Sunday, 25 July 2021 00:00

“ማኪያቶ! ያውም በቅዳሜ ምድር!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው...ነጻ ገበያ የሚለውን ነገር አስረዱን እንጂ! ግራ ገባና....በየቀኑ በሚባል ደረጃ እንደተፈለገው ዋጋ እየተቆለለ እኮ ግራ ገባን!
“እነኚህ ሰዎች እኮ ጨርቃችንን ሊያስጥሉልን ነው!”
“እነማንን ማለትህ ነው?”
“ነጋዴው፣ ነጋዴው ነዋ! እንደው ትንሽ እንኳን ሰብአዊነት ያልፈጠረባቸው! ሁሉም ነገር ነጋ መጨመር ነው፣ ጠባ መጨመር ነው! እያሳቀቁን ከሰውነት ውጭ አደረጉን እኮ!”
“እንግዲህ ምን ይደረግ ብለህ ነው... አቅም የሌለው ህዝብ ያው መነጫነጭ ብቻ ነው፡፡ ደጉን ጊዜ ያምጣው እንጂ ሌላ ምን ይባላል!”
“መንግሥት የማንን ጎፈሬ ያበጥራል! ህዝብ እንዲህ ጠዋት ማታ ሲያለቅስ የሆነ ነገር አያደርግም?”
“ለምሳሌ ምን ያድርግ?”
“ዋጋ ይቆጣጠርልና!”
“በአሁኑ ጊዜ እንደሱ ማድረግ ይቻላል ብለህ ነው?”
“ለምን አይቻልም! ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ መጠየቅ የሚቻለውን የክፍያ ጣራ ቢያስቀምጥልን እኮ ከዛች ውልፍት አይሉም ነበር፡፡ እነሱ አዳዲስ መኪናና ቤት ለመግዛት በፈለጉ ቁጥር የእኛ አንጀት በረሀብ መተጣጠፍ አለበት እንዴ!”
“ግን እኮ አሁን ነጻ ገበያ ነው ተብሏል፡፡”
“ቢሆንስ?”
“መንግሥት ዋጋ መወሰን ውስጥ አያገባውማ!”
“እንዲህ እያላችሁ ነው ለነጋዴዎቹ የልብ ልብ የምትሰጧቸው፡፡ ነጻ ገበያ ማለት ህዝብ ይዘረፍ ማለት ነው?!”
እናላችሁ...እነኚህ ዲክሺነሪ ለዲክሺነሪ የሚያሯሩጥንን ቋጥኝ የሚያካክሉ ቃላት ተዉንና በሚገባን ቋንቋ በነጻ ገበያ ስርአት ውስጥ ነጋዴው ማድረግና አለማድረግ የሚችላቸውን ነገሮች ንገሩንና እኛም እነሱን እያንጋጠጥን አሳልፈን መስጠታችንን እንተው፡፡
ስሙኝማ... ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... ይሄ የኑሮ መወደድ ወዳጅነቶችን ሁሉ እየተፈታተነ አይመስላችሁም! ልክ ነዋ... ከአብዛኞቹ ወዳጅነቶች ጀርባ ‘ብሪቱ፣ ነይ ነይ ብሪቱ’ አለቻ! የምንገባበዘው እኮ እሷዬዋ ነገር ስትኖር ነው፡፡ ‘ነገር’ አልኳት አይደል! እየከሳች፣ እየመነመች ስትሄድብኝ ምን ላድርግ ብላችሁ ነው! እና ‘የድሮ ናፋቂ’ ያስብልም አያስብልም... በሸመታ ደረጃ ትናንት ቢናፍቀን አይገርምም፡፡ አንዲት ስኒ ቡና ሀያ አምስት ሠላሳ ብር በምትባልበት ጊዜ እንዴት አድርገን ነው “ስማ፣ ለምን ቡና አልጋብዝህም...” ምናምን መባባል የምንችለው!
 “ምን ልታዘዝ?”
“አንድ የመጥበሻ ሹሮ፣ ሁለት በያይነቱ...አንድ ላይ አድርጊው፣ እሺ?”
“የሚጠጣስ...?”
“ሁለት አምቦ ውሃና ሁለት ለስላሳ፡፡”
ከአርባ አምስት ደቂቃ በኋላ ትሪዋም ጠርሙሶቹም ባዶ ሲሆኑ ሂሳብ ይመጣል፡፡ ያውም በሆነች ብጣሽ ወረቀት ነገር፡፡
“ሂሳቡ ስንት እንደሆነ ታውቃላችሁ?”
“ስንት ሆነ?”
“ሰማንያ ዘጠኝ ብር!”
“በለው! የዚህ የዚህ ሂልተን አንሄድም ነበር!” ቂ...ቂ...ቂ...
እናላችሁ... በሰማንያ ዘጠኝ ብር በ‘ግሩፕ’ ጥግብ እስኪሉ ድረስ መመገብና መጠጣት የሚቻልበት ዘመን በማለፉ ወዳጅነቶች እየሳሱ ነው ለማለት ያህል ነው፡፡ እናማ... የጋባዥና የተጋባዥ ግንኙነቶች በሳሱበት ቀደም ሲል በአለፍ አገደም ስንቀማምሳቸው የነበሩ ምግቦች መጠሪያዎች ቢጠፉን ምን ይገርማል! የአዳዲሶችንማ ተዉት! አይደለም ስማቸው የአጭር አጭር ልብወለድ የሚሉትን አይነት የረዘሙትን ያላቸውን... ‘እርጥብ’ ምን እንደሆነች ለማወቅ ስንት ጊዜ ፈጅቶብን ነው የደረስንባት!
“ስማ ቅዳሜ የት ነህ?”
“ከቤት ሳልወጣ እውላለሁ ብያለሁ፡፡”
“ቤት ምን ታደርጋለህ!”
“መጽሐፍ አነባለሁ፣ ሙዚቃ እሰማለሁ፣ ፊልም አያለሁ...”
“ለምን ወጣ ብለን ዞር፣ ዞር አንልም...”
“ብር አገኘህ እንዴ!?”
እንክት አድርጎ አግባብ ያለው ጥያቄ ነዋ! ልክ ነዋ... በባዶ ኪስ “ወጣ ብለን ዞር፣ ዞር እንበል...” ብሎ ነገር የለማ!
“እንትና ባር ማኪያቶ እጋብዝሀለሁ፡፡”
“ምን! ማኪያቶ! ያውም በቅዳሜ ምድር!”
ኮሚክ እኮ ነው፡፡ ቁርጥ ቤት የምንሄደው በአምስት ወር አንድ ቅዳሜ ያቺኑ ግማሽ ኪሎ ለሁለትም ለሦስትም ለመቃመስ ቢሆንም፣ “ያውም በቅዳሜ ምድር!” የምንላት ነገር አለች፡፡ ማን እጅ ይሰጣል!
“ስማ ፒዛ እንዴት እንደናፈቀኝ ልነግርህ አልችልም!”
“ታዲያ ምን ችግር አለው! ቅዳሜ በእኔ ወጪ የእንትናን ቤት ፒዛ እንበላለን፣” ይባል ነበር፡፡ ልክ ነዋ...ወዳጅነታችን በአብዛኛው ሆድን ባማከለ መልኩ የሚመሰረት ነዋ፡፡
አሁን ልጄ... አለ አይደል... “በእኔ ግብዣ...” ብሎ የሚጀምር ዓረፍተ ነገር መስማት የሚናፈቅ ነገር ሆኗል፡፡ “የእንትናን ቤት ፒዛ እንበላለን...” አይነቱን ነገርማ እርሱት፡፡ መጀመሪያውኑም... አለ አይደል...ኪሳችንን ስለምንተዋወቅ “ከቤት ውጣና ዞር፣ ዞር እንበል...” ብሎ ሙዚቃ እየቀረ ሳይሆን አይቀርም፤ ልክ ነዋ ...“ልጋብዝህ፣” የሚለውን ነገር መስማት አሪፍ የምንወደውን ሙዚቃ እንደመስማት ነዋ!
እናማ... ነጻ ገበያ ምን ማለት እንደሆነ ይብራራልንማ!
“የፈለግሁትን ያህል ዋጋ ብጨምር ማን ያገባዋል?” አይነት ‘ቢዝነስ ስትራቴጂ’ ምናምን ያለ ነው የሚመስለው፡፡ (እኔ የምለው...አንድ ሰሞን “ማን ይከለክላል ያለኝን ምናምን...” እያለች ስታንጎራጉር የነበረች ዘፋኝ ነበረች ወይስ የሆነ ነገር አምታትቼ ነው!)
እነእንትና... “ድሮ’ኮ በየሳምንቱ ነበር ብሩንዷችንን የምንከሸክሸው!” ብሎ ኖስታልጂያ ምናምን አያስፈልግም። ጊዜ አልፎበታላ! የብሩንዶን ምንነት አይደለም እኛ፣ ጁኒየር የሉካንዳ ቆራጮችም ማወቃቸውን እንጃ!
እናማ... ምን ለማለት ነው የሁሉም ነገር መወደድ እያራቆተ ያለው መሶባችንንና ጓዳችንን ብቻ ሳይሆን ወዳጅነታችንንም እያሳሳብን ነው፡፡ ተራራቅና!
ሞባይላችን ይጠራል፡፡ ቀደም ሲል በሳምንት ሦስቴ እናገኘው የነበረና ከጊዜ በኋላ እየተራራቅን የመጣነው ወዳጅ ነወ፡፡
“አንተ እዚህ ሀገር አለህ እንዴ?”
“አለሁ፣ የት እሄዳለሁ ብለህ ነው!;
“በጣም ጠፋሃ! መንገድ ላይም እኮ መገናኘት ጠፋ!”
“ዘንድሮ...ምን የሚያገናኝ ነገር አለ ብለህ ነው!”
እናላችሁ... ይሄ ቦተሊካም አይደል፣ አክቲቪስትነትም አይደል! ይሄ.. ማኪያቶ! “ያውም በቅዳሜ ምድር!” የሚለው የመገባበዣ ዘመን ትውስታ ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1391 times