Friday, 30 July 2021 00:00

እነ ዶ/ር ደብረ ፅዮን፣ ጌታቸው ረዳና ጀነራል ጻድቃንን ጨምሮ በህውሃት ከፍተኛ አመራሮች ላይ ክስ ተመሰረተ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

   - ከ500 በላይ የሰው ምስክሮችና ከ5 ሺ በላይ የሰነድ ማስረጃዎች ቀርበዋል
          - በ2 መዝገቦች በተከፈተው ክስ ከ136 በላይ ተከሳሾች ተካተዋል
         - ክስ ከቀረበባቸው ባስልጣናት ወደ 40 የሚጠጉት በቁጥጥር ስር የዋሉ ናቸው
                    
             የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በእነዶ/ር ደብረ ፅዮን፣ ጌታቸው ረዳና ጀነራል ጻድቃን ገ/ትንሣኤን ጨምሮ ከ130 በላይ በሚሆኑ የቀድሞ የሕውሃት ከፍተኛ አመራሮች ላይ ክስ መሰረተ።  በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የህገ መንግስትና የሽብር ወንጀሎችን በሚመለከተው አንደኛ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 27/28/02 የቀረበው ይኸው ክስ፤ የህዝባዊ ወያኔ አርነት ትግራይ ከፍተኛ አመራር የነበሩት ዶ/ር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል፣ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሔር፣ ጌታቸው ረዳ፣ አለም ገ/ዋህድን ጨምሮ 62 ተከሳሾች የተካተቱበት ሲሆን- ጀነራል ጻድቃን ገ/ትንሳኤ፣ ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወርደ፣ ሜጀር ጀነራል ዮሐንስ ወ/ጊዮርጊስና ብርጋዴር ጀነራል ምግበ ኃይለን ጨምሮ በ74 የቀድሞ  የህወሃት  ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንንች ላይም ዐቃቤ ህግ  ክስ መስርቷል።
ዐቃቤ ህግ የፌደራል መንግስቱን በኃይል ለመለወጥ በማሰብ፣ በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ከህውሃት አመራሮች ተልእኮን በመቀበል ጥቃት ለማድረስ የሚችል የትግራይ ወታደራዊ ኮማንዶን አደራጅተዋል በሚል ክስ ከመሰረተባቸው ከእነዚህ 74 ከፍተኛ የጦር መኮንኖች መካከል በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ይገኙበታል ተብሏል።
ወታደራዊ የጦር መኮንኖቹ በትግራይ ክልል በተለያዩ ቦታዎች ላይ በሚገኙ የሰሜን ዕዝ የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት፣ በፌደራል ፖሊስና በፌደራል የመንግስት ተቋማት እንዲሁም በአማራና በአፋር ክልሎች ላይ በተጨማሪም በኤርትራ  ላይ ጥቃት አድርሰዋል ሲል በክሱ ላይ ገልጿል።
የ1996 የወንጀል ህግንና የሽብር ወንጀል ለመከላከልና ለመቆጣጠር በ2012 የወጣውን አዋጅ በመተላለፍ ክስ በተመሰረተባቸው በእዚህ የህውሃት  ክፍተኛ አመራሮችና የጦር መኮንኖች ላይ ዐቃቤ ህግ ከአምስት ሺ ሶስት መቶ ገጽ በላይ የሰነድ ማስረጃዎችና የቪዲዮ ማስረጃዎችን እንዲሁም የቴክኒክ ማስረጃዎችን ለፍርድ ቤት ማቅረቡንም ገልጿል። ከ500 በላይ የሰው ምስክሮችም ለክሱ በማስረጃነት መያዛቸውን ዐቃቤ ህግ አመልክቷል።
በዐቃቤ ህግ ክስ ከተመሰረተባቸው ከ74ቱ ከፍተኛ ወታደራዊ  አመራሮች መካከል 20 የሚሆኑት በተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ በቁጥጥር ስር እንደሚገኙ ያመለከተው የዐቃቤ-ህግ የክስ መዝገብ፤ 54ቱ ደግሞ ክሱ በሌሉበት የተመሰረተ መሆኑን ጠቁሟል። በ74 ወታደራዊ መኮንኖች ላይ የቀረበውን ክስ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ሶስተኛ የፀረ ሽብር ወንጀል ችሎት  እየተመለከተው ይገኛል።
ዐቃቤ ህግ በእነ ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ላይ በመሰረተው ክስ፣ ስልሳ ሁለት ሰዎች  የተካተቱበት ሲሆን መዝገቡ የህውሃት ከፍተኛ አመራሮችንና በድርጅቱ ስር የነበሩ ተቋማትንና አካቷል።
ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በክስ መዝገቡ ላይ እንዳመለከተው፤ በዚህ መዝገብ ውስጥ ክስ የተመሰረተባቸው የህወሃት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ ውሳኔ በመስጠት ከፍተኛ ተሳትፎ የነበራቸው የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትና የክልል መንግስት ካቢኔ አባላትም ይገኙበታል።
የዐቃቤ ህግ በክሱ ካካተታቸው ተቋማት መካከልም የኤፈርት ድርጅቶች፣ የግልና የመንግስት ተቋማት አመራሮች የሚገኙበት ሲሆን፣ በትግራይ ክልል በተካሄደው ኢ-ህገመንግስታዊ  ምርጫ ላይ ተሳትፎ ያደረጉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ሊቃነ መናብርት፣ የትግራይ ምርጫ ኮሚሽን አመራሮችና የቀድሞ የህውሃት ከፍተኛ አመራር የነበሩ ታዋቂ ግለሰቦችም ይገኙበታል።
ፍ/ቤቱ የዐቃቤ ህግን የክስ መዝገብ ተቀብሎ በማረሚያ ቤት የሚገኙትን ተከሳሾች ማረሚያ ቤት እንዲያቀርባቸው፣ ቀሪ ተከሳሾችን ደግሞ የፌደራል ፖሊስ መጥሪያ አድርሶ እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቶ ጉዳይን ለማየት ለሐምሌ 26 ቀን 2013 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል።

Read 1178 times