Friday, 30 July 2021 00:00

በ10 ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የጤና ባለሙያዎች የኮሮና ክትባት አላገኙም

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   67.6 በመቶ ህንዳውያን ኮሮናን የመከላከል አቅም አዳብረዋል ተባለ


           የጤና ባለሙያዎች በዓለማችን የኮሮና ክትባት ስርጭት ቅድሚያ ይሰጣቸዋል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ በ10 ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የጤና ባለሙያዎች የመጀመሪያውን ዙር ክትባት እንኳን እንዳልተከተቡ ቢቢሲ ባወጣው ዘገባ ገልጧል፡፡
27 ሚሊዮን የጤና ባለሙያዎችን በአባልነት የያዘው ኢንተርናሽናል ካውንስል ኦፍ ነርስስ የተባለ አለማቀፍ ቡድን ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ የጤና ባለሙያዎች ለቫይረሱ የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ እንደመሆኑ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንደሚከተቡ የአለም የጤና ድርጅትና መንግስታት በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቢቆዩም በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩት ግን አሁንም መከተብ አልቻሉም፡፡
የአለም የጤና ድርጅት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በመላው አለም በየቀኑ በአማካይ 200 ያህል የጤና ባለሙያዎች በኮሮና ሳቢያ እንደሚሞቱ መግለጹን ያስታወሰው ዘገባው፣ መንግስታት ለዚህ አደገኛ ክስተት ትኩረት አለመስጠታቸው የሚያሳዝንና እጅግ አደገኛ መሆኑን የኢንተርናሽናል ካውንስል ኦፍ ነርስስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆዋርድ ካተን መናገራቸውን አመልክቷል፡፡
በአለም የጤና ድርጅት የአፍሪካ ቢሮ በአህጉሪቱ በሚገኙ 38 አገራት ውስጥ 2.4 ሚሊዮን ያህል የጤና ባለሙያዎች የተለያዩ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን መውሰዳቸውን እንዳስታወቀ የጠቆመው ዘገባው፣ ሁሉም የአፍሪካ የጤና ባለሙያዎች ሁለት ዙር እንዲከተቡ ተጨማሪ 66.2 ሚሊዮን ክትባቶች ያስፈልጋሉ መባሉንም አስረድቷል፡፡  
የአለም የጤና ድርጅት በአለማችን በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ለሞት የተዳረጉ የጤና ባለሙያዎች ቁጥር ከ115 ሺህ በላይ ነው ማለቱን ያስታወሰው ዘገባው፣ ይህ ቁጥር ግን ከዚህም በእጅጉ ይበልጣል ተብሎ እንደሚገመትና በአሁኑ ወቅት በመላው አለም የጤና እንክብካቤ የሚሰጡ ባለሙያዎች ቁጥር 135 ሚሊዮን ያህል  እንደሚደርስም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜና ደግሞ፣ በህንድ የተሰራ አንድ ጥናት ከአጠቃላዩ የአገሪቱ ህዝብ 67.6 በመቶ ያህሉ በኮሮና ቫይረስ በመጠቃታቸው ወይም ክትባት በመውሰዳቸው ሳቢያ ሰውነታቸው የኮሮና ቫይረስን የመቋቋም አቅም እንዳዳበረ ማረጋገጡን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
በአገሪቱ የተሰራው ይህ ብሔራዊ ጥናት በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ቫይረሱን የመቋቋም አቅም ማዳበራቸው ቫይረሱ ምን ያህል በማህበረሰብ ደረጃ እንደተስፋፋ ያመለክታል ማለቱን የጠቆመው ዘገባው፣ ጥናቱ ከተሰራባቸው ሰዎች መካከል 62.2 በመቶ ያህሉ የኮሮና ክትባት አለመውሰዳቸውንንም አክሎ ገልጧል፡፡
በጥናቱ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሚገኙ 29 ሺህ ያህል ሰዎች መካተታቸውን የገለጸው  ዘገባው፣ 400 ሺህ ህንዳውያን የኮሮና ቫይረስን የመከላከል ተፈጥሯዊ አቅም እንዳላዳበሩና ለሶስተኛ ዙር የወረርሽኙ ማዕበል የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍ ያለ እንደሆነ አመልክቷል፡፡ በአገረ ህንድ ባለፈው ጥር ወር ላይ በተሰራ ተመሳሳይ ጥናት ኮሮና ቫይረስን የመቋቋም አቅም ያዳበሩ ሰዎች 24 በመቶ ያህሉ ብቻ እንደነበሩም ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 6533 times