Print this page
Monday, 26 July 2021 19:21

መንገጫገጩ የጨበጥነውን እንዳያስጥለን!

Written by  በላይነህ አሰጉ
Rate this item
(1 Vote)

 አድማስ ትውስታ
            እንዴት ያለ ሁኔታ ውስጥ ነበርን?
በዘር ተደራጅተን፣ በዘር ብልቃጥ ውስጥ ብቻ እንድናስብ እየተገደድን፣ አንዱ አንዱን በጎሪጥ እንዲያይ እየተደረገ 27 ዓመታትን አይኖር የለም ኖርነው። ገዢዎቻችን በቀደዱልን ቦይ ብቻ እንድንፈስ ማንቁርታችንን ተይዘን ይኸው 27 ዓመት ሞላን፡፡ በአንድ በኩል በዘር ተደራጁ እየተባልን፣ ለገዢዎቻችን የማይመች ሲሆን ደግሞ ማንነታችን እየተካደ፣ የአንድ ትውልድ ዕድሜ ባከነ፡፡
ሰብአዊ መብታችንን ተነፍገን፣ ስንበደል አቤት የምንልበት አጥተን፣ ከተራ የመንደር ዱርዬ የማይሻል ካድሬ እንደፈለገው ሲያደርገን ኖርን፡፡ ተበደልን፣ ተገፋን ብለን ስንጮህ፣ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ የተነሳ … እየተባልን በየእስር ቤቱ ታጎርን፣ ተደበደብን፣ ተሰቃየን ተገደልን፡፡ የበደል ጩኸቴን ላሰማ ብሎ አደባባይ የወጣ ስንቱ ዜጋ፣ ዕድሜና ፆታ ሳይለይ፣ በየአደባባዩ በአልሞ ተኳሽ ጥይት ተነደፈ፡፡
የተያዘው መንገድ አያዋጣም፣ አገርንና ሕዝብን ይጎዳል ብሎ የተናገረ፣ የጻፈ ሁሉ አሸባሪ፣ የቀድሞው ሥርዓት ናፋቂ… እየተባለ በእስር ማቀቀ፡፡ ቤተሰቡ ለችግር ተዳረጉ፣ እምቦቀቅላ ሕፃናት ወላጆቻቸውን እያዩ በፍቅር እንዳያድጉ ተደረጉ፡፡
በሕገ መንግሥቱ ተፈቅዷል ብለው ፓርቲ ያደራጁ ወይ የይስሙላ ሆነው እንዲጮሁ ተደረጉ፣ አሊያም አሸባሪ እየተባሉ ተንገላቱ፣ ታሰሩ፣ ከአገር ተሰደዱ፡፡ ለይስሙላ በሚደረጉ ምርጫዎች እንኳን ሾልከው እንዳይወጡ የምርጫ ካርዱ እየተሰረቀ፣ እየተጭበረበረ፣ ኮረጆ እየተገለበጠ ሕዝብ የመረጠው ሌላ፣ መንግሥት ያወጣው ሌላ ሆኖ ኖርን፡፡
ይህ ሁሉ ችግር እያለ ትናንትና ቤሳ ቤስቲኒ ያልነበረው በዘሩ፣ በፖለቲካ ማንነቱ፣ በዘመድ አዝማድ ባለ ጊዜን እየተጠጋ፣ ፎቅ በፎቅ ሲሆን፣ ቪ8 ሲነዳ፣ ውስኪ በያይነቱ ሲያማርጥ፣ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ጥሮ ጣጥሮ የእለት ጉርሱን የአመት ልብሱን መሸፈን አቅቶት ኖረ፡፡ ሁለት አሃዝ ዕድገትም ተዘፈነለት፡፡    
 ዛሬስ ምን ላይ ነን?
ይህ አሰራር ያስመረረው ሕዝብ በየስፍራው ሲጮህ፣ ሲታገል፣ ሲወድቅና ሲነሳ የግፉ ጽዋ ሞልቶ ፈሰሰና ከተቃዋሚ ሳይሆን ከኢህአዴግ ከራሱ ውስጥ አበዛነው፣ ግፍ ናኘ፣ ሕዝብን አስመረርን፣ በዚህ መንገድ መቀጠል  አይቻልም የሚለው የእነ ዶ/ር ዐቢይ ቡድን ብቅ አለ፡፡ ገና እንደወጣ በርካቶች ለማመን ሁሉ ተቸግረው ነበር። እስካሁን ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂው መንግሥት ነው፤ የዜጎችን መብት ጥሰን ያለ ወንጀላቸው ለእስር ዳረግናቸው፣ መብታቸው ተረገጠ፣ ሕዝቡን ያስቆጣው ይኸ ስለሆነ ይቅርታ እንጠይቃለን።-- አሉ፡፡
የሕግ በላይነት መከበር አለበት፣ ሕግ ለሁሉም ዕኩል ስለሆነ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ሕግ አስከባሪዎች ጭምር ሕግን ማክበር ይኖርባቸዋል፣ አለበለዚያ ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡ -- ተባለ፡፡
ተቃዋሚ የሆነ አብዛኛው፣ አሸባሪ፣ ፀረ - ሰላም፣ ነውጠኛ እየተባለ የታሰረና የተሰደደ ሁሉ ተፎካካሪ እንጂ ተቃዋሚ አይደለም፣ የታሰረ ሁሉ ይፈታ፣ አገር ጥለው የኮበለሉ፣ የትጥቅ ትግል የጀመረ ሁሉ ይመለስና በሰላማዊ መንገድ ይታገል --- ቢባል ብዙዎቻችን ማመን አቃተን፡፡ ነገሩ በዓይናችን ስር ዕውን እየሆነ ሄደ፡፡ የተሰደደ ተመለሰ፣ የታሰረ ተፈቶ ከወገኑ ጋር ተቀላቀለ፡፡
እንደነ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ፣ አንዳርጋቸው ጽጌ ያሉ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው በሰላም ወደ አገራቸው ገብተው ሰላማዊ ትግል እንዲያደርጉ ተጋብዘው በክብር በአደባባይ አቀባበል ሲደረግላቸው አሳሪ፣ አፋኝ፣ ደመኛ አድርጎ ይቆጥር የነበረ እንዴት ይቻለው፡፡
በጦርነት ጠላትን እንጂ እርስ በርሳችን ተሸናፊና አሸናፊ ሆነን መኖር አንችልም። ሁላችንም ተሸናፊ ነው የምንሆነው። በሀሳብ እንታገል፣ እንደማመጥ፣ ሕዝብ የፈቀደውን በምርጫ ይወስን፡፡ ጥላቻን ቂም በቀልን እናስወግድ፣ ይቅር እንባባል፣ እንደመርና አገራችንን ትልቅ እናድርጋት አሉ፡፡ ተደርጎ በማይታወቅበት መልኩ ትናንትና ተገንጥላ፣ ከዚያም እንደገና ለአስከፊ ጦርነት ተዳርገን፣ ስንትና ስንት ወገን ያለቀባትን ኤርትራ “ወንድሞቻችን ናቸው” ብሎ በፍቅር ጋብዞ ያስማማ መሪ አገኘን፡፡
ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳንሆን የአፍሪካ ቀንድ በሞላ እንደመርና ትልቅ የሰው ኃይል፣ ሀብት፣ ውሃ፣ ነዳጅ ያላትን አንድ አገር መሥርተን ከልመና እንውጣ፡፡ አለበለዚያ ሁላችንም ደህይተን ቻይናን እርዳታ ለመለመን እንሰለፋለን አሉ፡፡ ይህን ስሰማ አንድ የዶጋሊ መቶኛ ዓመት ሲከበር የመጣ የደቡብ አፍሪካ ሰው ያሉኝን አስታወስኩ፡፡ ሰውዬው ሆሴ ጃፌ ይባላሉ፡፡ ዘራቸው ፖላንዳዊ ሲሆን ተወልደው ያደጉትና በዜግነትም ደቡብ አፍሪካዊ ናቸው፡፡ በደቡብ አፍሪካ ፀረ-ዘረኝነት ትግል በሚደረግበት ወቅት ፈረንጅ ሆነው ከጥቁሮቹ ጎን ተሰልፈው የኤኤንሲ አባል ሆኑ፡፡ በዚህ ምክንያት ዘረኛው መንግሥት ካገር አስወጥቷቸው ኢትዮጵያ መጥተው በመድኃኒዓለም ትምህርት ቤት የታሪክ መምህር እንደነበሩ ነግረውኛል። ከዚያ ወደ ውጭ ሄደው ኢጣሊያ ውስጥ ይኖሩ ነበር። ስለ ኢትዮጵያ ስለሚጽፉ በዶጋሊው መቶኛ ዓመት ክብረ በዓል እንዲሳተፉ ተጋብዘው መጡ፡፡
እኝህን ሰው፣ መሪያ ራይት የተባሉ የሶቪየት ህብረት ዜጋና ሀጋይ ኤርሊክ የሚባሉ እስራኤላዊ በኢትዮጵያ ውስጥ ይካሄድ የነበረውን የሰፈራና መንደር ምሥረታ እንዳስጎበኛቸው ተመድቤ አስር ቀን ያህል አብረን ዞረናል፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር ሆሴ ጃፌ ለእኔና ለሌሎች ታሪካቸውን ያጫወቱን። አንድ ቀን በጨዋታ መሀል፣ የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት ጉዳይ ተነሳና፣ እንግሊዞች የኢትዮጵያን ንጉሠ ነገሥት ደግፈው፣ ጣሊያኖችን ባስወጡበት ወቅት በደቡብ አፍሪካ ጋዜጦች በሞላ፡- «ጀግናው የእንግሊዝ ጦር ኢትዮጵያን ከጣሊያኖች ነፃ አወጣ» እያሉ ይጽፉ ነበር።
ታዲያ በዚያን ጊዜ «የእንግሊዝ ሠራዊት የመጣው ኢትዮጵያን ነፃ ለማውጣት ሳይሆን የራሱ ቅኝ ግዛት ለማድረግ ነው፡፡ ጦሩ ኢትዮጵያን ነፃ ለማውጣት ካሰበ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ጂቡቲና ሱማሊያ በአንድ ሰንደቅ ዓላማ ስር መሆን ይኖርባቸዋል” ብዬ ጽፌ ነበር፡፡ ምክንያቱም እነዚህ አገሮች በጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ፣ በጂኦ ፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ የተሳሰሩ ናቸው። ለየብቻቸው ከሆኑ ሁሌ ሲናቆሩ ነው የሚኖሩት፡፡ ስለዚህ በሆነ መልኩ በአንድ ሰንደቅ ዓላማ ስር ቢሆኑ ሁሉም ተጠቃሚ ይሆናሉ ሲሉ አጫወተውኝ ነበር። ይህንን ለብዙ ሰዎች አጫውት ነበረና ከጠቅላይ ሚኒስትራችን አፍ ይህንኑ ስሰማ ከልቤ ደስ አለኝ። አርቆ አስተዋይ መሪ ስለሰጠን ፈጣሪን አመሰገንኩ። ለወደፊቱም አያሳጣን፡፡    
ኢትዮጵያ በታሪኳ፣ እኛም በሕይወት ዘመናችን፣ እኔ ብቻ ማለት ባለፉት መቶ ዓመታት ኪሳራ እንጂ ትርፍ አላመጣምና አንድ መሪ ከሁለት የምርጫ ወቅት በላይ መሥራት የለበትም የሚል መሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንሰማ ንጹህ ልቦና ያለው ሁሉ እንደሚደሰት ይገባኛል፡፡
ተሸናፊ ወደ ከርቸሌ፣ በኋላ ደግሞ ቃሊቲ፣ ቂሊንጦ ወይም ወደ ሞት በሚመራባት አገር፤ ጥፋታችንን አምነን ይቅርታ ጠይቀን በሰላማዊ መንገድ ሀሳባችንን እንግለጽ ብሎ ለገደሉን፣ ለዘረፉን፣ ላዋረዱን ሁሉ ምህረት የሚያደርግ መሪ መጣ፡፡ ይህን ይመስላል የዛሬው የተስፋ ጭላንጭል፡፡
በምላሹስ  ምን እያደረግን ነው?
ለዚች ጽሑፍ ያነሳሳኝ ይህ ጭንቀት ነው፡፡ አልተመጣጠንም ወይስ የጠቅላይ ሚኒስትራችን አስተሳሰብ እጅግ እርቆብን መጨበጥ አቃተን? አትቃወሙ አልተባልን፣ ሀሳባችሁን በሰላማዊ መንገድ በማንኛውም መልኩ ግለጹ ነው የተባልነው። መንግሥትንም ይሁን የማንኛውንም ተፎካካሪ ፓርቲ መደገፍ አልተከለከልን፡፡ ታዲያ ለሃያና ከዚያ ለበለጠ ዓመታት፣ ሆን ተብለው፣ እንደ ፈንጂ የተቀበሩ ጥያቄዎችን በአንድ ጀንበር ካልፈታልን እያልን፣ በሰው አካልና ህይወት ላይ አደጋ የምናደርስ፣ ትምህርት ቤት፣ ክሊኒክ፣ ነገ ተጠያቂዎች ልናፈላልግ የምንችልበትን የመሥሪያ ቤት ሰነዶች፣ የእምነት ስፍራዎችን፣ የግለሰብ ንብረት የምንዘርፍና የምናቃጥል ምን ነክቶን ነው?
አንዳንዶቹ፣ በተለይ ሥልጣንን ተገን አድርገው እስኪበቃቸው የዘረፉ፣ የሰው ህይወትና ንብረት ያጠፉ፣ ይቅርታ ጠይቃችሁ ተደመሩ ቢባሉም ትናንትና እነሱ ቃላቸውን እያጠፉ ያሰቃዩ ነበረና እንደዚያ መስሏቸው ጎራ ለይተው፣ ቢቻል ወደ ሥልጣን እንመለሳለን ካልተቻለ ሥልጣን ላይ የወጡትን እናስወጣለን፣ መምራት አልቻሉበትም እናስብላለን ብለው፣ በራሳችን ገንዘብ ራሳችንን ለማመስ አሻጥረው መሸጉ፡፡ ይህን ማድረጋቸው አያስደንቀኝም፡፡ አስራ ሰባት ዓመት ተዋግተው፣ ተጎሳቁለው፣ ከሞት ተርፈው መጡ። ያልታሰበ አልጋ ላይ ወጡ፡፡ ተራው ሰው እንዴት እንደሚኖር እስኪረሱ ድረስ ተድላና ደስታ አራዣቸው። እንዴት ብለው ወደ ተራ ህይወት ይመለሱ? እንዴትስ ብለው ያንን ሁሉ ወንጀል በፈጸሙበት ህብረተሰብ መሀል ይኑሩ? ልዩነትን በኃይል እንጂ በፍቅር ፈቶ ለማያውቅ ይኼ ስብከት እንዴት ይዋጥለት፡፡ የሥልጣኑ መወሰድ አሁንም ህልም እንጂ እውን አይመስላቸውምና ወይ ከእንቅልፋቸው እስኪነቁ አሊያም ከመሸጉበት ጎሬ እስኪወጡ ማመሱን መረጡት፡፡ ካልበላሁ ጭሬ ላፍሰው ዓይነት ነው፡፡
እኛ ታዲያ ምን ነካን? ያደረጉብንን ሁሉ እያወቅን ባዘጋጁልን አሽኬላ ውስጥ እንዴት ብለን እንገባለን? ትናንትም ሆነ ዛሬ፣ ነገም አብረን የምንኖረውን ዜጋ፣ ጉሊት ቸርችራ የምታድረውን ምስኪን፣ ሕፃን ታቅፋ የተኛችን እናት፣ በሥራ ላሽቆ የተኛን አረጋዊ በአሰቃቂ ሁኔታ እንድንገድል የሚያስችለንን ሰይጣናዊ ሞራል ከየት አመጣን? በዓለም ላይ ቁልቁል የተሰቀለ የሰማሁት ሞሶሎኒ ብቻ ነበር፡፡ በሚገርም ሁኔታ አንድ ንጹህ ዜጋ ቁልቁል ተሰቀለ፣ እንደታረደ በግ። ምን እየሆንን ነው? ማንን ለማስደሰት ወይስ የማንን ዕዳ ለመክፈል። የአንድን ግለሰብ መብት ስንጋፋ፣ የእኛ  መብት ዜሮ እንደሚሆን ማወቁ ጥሩ ነው፡፡ ዛሬ ስንገድል ነገ እኛም ለመገደል ተራ እንደምንይዝ ብናስብ መልካም ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በእጅ የያዙት ወርቅ ሆኑብን? ጨርሶ አይመስለኝም፡፡ በየቤታችን ምን ያህል እንደምንሳሳላቸው፣ ምን ያህል እንደምንጨነቅላቸው፣ ለሁለት ቀን ድምጻቸውን ካልሰማን ምን ያህል ሀሳብ እንደሚገባን አውቃለሁ፡፡ እንዲያ ከሆነ ይህንን ለውጥ ለማደናቀፍ የሚፈልጉትን ወጊድ እያልን መዋጋት፣ ሥርዓት ማስያዝ እንጂ እንዴት ብለን ለሰላም የተዘረጋን እጅ ከሚነክሱ፣ ፍቅርን ከሚጠሉ፣ ይቅርታ አልዋጥ ካላቸው፣ ግጭትን፣ ጦርነትን፣ ጥላቻን፣ ጠብን፣ ብቀላን ከሚያቀነቅኑና ከሚወዱ ጎን ተሰልፈን የገዛ ወገናችንን እናሰቃያለን? ከእነዚህ ድርጊቶች የሚያተርፍ ሰይጣናዊ አዕምሮ ብቻ ነው፡፡
በርግጥ በሕይወት ዘመናቸው በሞላ ሳይቀድመኝ ልቅደመው እያሉ የኖሩ ናቸውና ፍቅርና ሰላም የሚሉት ነገር በዓይነ ህሊናቸው ዞሮምም አያውቅ። አከርካሪያቸውን ሰበርናቸው፣ ድባቅ መታናቸው፣ ደፈቅናቸው የሚል ዜማ እንጂ የፍቅር ስብከት ለእነሱ የባዕድ ዓምልኮ ነው። ትናንትና ጠላት ይሉት ከነበረ ፍቅር፣ ሰላም እንዴት ይግባቸው፣ አንፍረድባቸው፡፡ ያልተለመደ ስለሆነ አይዋጥላቸውም፡፡
በለውጥ ጊዜ በትንሹ መንገጫገጭ የተለመደ ነው፡፡ የእኛው ግን በዛ፣ ከልክ አለፈ፣ የጨበጥነውን የሚያስጥለን መሰለ። በዚህን ጊዜ ዶ̃ቻ/ ይሁኔ በላይ እንዳለው፤ ሰከን አርጎ መያዝ ነው የሚያዋጣን ብዬ ነበር፤ በዚሁ ጋዜጣ ላይ (አዲስ አድማስ ቅፅ 19 ቁጥር 956፣ ቅዳሜ ግንቦት 4/2010)፡፡ አሁንም ዶ̃ቻ! እላለሁ፡፡
ምክረ ሀሳብ ለለውጥ ኃይሎች
እናንተ ታጡታላችሁ ወይም ሌላም ሰው አልነገራችሁም ብዬ አይደለም። ብቻ እኔ የሚሰማኝን፣ ከጓደኛም ሆነ ከዘመድ የምናወራውን፣ ከዚህ በፊት ያለኝንም ልምድ አክዬ ባካፍላችሁ አይከፋም ከሚል ነው፡፡ ኢትዮጵያ በታሪክ እንዲሁም ከራሴ ልምድ ከማውቀው ከችግር ወጥታ የማታውቅ አገር ናት፡፡ ከውጭም ከውስጥም ስንጎሻሸም የኖርን ነን፡፡ የፍቅር ህይወት አልነበረበትም ማለቴ ግን አይደለም፡፡ እነዚያን ችግሮች እያለፈች የመጣችበት የራሷ በርካታ ልምዶች አሏት፡፡
ከእነዚህ አንዱ ጠላት ሲመጣ፣ ሽፍታ ሲያስቸግር የጎበዝ አለቃ መርጦ በእሱ ስር መሰለፍና አደጋውን መቋቋም ነው፡፡ ይህንን ልምድ በ1966 አብዮት ሲፈነዳ፣ እኔ ራሴ በነበርኩበት በጎፋ ተጠቅመንበታል። ህብረተሰቡ ተሰብስቦ አንድ ኮሚቴ አቋቋመ። አውራጃ ገዢውን ከቤታቸው እንዳይወጡ አድርገን፣ አስተዳደሩን ኮሚቴው እንዲመራ ተደረገ፡፡ የሕዝብ ንብረት እንዳይዘረፍ፣ በአካባቢው ረብሻ እንዳይነሳ፣ ሥርዓት እንዳይጠፋ ከፖሊስና ተባባሪያችን ከነበሩት የአውራጃው ዋና ጸሐፊ ጋር ሆነን እያስተባበርን ወደ ሁለት ወር ገደማ ቆየን። ከዚያ የልጅ እንዳልካቸው መንግሥት አብዮቱን ተቀላቀልኩ ያለው ወታደር ታማኝነቱን ሲገልጽለት በየአካባቢው የተቋቋሙት ሕዝባዊ ኮሚቴ የሚባሉት ከዛሬ ጀምሮ ፈርሰዋል፣ ፖሊስና ጦሩ እርምጃ እንዲወስዱ ታዘዋል ሲባል፣ የፖሊስ አዛዡ “የእንጀራ ጉዳይ ስለሆነ ከታዘዝን እርምጃ መውሰዳችን ስለማይቀር ኮሚቴው ሥራውን ቢያቆም ይሻላል” በማለት አማከሩንና ኮሚቴው ፈረሰ። የኮሚቴው መፍረስ ለአፍራሾቹም ሳይበጅ ቀረ እንጂ ለጊዜው ሠርቷል፡፡ ኢህአዴግ ሲመጣ ደግሞ  በኃላፊነት ላይ ያሉት ሁሉ ከአካባቢው ሲሸሹ፣ የጎፋ ሕዝብ ይህንኑ ዘዴ ተጠቅሞ ሰላሙን እያስጠበቀ ቆይቶ ከበርካታ ቀናት በኋላ የኢህአዴግ ጦር ሲገባ አስረክቧል፡፡
ይህንን ያመጣሁት አሁን ያለውን ሁኔታ ስመለከት በሆነ መልኩ ህብረተሰቡን አደራጅቶ ሁኔታዎችን ማረጋጋት ካልተቻለ፣ ችግሩ እየሰፋ ይሄዳል የሚል እሳቤ ስላለኝ ነው፡፡ ህብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም ማስጠበቅ ከቻለ፤
ሀ/ የለውጡ ኃይል ጊዜ አግኝቶ በጀመረው መንገድ ለመሄድ ፋታ ያገኛል፤
ለ/ አጋጣሚውን ተጠቅመው ከኛ በዘረፉት ገንዘብ እኛኑ አተራምሰው ለውጡን ለማጨናገፍ የሚሯሯጡትን በቅርበት መከላከልና መግታት ይቻላል ብዬ አምናለሁ፡፡
ሁለተኛው ምክሬ መቅደም መቻል ነው። ጪስ ባለበት እሳት አለና ሲቻል ጪሱ ከመውጣቱ በፊት ካልሆነም ገና ጪሱ ሲወጣ እዚያው ደርሶ ማጥፋት መቻል ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ከህብረተሰቡ ጋር መሥራት ወሳኝ ነው፡፡ የመንግሥት መዋቅሩ 27 ዓመት ሙሉ ሲዶለትበትና ሲሸረብበት የነበረ በመሆኑ ሙሉ እምነት ሊጣልበት አይችልም፡፡ ገና መዋቅሩ ጠርቶ በሙሉ ኃይሉ ለለውጡ መቆም እስኪችል ድረስ ጊዜ ይወስዳል፡፡
በዚያ ውስጥ የተደመሩ አሉ፣ ገና ጥርጣሬ ውስጥ ያሉ አሉ፣ የተጀመረው ለውጥ ጨርሶ የማይዋጥላቸው ሁሉ አሉ፡፡ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉንም በአንድ መልክ ከመፈረጅ ይልቅ በሚገባ አጥንቶ፣ በሚሆነው መልኩ ማደራጀት ያስፈልጋል። ይህን ለማድረግም ህብረተሰቡን፣ በየመሥሪያ ቤቱ ያለውን ሠራተኛ ጭምር ማደራጀትና እስከ ታችኛው የሥልጣን እርከን፣ ለለውጡ ማሰለፍ ለነገ የሚባል አይደለም፡፡ ለዚህም በህብረተሰቡ ውስጥ ምቹ ሁኔታ አለ ብዬ አምናለሁ። በየአካባቢያችን የተለያዩ ማህበራዊ ድጋፍ የሚሰጡ ዕድሮች፣ ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦች፣ ለለውጡ ቆርጠው የተነሱ ወጣቶች … በመኖራቸው፣ እነዚህን ለዚህ ቁርጥ ቀን በአግባቡ አደራጅቶ መጠቀም ይቻላል እላለሁ፡፡
ሦስተኛው ምክሬ፣ እኔ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አካሄድ ይጥመኛል፡፡ ግን ያንን እንደ ድክመት ቆጥረው የሚሯሯጡ ስላሉ መንግሥት፣ መንግሥትነቱን ማሳየቱ አስፈላጊ ነው፡፡ እንደከዚህ ቀደሙ በለው፣ መንጥረው ሳይሆን ጥፋት ሲፈጸም በጥፋቱ ልክ አፋጣኝ ውሳኔ መስጠት ያስፈልጋል። 27 ዓመት ሙሉ ሆን ተብሎ እርስ በርሱ የተተበተበ ሀገር አቀፍ ወደር የለሽ የጥፋት መረብ በወራት ቀርቶ በጥቂት ዓመታትም መፍታት አይቻልም፡፡
በአፋጣኝ ጥያቄያችን ካልተመለሰ ብለው አፍንጫ ሰንገው የሚይዙትን ሁኔታው ተጠንቶ እንደሚፈታ ማስረዳት፣ በአካባቢ ታዋቂ ግለሰቦችም አበክሮ ማስመከር፣ አሌ ብለው ለሌሎች መጠቀሚያ ሆነው የሚንቀሳቀሱትን የመንግሥት ክንድ ማሳየት ጥሩ ነው። በፍቅር ለመሳም የተጠጋን ከንፈር የሚነክሱትን ችላ ማለት፣ ነገ ምላስን ሊያስቆርጥ የሚችል አደጋን ስለሚያስከትል ሳይቃጠል በቅጠል ነው፡፡ ፍትሀዊነቱ ሳይጓደል፡፡
አራተኛውና የመጨረሻው ምክሬ፤ የችግሩን ቅርንጫፍ መቸፍቸፍ ሳይሆን ግንዱን መቁረጥ ነው፡፡ ቅርንጫፉ የተፈለገውን ያህል ቢቆረጥ፣ የዕለት እፎይታን ይሰጥ እንደሁ እንጂ ዘላቂ መፍትሄ አያመጣም፡፡ ለዚህ አንድ ምሣሌ ልጥቀስ። በአንድ ወቅት ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃ/ማርያም ለሥራ ጉብኝት ወደ ጋሞ ጎፋ ይሄዳሉ፡፡ ከጎበኟቸው ስፍራዎች አንዱ በወቅቱ በህብረት ሥራ ማህበር ተደራጅቶ የነበረውና ዛሬ በሙዝና በማንጎ ዛፍ የተሸፈነው ላንቴ አካባቢ ነበር፡፡ እዚያ እንደደረሱ የተለያዩ ካድሬዎችና በወቅቱ የክፍለ ሀገሩ የደርግ ተወካይ የሆኑት ስማቸው በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀው አሊ ሙሳ ነበሩ፡፡ ካድሬዎችም፣ አሊ ሙሳም እየተነሱ አካባቢው የኢጭአትና የመኢሶን መፈልፈያ እንደነበረ፣ ዛሬ እነዚህ ተመንጥረው ሰላም እንደሰፈነና ህብረተሰቡ ወደ ምርትና አብዮቱን ወደ መደገፍ እንደዞረ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በካድሬ ቋንቋ ይናገራሉ፡፡ በዚህን ጊዜ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ፤ እስኪ ከአገር ሽማግሌዎችም እንስማ ይላሉ፡፡ አንድ በንግግሩ አንጀታቸው ያረረና በድርጅታዊ ሥራ ያልተጀነጀኑ ሽማግሌ ይነሳሉ፡፡ እንዲህ በማለት ነበር ሁኔታውን የገለጹት፡-
በቀድሞ ጊዜ አንድ ግለሰብ አንዲት የወተት ላም ገዛ አሉ፡፡ ላሚቱም ወለደችና ወተት ትሰጣለች፣ ጥጃውም ያድጋል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ጥጃው ቀበኛ ይሆንና ልብስ መብላት ይጀምራል፡፡ ብዙ ልብስ በመብላቱ ተናደው ጥጃውን ገበያ አውጥተው ይሸጡታል። እንደገና ላሚቱ ወለደች፣ አሁንም ጥጃው ቀበኛ ሆነ፣ ልብስ መብላት ጀመረ፣ ተሸጠ። በዚህ የተበሳጨው የላሚቱ ጌታ፣ ወደ አንድ ሽማግሌ ይሄድና ምክር ይጠይቃል፡፡ ሽማግሌው ቀበኛ ጥጃ እየወለደች፣ ልብሳችሁን የምታስጨርሰው እናቲቱ ናትና እሷን ሽጣትና ሌላ ግዛ አሉት ይባላል፡፡
ይህን ምሣሌ ከተናገሩ በኋላ “አሁን ኢጭአት፣ ሜኢሶን የምትሏቸውን ሁሉ እኛ አልወለድናቸውም፤ ስትሉ ነው የሰማነውና የመጡትም ከእናንተው ዘንድ ስለሆኑ እናታቸውን ፈልጉ” በማለት መተንፈሻ አጥቶ የተቀመጠውን ሰው ሁሉ አስጨበጨቡ። ዛሬም በየአካባቢው ችግር ሲፈጠር ሰው የአካባቢውን ህብረተሰብ ይወቅሳል። እንዴት እንዲህ ያለ ነገር ይፈጸማል ይላል። የአካባቢ ነዋሪዎች ሲሰባሰቡና የመናገር ዕድሉን ሲያገኙ ደግሞ “ጥፋቱን የፈጸሙት እኛን አይወክሉም፣ ከሌላ ስፍራ የመጡ እንጂ የእኛ ልጆች አይደሉም” ሲል ይሰማል፡፡ እንዲህ ከሆነ አንድ ስፍራ እናት አለች ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የችግሩን ግንድ ማግኘትና ማስወገድ የግድ ነው፡፡ አለበለዚያ የተቆረጠ ግንድ ከበፊቱ የበለጠ ቅርንጫፍ ያወጣልና ጠንቀቅ እንበል፡፡      
የተጀመረውን የለውጥ መንገድ ለመደገፍ ወኔውን ይስጠን! ሰብሰብ፣ ጠንከር እንበል! ታዲያ ሁሉም ነገር እየተስተዋለ፡፡
Read 10948 times