል እንደመሆኗ የከተማዋ ኮሪደር ደኅንነት ማሻሻያና ሁለተኛ ዙር የፍጥነት አስተዳደር ፕሮጀክት መጠናቀቁን የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ም/ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ብርሀኑ ግርማ አስታወቁ፡፡
 የጤናማ ከተሞች ሽርክና እውቅና ያለው ዓለም ዓቀፍ የከተሞች መረብ ሲሆን እንደ ካንስር፣ ስኳር፣ የመንገድ ትራፊክ አደጋና የመሳሰሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በመከላከል በዓለም ዙሪያ ከ300 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ህይወት ለመታደግ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ይታወቃል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከዚህም ዓለም አቀፍ ኢኒሽዬቲቭ ጋር የመንገድ ደህንነት ማሻሻያ ሥራዎችን  በጋራ እንደምታከናውን የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ መግለጫ ጠቁሟል፡፡
“የማህበረሰብ ጤናን ለማሻሻል ጠንካራ አመራር ይጠይቃል” ያሉት ኢንጂነር ብርሀኑ፤ የጤናማ ከተሞች ሽርክና ዓለም ዓቀፍ መረብ የመጀመሪያ ዙር በመዲናዋ የተጀመረው በ2010 ዓ.ም እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ም/ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም፤ “ነዋሪዎቻቸው የተሟላ ህይወትና ረጅም እድሜ እንዲኖራቸው አበክረው ከሚሰሩ ከእነዚህ ዓለም አቀፍ እውቅና ካላቸው የከተሞች ቡድን አባላት ጋር በጋራ የመስራት እድል በማግኘታችን ደስተኛ ነን” ብለዋል፡፡
የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ባወጣው መግለጫ እንደጠቆመው፤ ከፍጥነት ወሰን በላይ በማሽከርከር የሚከሰት የትራፊክ አደጋን ለመከላከል የጤናማ ከተሞች ሽርክና 50 ሺ ዶላር ቀጣይነት ያለው እርዳታ (renewal grant) ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፍጥነት መቆጣጠሪያ ራዳር መግዢያ አበርክቷል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢንጂነር ብርሀኑ እንዳስታወሱት፤ ባለፈው ዓመት በዚሁ ድርጅት ለመጀመሪያ ዙር የፍጥነት አስተዳደር ፕሮጀክት፣ በ90,819.12 ዶላር እርዳታ፣  ዲጂታል ቋሚ የፍጥነት መጠን ጠቋሚዎችን በመግዛትና በፒያሳ ዙሪያ በመትከል፣ በአካባቢው ያለውን ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር ለመቀነስና የህግ ማስከበሩን ስራ በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ተችሏል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በየዓመቱ በአማካይ ከ450 ሰዎች በላይ በትራፊክ ግጭት ምክንያት ህይወታቸውን እንደሚያጡ ያመለከተው መግለጫው፤ ለመንገድ ትራፊክ አደጋ ከሚያጋልጡ ምክንያቶች ውስጥ ደግሞ ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር የአደጋ መንስኤ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ ያመለክታል። በፍጥነት ማሽከርከር ለአደጋ የማጋለጥ እድሉ ከፍተኛ ሲሆን የሚያደርሰውን ጉዳትም እንዲሁም የከፋ ያደርገዋል፡፡ በአጠቃላይ ከሚደርሰው የትራፊክ ግጭት ውስጥ 1/3ኛ የሚሆነውን ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር እንደሚሸፍን ጥናቶች እንደሚያመለክቱ ተጠቅሷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የማህበረሰቡ ከፍተኛ የጤና ችግር የሆነውን በተለይም አምራች የሆነውን ዜጋ እየቀጠፈ ያለውን የትራፊክ ግጭት ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ የመፍትሔ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል። ይኸውም የትራፊክ አደጋ መረጃዎች አያያዝና አስተዳደር ስርዓትን ማዘመን፣ የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታና ዲዛይን ማሻሻያ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ እንዲሁም የትራፊክ ደንብ ማስከበር በተለይም የፍጥነት ገደብ ቁጥጥር ሥራዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው ተብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ትራፊክ ማጅመንት ኤጀንሲ ከጤናማ ከተሞች ሽርክና ጋር በመተባበር በከተማዋ የተመረጡ የተለያዩ ኮሪደሮች የመንገድ ደህንነት ለማረጋገጥ ሁለተኛውን ዙር የመንገድ  አካፋይ ደህንነት ማሻሻያና የፍጥነት አስተዳደር ፕሮጀክት በስፋት አከናወኗል የሚለው መግለጫው፤ ኤጀንሲው በመጀመሪያ 4.5 ኪ.ሜ የሚሸፍኑትን አጎሮ-ጃክሮስ መብራት ኃይል- ሃያ አራት ኮሪደሮች ለይቷል ብሏል። የኮሪደሮቹ ሁለቱም አቅጣጫዎች 30 ሜትር ስፋት ያላቸው ሁለት መስመሮች (lanes) የያዙ ሲሆኑ በተጨማሪም የእግረኛ መንገድና መከለያ አጥር ዲዛይን የተደረገውና የተገነባው ዋና መንገዶችን (principal arterial street) ጥቅም ላይ ለማዋል ባወጣው መመዘኛ መስፈርት መሠረት መሆኑም  ተጠቁማል፡፡
“የተመረጡ ኮሪደሮች ከመሀል ከተማ ወደ ምስራቅ አቅጣጫ ከመኖሪያ አካባቢ ወደ ስራ ቦታ ደርሶ መልስ የሚያጓጉዝ መስመር በመሆኑ ስትራቴጂካል እንደሆነም ታምኖበታል፡፡ ከምንም በላይ ኮሪደሮቹ የተመረጡት የመንገድ ደህንነትና የትራፊክ እንቅስቃሴ ችግር ያለባቸው በመሆኑ ነው። ከ2008 እስከ 2010 ዓ.ም ያለው የትራፊክ አደጋ መረጃ እንደሚያሳየው፤ በእነዚህ የመንገድ አካፋዮች ከ31 ሰዎች በላይ በትራፊክ ግጭት  ምክንያት ህይወታቸው አጥተዋል፡፡”
 “በእነዚህ የተለዩ ኮሪደሮች የመንገድ ደህንነትና ፍሰት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ለመቅረፍ ከተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎች መካከል በመጋጠሚያና ማቋረጫ ቦታዎች ላይ የተደረገ ማሻሻያ፣ የፍጥነት ወሰን፣ የትራፊክ ማቀዝቀዣ እርምጃዎችና የእግረኛ መከላከያ አጥሮች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ እነዚህ በኢንጂነሪንጉ የተወሰዱ እርምጃዎች ከትራፊክ ደንብ ማስከበር ሥራዎች ጋር ተደምረው በኮሪደሮች አካባቢ ያለውን የተሽከርካሪዎች ፍጥነት ለመቆጣጠር ያስችላሉ”
ከጤናማ ከተሞች ሽርክና በእርዳታ  የተገኘው 50 ሺህ ዶላር ለትራፊክ ደንብ ቁጥጥር ስራ የሚያገለግል ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ የፍጥነት መቆጣጠሪያ ራዳር ግዢ መዋሉ የተጠቆመ ሲሆን የተገዛው ራዳር  ቀንም ሌሊት የመስራት አቅም አለው፤ ምንም ዓይነት ስህተት እንዳይሰራና አውቶማቲክ (automatic calibration with zero tolerance/error) ተደርጎ የተዘጋጀ ነው ተብሏል። "በተጨማሪም በቪዲዮ የተደገፈ ዳታ ቤዝ አለው፤ በመስክ ላይ ማተም (ፕሪንት ማድረግ) ያስችላል፤ ለመቆሚያ የሚያገለግል ትራይፖይድ አለው፡፡ ለ12 ደንብ አስከባሪ ባለሙያዎችም የራዳሩን አጠቃቀም አስመልክቶ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል፤ ሰርተፌኬትም አግኝተዋል።" ሲል መግለጫው ያብራራል፡፡
ይህ የጤናማ ከተሞች ሽርክና የብሉምበርግ ፊላንትሮፒስ፣ ከዓለም ጤና ድርጅትና ቫይታል ስትራቴጂ ጋር በመተባበር ድጋፍ የሚሰጡት ፕሮጀክት መሆኑ ታውቋል፡፡

Read 352 times