Print this page
Saturday, 24 July 2021 00:00

በሀገር አንድነትና ሰላም ላይ የተደቀነውን አደጋ የመመከት ኃላፊነት በዋነኛነት የፌደራል መንግሥቱ ነው!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 (ከኢዜማ የተሰጠ መግለጫ)


             መንግሥት በትግራይ ያለው ግጭት ቆሞ ለሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ የተሻለ ሁኔታ ለመፍጠርና ሌሎች ምክንያቶችን ጠቅሶ የተናጥል ተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ፣ ሰኔ 26 ቀን 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ባወጣው የቢሆንስ ትንተና ሊሆን ይችላል ብለን ያስቀመጥነው ሁለተኛው ቢሆንስ (Scenario)፣ መንግሥት በትግራይ ክልል የተናጠል ተኩስ አቁም ካወጀ በኋላ የትግራይ አማጺዎች ግጭቱን ለማስፋት የሚያደርጉት ሙከራ ቀጥሎ ግልፅ አሸናፊ የማይኖርበት ሁኔታ ይከሰታል የሚል ነበር። ይህም ከቀጠለ በክልሉ ሕግና ሥርዓትን ማስከበር አዳጋች መሆኑ የሚፈጥረውን አጋጣሚ በመጠቀም ዘረፋዎች ሊበራከቱ እንደሚችሉ፣ የእለት እርዳታ የሚያስፈልጋቸው የክልሉ ነዋሪዎች በሚፈለገው ደረጃ እርዳታ ሳያገኙ ቀርተው ለከፍተኛ አደጋ ሊጋለጡ እንደሚችሉ፣ መሰረታዊ ለኑሮ የሚያስፈልጉ አገልግሎቶችና ግብዓቶች (የውሃ፣ የመብራት፣ ህክምና) ማግኘት የማይቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር የሚችልበት ዕድል ከፍተኛ በመሆኑ የክልሉ ሕዝብ ለከፍተኛ ችግር የሚጋለጥበት ሁኔታ ሊበራከትና ለረጅም ጊዜ ምንም ዓይነት አስተዳደራዊ አገልግሎት ሊያገኝ የማይችልበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችልና የዚህ ዓይነት የማያቋርጥ ግጭት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ብዙ ችግሮችን ስቦ በማምጣት (ኢንቬስትመንት ይቀንሳል፤ ቱሪዝም ይቀንሳል፤ በዚህም የሥራ አጥ ቁጥር ይጨምራል)፣ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችም አለመረጋጋትን ያስከትል ይችላል የሚል ትንተና አስቀምጠን ነበር። በትንተናችን ውስጥ ይህ ቢሆንስ (Scenario) የመሆን ዕድሉ ከሌሎቹ የበለጠ መሆኑን ጠቅሰን፣ በክልሉና ባጠቃላይ በሀገራችን ከብሔር ፖለቲካ ጋር ተያይዞ የመጣውን አደጋ በዘላቂነት የማይፈታ፣ ሀገሪቱን ቀስ እያለ ውስጧን እንደሚበላ በሽታ ከመግደሉ በፊት መፍትሄ የሚፈልግ እንደሆነ ገልፀን ነበር። በተጨማሪም በዚህ ሁኔታ ውስጥ መረጋጋትን ማስፈን ስለማይቻል የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ወደ ከፍተኛ ግጭት ማምራቱ እንደማይቀር በትንታኔያችን ውስጥ አስቀምጠን ነበር።
የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በይዞታው ስር የነበሩ ቦታዎችን ለቆ ከወጣ በኋላ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ያስተዋልነው እንቅስቃሴ በቢሆንስ (Scenario) ትንተናችን ውስጥ ከሁሉም የተሻለ የመከሰት ዕድል አለው ብለን ያስቀመጥነው ሁለተኛው ቢሆንስ (Scenario) እውን እየሆነ እንደሆነ የሚያመላክት ነው።
በእርግጥ ከላይ በጠቀስነው ትንተናችን ውስጥ ሕወኃት የሚያደርሳቸው ትንኮሳዎች በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት እየተመከቱና እየከሸፉ ሊሄዱ ይችላሉ የሚል ግምታችንን ብናስቀምጥም፣ በተግባር ያየነው ግን የፌደራል መንግሥት ሕወኃት ግጭቱን ለመቀጠል የወሰዳቸውን እርምጃዎች በግንባር ቀደምነት አመራር እየሰጠ ለማክሸፍ ከመሞከር ይልቅ ግጭቱን በክልሎች መካከል ያለ ግጭት እስኪመስል ድረስ የወሰደው ግልፅ ያልሆነ አቋም እጅግ አስደንጋጭ ሆኖ አግኝተነዋል።
ከዚህም በላይ ግጭቱን በተመለከተ በፌደራል መንግሥቱ በኩል የሚወሰዱ እርምጃዎች የተጣደፉና በቅጡ ያልታሰበባቸው መምሰላቸው፣ በአጭር ጊዜ ከሕወኃት የተደቀነውን አደጋ በማንኛውም መንገድ ከማክሸፍ ባለፈ እርምጃዎቹ ለሀገራችን ሰላምናና አንድነት በዘላቂነት የሚኖራቸውን አንድምታን ያልገመገሙ ስለመሆናቸው አመላካች ሆነው አግኝተናቸዋል።
መንግሥት የሚወስዳቸው እርምጃዎችን በተመለከተ ጊዜውን የጠበቀና ትክክለኛ መረጃ ለሕዝብ ባለማድረሱ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ መደናገጥ ከመፍጠሩም ባለፈ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸር ምክንያት ሆኗል። በተጨማሪም ሕወኃት ያደረሳቸውን ወንጀሎችና የሚፈጽማቸውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ከተራ ክስ ባለፈ በተጨባጭ ማስረጃዎች አስደግፎ ለዜጎችና ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ እንዲደርስ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ክፍተት እየተስተዋለ ይገኛል። እነዚህ ክፍተቶች በጊዜ መፍትሄ ካልተበጀላቸው ችግሩን የበለጠ እያባባሱት እንደሚሄዱ እናምናለን።
መንግሥት በተጨባጭ ማስረጃዎች ላይ ተመስርቶ ለሕወኃት የሚደረግ ማንኛውንም ዓይነት ድጋፍ ለማስቆምና ተጠያቂነትን ለማስፈን ያለበትን ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ የምንደግፍ ቢሆንም፣ በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች ሕወኃትን ትደግፋላችሁ በሚል ምክንያት የሚወሰዱ እርምጃዎች ማስረጃ ላይ የተመሰረቱ ከመሆን ይልቅ እንዲሁ በጅምላ የሚወሰዱ መሆናቸው የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የሚጋፉና በትግራይ ያለውን ችግር የበለጠ የሚያወሳስቡ ድርጊቶች ናቸው። ለአብነት
በአዲስ አበባ ከተማ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ብቻ በተመሳሳይ ወቅት ቢያንስ 60 የንግድ ተቋማት/ሱቆች ከግጭቱ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ታሽገው ላለፉት ሁለት ሳምንታት ተዘግተው ቆይተዋል። ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርስ እንግልት፣ ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ እስርና ጥቃት በአፋጣኝ መቆም እንደሚገባው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን
ሐምሌ 8 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ መጠየቁ ይታወሳል። ከላይ የተጠቀሱትን መሰረት በማድረግ የሚከተሉት ምክረ ሀሳቦች ተግባራዊ እንዲደረጉ
እንጠይቃለን፥
1. በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች የሚገኙ የፀጥታ አስከባሪዎች ሕወኃት የደቀነው አደጋን ለማክሸፍ እያደረጉ ያሉትን መረባረብ በከፍተኛ አክብሮት እናደንቃለን። ሕወኃት የፌደራል መንግሥቱን በበላይነት ይቆጣጠር በነበረበት ጊዜ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ላይ በሙሉ ግፍ ሲፈጽም እንደነበረ ሁሉ አሁንም የደቀነው አደጋ በሀገር አንድነትና ሰላም ላይ እንጂ በአንድ ወይንም በጥቂት ክልሎች ላይ ብቻ ያነጣጠረ እንዳልሆነ በመረዳት አደጋውን ለመከላከል የሚወሰደው እርምጃ አንድ ወጥ የዕዝ ሰንሰለት ኖሮት በፌደራል መንግሥትና በኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት አመራር ሰጪነት ብቻ እንዲወሰድ፤
2. በትግራይ ክልል ያለውን ችግር አሁን ከፊታችን ሕወኃት ከደቀነው አደጋ እንፃር ብቻ በማየት ሕወኃትን ማሸነፍን ብቻ ዓላማ ያደረገ የአጭር ጊዜ ስልት ይዞ ከመንቀሳቀስ ባለፈ በዘላቂነት ክልሉ ወደተረጋጋ ሰላምና ዜጎች ወደ መደበኛ ሕይወታቸው ሊመለሱ የሚችሉበት እንዲሁም ግጭቱ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተቋጭቶ የሀገር ህልውና እና
አንድነትን በዘላቂነት ማረጋገጥ የሚቻልበት ስልት የአካባቢውን ተወላጆች በማሳተፍ እንዲነደፍና ተግባራዊ እንዲደረግ፤
3. አሁን ያለው ግጭት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያበቃና ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ በትግራይ ክልልም ሆነ በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች የምትገኙ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ልሂቃን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የምታስፈልጉበት ወቅት ላይ መሆናችሁን ተረድታችሁ የሚጠበቅባችሁን ኃላፊነት እንድትወጡ፤
4. የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ድጋፍ እንዲደርሳቸው የሚደረገው ጥረት አሁን ከምንዜውም በላይ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ በክልሉ ለሚኖሩ ዜጎች እንዲዳረስ የሚያደርገውን ጥረት በግልፅ እንዲያሳውቅ፤ እንዲሁም በዚህ ተግባር የሚሳተፉ የሰብዓዊ ድርጅቶች በግልፅነት እንዲንቀሳቀሱ ተገቢው ክትትል እንዲደረግ፤
5. የተለመዱ መንግሥትን የሚያሞግሱ የፕሮፓጋንዳ ሥራዎችን እየደጋገሙ ሕዝብን ከማሰልቸት ይልቅ መንግሥት የወሰዳቸውን እርምጃዎች በተመለከተ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ለሕዝብ እንዲደርስ እንዲደረግና ሕወኃት የሚፈፅማቸውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችና ታዳጊዎችን በወታደርነት መመልመልና በጦርነት ማሳተፍን የመሳሰሉ ወንጀሎችን በተገቢው ፍጥነት በተጨባጭ ማስረጃዎች እያስደገፉ ይፋ የማድረግ ሥራ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሠራ፤
6. ዜጎች ለሕወኃት የሚደረግ ማንኛውም የሞራልም ሆነ ቁሳዊ ድጋፍ በሕዝብ ሠላም፣ በሀገር ደህንነትና ሕይወቱን ለመስዋዕትነት አዘጋጅቶ በተሰለፈው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ላይ የሚደረግ ክህደት መሆኑን በመረዳት ከተመሳሳይ ድርጊቶች እንዲታቀቡ፤
7. ሕወኃትን ደግፋችኋል በሚል በጅምላ የሚወሰዱ እርምጃዎች ባስቸኳይ እንዲቆሙና እስካሁንም በዚህ መልኩ የተወሰዱ እርምጃዎች ላይ አፋጣኝ ማጣራት ተደርጎ እርምት እንዲወሰድ እንዲሁም አሁን ያለውን ሁኔታ እንደ አጋጣሚ በመጠቀም የግል ጥቅም ለማግኘት ዜጎች ላይ እንግልት የሚፈፅሙ የመንግሥትና የፀጥታ ሠራተኞች ላይ አስፈላጊው ማጣራት በአስቸኳይ ተደርጎ የማያዳግም ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ፤በመጨረሻም የሀገራችን ሰላምና አንድነት በዘላቂነት ተረጋግጦ፣ የሁሉም ዜጎች መብት እኩል የሚከበርበትና እኩል ዕድል የሚሰጥበት እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ሁላችንም የምንችለውን ሁሉ የምናዋጣበት አሳሳቢ ወቅት ላይ እንዳለን እያስታወስን፣ ሁላችንም ኃላፊነታችንን ከምር ወስደን እንድንወጣ እናሳስባለን።
ሐምሌ 10 ቀን 2013 ዓ.ም


Read 1182 times
Administrator

Latest from Administrator