Monday, 26 July 2021 19:33

“ንባብና ክረምት” የመፃሕፍት አውደ ርዕይ ተከፈተ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 በዋልያ ኢቨንት  የተዘጋጀውና “ክረምትና  ንባብ” የሚል መሪ ቃል የተሰየመለት የመፃሕፍት አውደ ርዕይ ከትላንት በስቲያ ሀሙስ አራት ኪሎ በሚገኘው ኢክላስ ህንፃ ላይ ተከፍቷል። በመክፈቻ ስነ-ሥርዓቱ ላይ ደራሲ አበረ አዳሙ የሙዚቃ ተመራማሪ ሰርፀ ስብሀትና ደራሲ ዘነበ ወላ በእንግድነት መገኘታቸውም ታውቋል፡፡
ከሀምሌ 15 እስከ  ነሐሴ 10 ቀን 2013 ዓ.ም በሚዘልቀው በዚህ አውደ ርዕይ ላይ በሚኖሩት ቀናት የተለያዩ ኪነ-ጥበባዊና ስነ-ፅሁፋዊ ሥራዎች ይቀርባሉ ተብሏል።
ከትናንት በስቲያ በመክፈቻው ዕለትም “ስነ- ጥበብና ፍልስፍና” በሚል ርዕስ የፍልስፍና ምሁሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፣ ገለፃ ማድረጋቸው ታውቋል። በቀጣይም ከ10 በላይ ነባርና አዳዲስ ደራሲያን መፅህፍቶቻቸውን የሚያስመርቁ ሲሆን እንደ አንጋፋው ደራሲ ሀይለመለኮት መዋዕል ያሉ ደራሲያንም ልምዳቸውን ያካፍላሉ፣ በሌላ በኩል ዛጎል የመፅሐፍት ባንክ ከአንባቢያን ያሰባሰባቸውን መፅሃፍት የተለያዩ ገጠርና ከተማ ቤተ መፃፍህት ያስረክባል፣ “ግጥሞች ለአባይ” ልዩ የሥነ- ፅሁፍ ምሽት የሚካሄድም ሲሆን በዚህ ዝግጅት ከነባር ገጣሚያን መካከል የባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህንና የሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው ግጥሞች፣ ከአሁኖቹ ደግሞ የዶ/ር በድሉ ዋቅጅራና አንዱዓለም አባተ (የአፀደ ልጅ) ግጥሞች ይቀርቡበታል ተብሏል፡፡
ከእነዚህ ቀናት በአንዱ ደግሞ ወጣት ደራሲና የፍልስፍና ሰው መሃመድ አሊ ቡርሃን ዲስኩር የሚያሰማ ሲሆን የደራሲ መስፍን ሀብተ ማሪያም ሰባተኛ ሙት ዓመቱን ምክንያት በማድረግም በስራዎቹ ዙሪያ የዲላ ዩኒቨርስቲ መምህር እንግዳ ወርቅ እንድሪያስ ትንታኔ እንደሚያቀርቡም  ተገልጿል፡፡

Read 12642 times