Monday, 26 July 2021 00:00

ኡጋንዳዊው ጋዜጠኛ - ስለ ህውኃት፣ ዓለማቀፉ ሚዲያና የፌደራሉ መንግስት

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(2 votes)

 “ዓለማቀፍ ሚዲያዎች የታጣቂውን ቡድን አጀንዳ በማራመድ በትግራይን ያለውን ሁኔታ ያባብሱታል አያቃልሉትም”
                           
              ኡጋንዳዊው ጋዜጠኛ ኩንጉ አል-ማሃዲ አዳም ከትናንት በስቲያ ሃሙስ በድረ ገፅ ባሰፈረው ፅሁፉ፤ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የታጣቂውን ህውሃት ቡድን አጀንዳ በማራመድ በትግራይ ያለውን ሁኔታ ያባብሱታል እንጂ አያቃልሉትም ሲል ክፉኛ ተችቷል። (ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ!)
ፅሁፉን ከትናንት በስቲያ በመስቀል አደባባይ ከተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ በተወሰደ ምስል አጅቦ ያቀረበው ኡጋንዳዊው ጋዜጠኛ፤ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ለአገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፋቸውንና ለመግለፅ ወደ መዲናዋ አደባባይ በመግለፅ ሃሳቡን ይጀምራል።
ብዙዎች የተለያዩ መፈክሮችን ይዘው መውጣታቸውን በመጥቀስም፤ ሰልፈኞቹ ለጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድና ለመከላከያ ሰራዊቱ ውዳሴና አድናቆት ማዝነባቸውን አመልክቷል። የነፃነት ዜማዎችን በማሰማትም፤ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት እንዲታቀቡ መጠየቃቸውን ጽፏል-ጋዜጠኛው።
“ለትግራይ ነፃ አውጭ ግንባር አዲስ ለሆናችሁ” በማለትም፣ ስለ ታጣቂው ቡድኑ ታሪካዊ አመጣጥ ጭምር ለማስተዋወቅ ይሞክራል። ህውሃት በ1970ዎቹና 80ዎቹ ከደርግ ወታደራዊ አገዛዝ ጋር ይፋለሙ ከነበሩ በርካታ ታጣቂ ቡድኖች መካከል አንዱ እንደነበር ያወሳል። ቀንደኛ የኮሙኒስት ርዕዮተ ዓለም አቀንቃኝ እንደ ነበረ በመጥቀስም፤ የመጨረሻ ግቡ ነፃዋን ትግራይ መመስረት ነበር ይላል - ጋዜጠኛው።
የደርግ ወታደራዊ አገዛዝ መውደቅን ተከትሎ፣ ህውሃት ከሌሎች ብሄር ተኮር ፓርቲዎች ጋር በመጣመር፣ ኢህአዴግን መስርቶ፣ አገሪቱን ለ27 ዓመታት መግዛቱን ያወሳል።
በህወኃት መራሹ የ27 ዓመታት የሥልጣን ዘመንም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ለፖለቲካዊ አፈና እንዲሁም ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መገለል መዳረጋቸውንም ያትታል።
ሆኖም መላ አገሪቱን ከናጠ ህዝባዊ አመፅና በገዢው ፓርቲ ውስጥ ለሁለት ዓመት ገደማ ከተደረገ ውስጣዊ ትግል በኋላ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በመጋቢት 2010 ዓ.ም ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ይጠቁማል።
ኡጋንዳዊው ጋዜጠኛ እንደሚለው፤ የለውጡ አመራር ስልጣን ላይ መውጣቱን ተከትሎ፣ ጥልቅ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሪፎርም ተግባራዊ መደረጉን ይገልጻል። የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር ከተገበራቸው ሪፎርሞች መካከልም ዋነኞቹን ያነሳል። መንግስት የፖለቲካ እስረኞችንና ጋዜጠኞችን ከእስር መፍታቱን በስደት ላይ ለነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ታጣቂ ቡድኖች ወደ አገር ቤት ገብተው በሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲሳተፉ ጥሪ ማድረጉንም ያትታል።
አዲሱ የለውጥ አመራር አንዳንዶች በተሳሳተ መንገድ እንደሚወነጅሉት፤ በህወሃት ቡድን ላይ ምንም ዓይነት የበቀል እርምጃ እንዳልወሰደ ፀሃፊው ይሞግታል። ሆኖም ድንገት ከእጃቸው ባመለጣቸው ስልጣንና ምቾት እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪነት ውስጣቸው የበገነው ቀንደኞቹ የህወሃት አመራሮች ከእነ ቡድናቸው ራሳቸውን አግለው መቀሌ መከተማቸውን ከትቧል።
ከዚያም ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የተከሰቱ ግጭቶችንና ሁከቶችን በማቀድና በማስፈፀም ጭምር በእጅጉ መሳተፋቸውን ያትታል።
የህወሃት ቡድን እንደ ወትሮው ስልጣን ይዞ መምራቱን ካልቀጠለ፣ በሚሊዮኖች የንፁሃን ህይወት ኪሳራ አገሪቷን በነውጥ ለማናጋት ዝግጁ መሆኑን ለዓለም ማሳየቱን ያትታል- ኡጋንዳዊው ጋዜጠኛ። እንደውም የህወሃት አመራሮች፤ የበላይነታቸውን ለማስቀጠል በሚያደርጉት ጥረት እንቅፋት ከገጠማቸው ወደ ጦርነት እንደሚገቡ ለውጭ አገራት ቲፎዞዎቻቸው በጉራ ይነግሯቸው እንደነበር ትዝብቱን ይገልጻል።
በአንፃሩ ጠ/ሚኒስትሩና መንግስታቸው በትግራይ አንዲትም የጥይት ድምፅ መስማት እንደማይፈልጉና ለዘመናት የተሰቃየው የትግራይ ህዝብ የሚያስፈልገው ሰላምና  ልማት እንጂ ጦርነት አለመሆኑን በተደጋጋሚ መግፃቸውን ጽፏል። እንዳለመታደል ሆኖ ግን ከረቡዕ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በኋላ ግን ሁሉም ነገር እንዳልነበረ መሆኑን ይጠቁማል።
“በትግራይ የተከሰተው አሳዛኙ ጦርነትና ሰብአዊ ቀውስ የፌደራል መንግስቱ፣ የህዝብና የዐቢይ አህመድ ፍላጎት አልነበረም፤ የህወሃት ቡድን በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ በሰነዘረው  ጥቃት አስገዳጅነት የተፈጠረ ነው እንጂ” ይላል።
 ለመሆኑ ህወሃት ጥቃቱን የሰነዘረው ለምን ዓላማ ነበር? ለሚለውም ጋዜጠኛው መልስ ይሰጣል። የህወሃት ዓላማ በክልሉ ይገኝ የነበረውን ከ80 በመቶ በላይ የመከላከያ ንብረት የሆነ የጦር መሳሪያ ለመዝረፍም ከዚያም የአገሪቱን መንግስት በሃይል ለመለወጥ ነበር በጠመንጃ አፈሙዝ።
“በዓለም ላይ የትኛውም አገር ሆነ መንግስት ይህን ዓይነቱን እርምጃ አይፈቅድም፤ ምናልባት ከተፈጸመም እንኳ የማያዳግም እርምጃ ነው የሚወስደው” ፀሃፊው እንደሚለው።
“ለፌደራል መንግስቱ ፈጣን ምላሽና ለውጤታማው የህግ ማስከበር ዘመቻ እንዲሁም ለህዝቡ  ድጋፍ ምስጋና ይግባቸውና፤ በህወሃት ቡድን ተደቅኖ የነበረው አደጋ ወይም ብሄራዊ ስጋት በ3 ሳምንታት ውስጥ ከሽፏል- ሁሉም የነፃ አውጭው ቡድን አመራሮች አንድም ተገድለዋል አሊያም ተይዘዋል ወይም ደግሞ በየዋሻው ውስጥ ተሸሽገዋል” ሲል ፅፏል- ጋዜጠኛው።
ከዚያን ጊዜ አንስቶ ሚዲያውና ሰብአዊ ድርጅቶችን ጨምሮ ዓለማቀፉ ማህበረሰብ በትግራይ የተከሰተው አስቀያሚ ሁነት በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የተቀናበረ የሚያስመስል ተረክ መፍጠራቸውን ይገልጻል በፅሁፉ።
በርካታ ዓለማቀፍ ሚዲያዎች የፌደራል መንግስቱ በትግራይ ክልል መደበኛ ህይወትን መልሶ ለማስፈን የሚያደርገውን ጥረት ለማኮሰስ በሚመስል እርምጃ፣ በዘፈቀደ መያዝና መታሰር እንዲሁም “ለዘር ማጥፋት የቀረበ” በሚል የሚጠቅሱት ወንጀል፣ በዐቢይ አስተዳደር መፈፀሙን ሲያስተጋቡ ነበር ብሏል።
ውንጀላው ግን ሃሰተኛና የታጣቂውን ቡድን አጀንዳ ለማራመድ ያለመ ብቻ ነበር፤ ይላል- ፀሃፊው። የኢትዮጵያ መንግስት በክልሉ በህግ ማስከበር ዘመቻው ለተጎዱ ዜጎቹ ድጋፍ ለመስጠት አስፈላጊውን ጥረት ሁሉ ከማድረግ አልተቆጠበም። ባለሥልጣናት የተገኙ አሃዛዊ  መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ የፌደራል መንግስት ድጋፍ እስካሁን ድረስ በክልል ለሚገኙ ከ4.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በሁለት ዙር ተዳርሷል።
ዓለማቀፉ ማህበረሰብ የሰብአዊ ድጋፍ አንገብጋቢነትን ሳያሰልስ ቢያውጅም ቅሉ፤ ከዓለማቀፉ ማህበረሰብ ሁሉም አጋሮች ባለፉት 8 ወራት የተገኘው ድጋፍ ከሚያስፈልገው 30 ፐርሰንቱን ያህል ብቻ ነው።
የሰብአዊ ድጋፉን የአንበሳ ድርሻ 70 ፐርሰንት ሲሸፍን የቆየው የፌደራሉ መንግስት መሆኑ ይታወቃል። እንዲያም ሆኖ ህወሃት የዓለማቀፍ ማህበረሰቡን ትኩረት ለማግኘት በእጁ ያለውን  ስልት ሁሉ ከመጠቀምነ ወደኋላ እንደማይል ሊጤን ይገባዋል የሚለው ፀሃፊው፤ እነዚህም ሰብአዊ እርዳታዎችን ማገድ፣ አርሶ አደሩ እንዳያርስ መከልከል፣ የሰብአዊ ድጋፍ ሰራተኞችን መግደልና መከላከያውን ለማጥቃት ሲቪሎችን በሽፋንነት መጠቀምን ይጨምራሉ-ብሏል።
“የዛሬው ሰላማዊ  ሰልፍ (ሐሙስ በመስቀል አደባባይ የተደረገው) የኢትዮጵያ ህዝብ በአገሪቱ አመራርና በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ያለውን እምነት በአፅንኦት ያስረገጠበት ነው” ሲልም ምስክርነቱን ሰጥቷል።
 እውነት ለመናገር በርካታ ታዋቂ ዓለማቀፍ ሚዲያዎች በቅርቡ የፌደራል መንግስት ስለወሰደው የተናጥል ተኩስ አቁም እርምጃ ሃሰተኛ ዘገባ ለማቅረብ መምረጣቸው አስገርሞኛል። የታጣቂውን ቡድን የአሸባሪነት ተግባራት ለማራመድ በያዙት አጀንዳ፤ የኢትዮጵያ ጦር  ከመቀሌ የወጣው ተሸንፎ ነው ሲሉ አስተጋብተዋል- ሲል ትዝብቱን አስፍሯል።
እውነቱ ግን ሌላ ነው። ይሄ የተደረገው ሆን ተብሎ በዋናነት መላውን የትግራይ ህዝብ ለመጥቀም ታስቦ ነው-የሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልገው ወገን ሁሉ እንዲዳረስና አርሶ አደሩ የክረምቱን ወቅት ተጠቅሞ የእርሻ ሥራውን ያለምንም ስጋት እንዲያከናውን ለማስቻል እንደሆነ መሆኑን ያትታል - ፀሐፊው።
የህወሃት ቡድን ብሄራዊ ስጋትነቱ መከኮላሸቱንና የኢትዮጵያ ሰራዊትን የመዋጋት አቅምም እንደሌለው ይጠቁማል።
የኡጋናዳው ጋዜጠኛ ኩንጉ አል-ማሃዲ አዳም ፅሁፉን የሚቋጨው ጠንካራ መልዕክት በማስተላለፍ ነው። እንዲህ ይላል፡-
“ዓለማቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል መደበኛ የተረጋጋ ህይወት ማስፈን እንዲችል ዕድልና ድጋፍ መስጠት ይገባዋል፤ ምክንያቱም አቅሙ አለው፤ ያንንም በተግባር አሳይቷል።
ሃቁን ማዛባትና አሳሳች ሪፖርቱ ማቅረብ እንዲሁም-የኢትዮጵያ መንግስትን በሃሰት መወንጀልና በትግራይ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ በሚዲያ ወገናዊነት ማሳየት፤ ችግሩን አይቀርፈውም፤ ይልቁንም ያባብሰዋል እንጂ።”
ማስታወሻ፡- (ፀሃፊው ለአፍሪካ ወቅታዊ ጉዳዮች ጥልቅ ፍላጎትና ስሜት ያዳበረ ኡጋንዳዊ ጋዜጠኛ ነው።)Read 1593 times