Print this page
Thursday, 29 July 2021 00:00

በደቡብ አፍሪካው ሁከት 215 ሰዎች ሲሞቱ፣ ከ1.38 ቢ. ዶላር በላይ ወድሟል

Written by 
Rate this item
(0 votes)


               በደቡብ አፍሪካ ባለፉት ሳምንታት በተከሰቱት የሁከት፣ ዝርፊያና ብጥብጥ ድርጊቶች በድምሩ 215 ሰዎች ለሞት መዳረጋቸውና እስካሁን ባለው መረጃ በአገሪቱ የደረሰው የንብረት ውድመት ከ1.38 ቢሊዮን ዶላር በላይ ይደርሳል ተብሎ እንደሚገመት ዘ ናሽናል ድረገጽ ዘግቧል፡፡
የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ መታሰራቸውን ሰበብ አድርጎ በተቀሰቀሰውና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተስፋፋው ሁከትና ብጥብጥ ከ40 ሺህ በላይ የንግድ ድርጅቶች በቀጥታ ተጠቂ መሆናቸውንና ድርጅቶቹ ዘረፋ ቃጠሎና ውድመት እንደደረሰባቸው የአገሪቱ መንግስት ማስታወቁን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች 161 የገበያ አዳራሾችና መደብሮች፣ 11 መጋዘኖች፣ 8 ፋብሪካዎች፣ 161 የመጠጥ ማከፋፈያዎች ውድመት እንደደረሰባቸው የአገሪቱ መንግስት ባወጣው መረጃ ያስታወቀ ሲሆን፣ በሁከትና ብጥብጡ ተሳትፈዋል የተባሉ ከ2 ሺህ 500 በላይ ሰዎች መታሰራቸውንና በተወሰኑት ላይ ዝርፊያና ግድያን ጨምሮ የተለያዩ ክሶች መመስረታቸውንም አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ ተደራራቢ የሙስና ክሶች ተመስርተውባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኘው የ79 አመቱ ጃኮብ ዙማ የተመሰረቱባቸውን ክሶች በተመለከተ ችሎት ቀርበው ምላሻቸውን እንዲሰጡ በፍርድ ቤት ጥሪ ቢደረግላቸውም፣ በተደጋጋሚ በእምቢተኝነት ፍርድ ቤት ሳይገኙ በመቅረታቸው የአገሪቱ ከፍተኛ የህገ መንግሥት ፍርድ ቤት የ15 ወራት እስር ቅጣት እንደጣለባቸውና ለእስር መዳረጋቸውን የተቃወሙ ደጋፊዎቻቸው ያስነሱት ተቃውሞ ወደ ከፋ ሁከትና ብጥብጥ ማምራቱን ባለፈው ሳምንት መዘገባችን ይታወሳል፡፡


Read 2526 times
Administrator

Latest from Administrator