Saturday, 08 September 2012 11:03

ገላና ቢጃማ

Written by  ዋሲሁን በላይ (አዋበ)
Rate this item
(3 votes)

ቤቱ ድግስ የተውረገረገበት መሆኑ እሙን ነው፡፡

ድግስ ካለ ብዙ ሰው እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለም፡፡

አልጫና ቀይ ሽታው ግድግዳው ላይ እንደቀለም

የተቀባ ይመስል…

መዓዛው ከቤት ሊወጣ አልቻለም፡፡

የትኩስ፣

ትዳር፣

ጐጆ፤

***

ሰፊው አልጋ ላይ ብቻዋን…መሀል ከተማ ላይ እንደወደቀ ደመራ ተገንድሳለች፡፡ ትላንትናዋን በአሻገር እየፈለገች ነው፡፡ ሂደቷ አጥር ጥግ እንደበቀለ ጽጌሬዳ አይነት ይመስላል…በትንሹ ስፍ ስፍ፣ አይን ገባ…ስፍ…ስፍ…አይን ሞላ… ከዛ እጆች ልብን ሳያስፈቅዱ…እንደሚሠነዝሩት አይነት፡፡

ፊት ለፊቷ የተገተረው ዘመናዊ የሬሳ ሳጥን የሚመስለው መደርደሪያ (መኝታ ቤት ውስጥ ምን ይሰራል) ውስጡ ያሉት ቄንጠኛ የወይን መጠጫ… የቡና ስኒ… እማይበላባቸው የምግብ ሳህኖች (ባለአበባ) ተቆልፎባቸው ያፈጡባታል…(እነሱን የሆነች መሠላት)፡፡ ሃያ ቀን ሙሉ በነፃ ያለ አንዳች

ከልካይ ፊልም ኮምኩመዋል…በቀጥታ ስርጭት፡፡ ዛሬ 21 ቀኗ ነው፡፡ (21)ከቤት አልወጣችም፡፡ እጆቿ ሆዷን እያሻሹ ነው፡፡

እሱ ግን በሳምንቱ ስራ ገብቷል፡፡ ጊዜው ጣዕሙ ያለቀበት ማስቲካ ሆኖበታል፡፡ እሷ ደግሞ

እንደቆሰለች ሴት ነብር ከተኛችበት አልወረደችም፡፡

አልጋ ለእረጅም ጊዜ ያስጠላል!...መውረድ ነፃነትን ያጐናጽፋል፡፡ ነፃነት ደግሞ ከማንም የሚለገሱት 

አይደለም፡፡ ከእራስ እንጂ!፡፡ ዝቅ ብሎ ከፍ ማለት እና ከፍ ብሎ ዝቅ ማለት ቅላቸው ለየቅል ነው፡፡

ሰውነት… ሰራተኛዋ ያበሰለችላትን ትበላለች፣ የታዘዘችውን አምጥታላት ትጠጣለች፤ 21 ግማሽ

ብርሃን…ቀፋፊ ሌሊት፡፡ ቢጃማዋን አልቀየረችም፡፡

ያን ቀን ማታ…እዚህ ቤት ስትገባ ያጠለቀችውን…የውስጥ ሀፍረት መሸፈኛዋን እንኳ አውልቃ

ከወተፈችበት ጥግ አላወጣችውም፡፡ (ትላንትናን መርሳት የት ድረስ;!)

ባዶ ገላዋ ላይ ቢጃማው ሠልጥኗል፡፡

***

ገላ ህሊና ነው፡፡ ቢጃማ ደግሞ መልካምነት፡፡ ገላና ቢጃማ ሲዋሀዱ ሙሉ መሆን አለ፤ ንፁህ ገላ

ብቻውን ቢጃማን ይወልዳል፡፡ ቢጃማ ግን ያለገላ አያምርበትም፡፡

***

ሁሉም ነገር ሠልችቷታል ሳይሆን ቅጡ ጠፍቶባታል…እጆቿ አሁንም ሆዷን እየዳበሱ ናቸው፡፡ እድሜ

አበባ ነው፤ አደይን ይመስላል፡፡

በወቅት ያጌጥና በማታ በማታ ታሞ ይጠወልጋል፣ ጠውልጐ ይታመማል፡፡

***

ጠዋት ከአልጋ ከመውረዱ በፊት…ምሣ ሰዓት ከስራ ተንደርድሮ መጥቶ ከትኩስ ምሣ በፊት ትኩስ

“እንጣዬ”፣ እንደ አቦል ቡና ፉት ይላል፡፡

ማታም እንዲችው…ሌሊቱን ሙሉ ያለምንም ረፍት ፈረሴ ሲላት ይነጋል፤ (ትዳር እንዲህ ነው እንዴ;

የሥጋ ስሜት ብቻ የሚፈተልበት የድር መንደር;) ሰዎች በእጮኝነት ጊዜያቸው ከንፈራቸው ቀፎ

የሌለው የንብ ማንቢያ ነው…አበባ ሳይቀስሙ ማር የሚሰሩበት…ሲጋቡ ከንፈር…የበር እጀታ ይሆናል፤

ቶሎ ነካ ለቀቅ፡፡

***

አሁን ቤቱን ለምዳዋለች…ቤት ሲለመድ ደግሞ ሰፊው አልጋ ላይ ያሉት ነገሮች ሁሉ የራስን ያህል ትኩረት ይሻሉ፡፡ ቤተሰቦቹይመጣሉ…”ለመድሽ” የመጀመሪያ ጥያቄያቸው ነው፣ የሰው ልጅ ትዳርን ትዳሬ ብሎ ከያዘው…ባይለምዱትስ…ያለመዱትን መልመድ እንጂ ምን ተፈትሎ ለገላ ምን ያለብሳል;… ለራስ ገላ ደፋ ቀና ካሉ ለሌላም ገላ መንገላታት ግድ ነው፡፡  ሁሉም ቤተሰቦቹ ወግ አጥባቂዎች ናቸው!...በተለይ ታላቁ ፊቷ ኩፍ ሳይል የተጋገረ እንጀራ ነው የሚመስለው፣ ፊቷ ልቧን ያሳብቃል፡፡ ገላዋ የውስጧን ፊቷ ላይ ጽፎታል፡(አስቀያሚ ፊደል) ስታወራ ጣዕሙ እንደለወጠ ምግብ ትመራለች፡፡ ሁሌም ለሰውነት ህመሟ ናት፤ “ቶሚ እንኳን ሰው የጫካ አሞራ ያላምዳል” ትላታለች…የቤት ርግብ እንደሚያሳድድ ያልገባት፡፡ የቤት አሞራ ያለ ይመስል አሞራ አሞራ ትላታለች…ወገንተኛ መሆን ጥሩ አይደለም፡፡ (አሞራ ፊት) አንዳንዴ ቤት ሳትመጣ ለመምጣት ስታስብ በጣም ስሜቷ ይታመማል፣ ስሜቷ ሲታመም…ገላዋ ላይ ፀሐይ ትጠልቃለች፡፡ ጨለማ ለምቦጩን ይጥላል፡፡

ወግ ከማጥበቋ ሌላ እኔ ያልኩት ካልሆነ ባይ ናት!...ልቦች ናቸው…የራሳቸውን ጐጆ

ሰርተዋል…ለሁሉም ገላ የራሱ ቆዳ ልኩ ነው፤…

የብርጭቆ አስተጣጠብ… የሰሀን አደራደር… ሌላው ቀርቶ እንጀራ እንዴት እንደሚቆረጥ ልታስተምራት

“ይኼ ልጅ አግብቶኝ ነው? ለሙከራ ነው ያመጣኝ?!” ሁሌም የህሊናዋ ጥያቄ ነው፤ ደግሞበፈለገችው ጊዜ ትጠራዋለች…በፈለገችው ጊዜ የትም ይዛው ትሄዳለች…የኔ መሆኑን ታጠራጥረኛለች…ያለውን የእረፍት ጊዜ አብሬው ማሳለፍ እፈልግና በየት በኩል…እሱ ሥጋ እሷ ጭልፊት ሆና፡ እውነት ነው መሠለኝ… የሚስት ቤተሰቦች ምንም ምቾት የላቸውም የሚባለው፡፡ የእኔ ቤተሰቦች በነፃነት ያምናሉ…ኑ ብዬ…ካልጠራኋቸው በስተቀር አይመጡም…ደግሞም የኔ ፍላጐት ብቻም ሳይሆን የቶሚም ፍላጐት መጠበቅ እንዳለበት ይገባኛል፡፡ ለብቻዋ ስታወራ አልታወቃትም፡ ገላዋ ከቢጃማዋ ወጥቷል በከፊል፡፡ እጆቿ ከሆዷ ዝቅ ብለው ማህፀኗን እየዳበሱ ነው…ፀሎት እያደረሱ ይመስላል፤ እሚወለደው ለእናቱ ልጅ እንዲሆን፡፡ አንገቷን አዘቅዝቃ እጆቿ ያሉበትን ተመለከተች፡፡ ህፃን በውስጡ ኖሮ የህፃን ኳስ…አክሏል…16

ሳምንቷ፡፡

***

“ያየሁሽ ሰዓት ነበር የወደድኩሽ፤ እንደወደድኩሽ ልቤን ፍቀድልኝ ላግባት ብዬ ጠየኩት…ለብዙ ጊዜ ለብዙ ሴቶች ልቤ ታዞልኝ አያውቅም…ለጊዜያዊ ዝላይ ካልሆነ በቀር…ብዙዎች ዐይናቸው አንቺ ላይ እንደሆነ ይገባኛል”…አላት…ፍዝዝ ብላ ታየዋለች…ቅዝዝ ብሎ…ያያታል…ነፍሷ ከገላዋና ከቢጃማዋ ጋር ሙግት ገጠሙ…ቢጃማዋ ቢቀየርም ቅሉ ያው ገላ ላይ ስለሆነ አንድ ነው እንበል…በመጠን ከበፊቱ ሰፋ ብሏል… “እኔ ግን ስህተት ነበር የሠራሁት” አለችው ለገላዋ…ገላዋ መቀየሙን በትኩሳት ነገራት…ቢጃማዋ ገላዋ ላይ ተጣብቆ እንደ ሆዷ አስተዳደግ አብሮ ለመለወጥ ይሻል “ቻይ ሁኚ” አላት

ቢጃማዋ፡፡

***

ገላ ቦዶውን ውበት የለውም፡፡ የተሸፈነ ነገር ያጓጓል… ሰው ቤተመቅደስ ነው ካልን…ቤተመቅደስ ደግሞ…በተዋበ፣ በተመረጠ፣ መሸፈኛ ይሸፈናል…ውብ የሆነ ሽቶ ያሻዋል…የተመረጠው ሁሉ ተመርጦ ይመረጥለታል፡፡ (ለቤተመቅደስ) መዐዛው ከሩቅ የሚጣራ እጣን መታጠን አለበት፡፡ ተራራው ድረስ የሚሸት … ተራራው እልል ብሎ ማመስገን ይችላል፡፡ እልልታው ግን ይሰማል እንጂ ለእይታ ብቁ አይደለም፡፡ ምሥጋናው አይቋረጥም፡፡ ይመሻል…ይነጋል…ማመስገኑ ይቀጥላል…እጣኑም እንደዛው…ከነ ማዕዛው ወደ ላይ በመላዕክት አጃቢነት…በእጅ ባልተሰራ መሠላል ይወጣል፡፡ እላይ ደግሞ ለታቹ የሚራራ አባት አለ፡፡ቤቱ ድግስ ድግስ መሽተት ትቶ…ነፍስ ነፍስ መሽተት አለበት…ሰው ነዋ የቤቱ ባለቤት፣ ቤተመቅደሱን ያላከበረ ገላው የእሱ አይደለም፡፡ ቢጃማም አያስፈልገውም፡፡ የቤተመቅደሱ ባለቤት የእያንዳንዱን ገላ ንፅህና ይፈልጋል፡፡ በባህሪው ንፁህ ስለሆነ፡፡ ገላው የሱም ገላ ነዋ፡፡ ቢጃማውም የሱ፡፡

***

“በእንዲህ አይነት ዘመን ሲመሽ ተወልጄ ጅቡን ጋሼ እላለሁ…ውሻውን ወድጄ” አንገቱን የደፋው አቀንቃኝ ዘፍኖታል፡፡ የቀደመው ሲፈጠር…ከተፈጠረው ላይ ተሠራ…የሴት ልጅ ገላ (አይናቅም) ከገላው በፊት ግን ሠፊው አልጋ ተፈጥሮ ነበር፡፡ “ደግሞ ለዚህ ለተበጀ ገላ” ልትል ብላ ማለቷን ባለማለት ተወችው፡፡ገላዋ 32 ሳምንቱ ነው፡፡ ውኃ እንደያዘ ስስ እቃ ውጥርጥር ብሏል፡፡ ቢጃማውም እንደዛው መልክ የሸሸው መስሏል፡፡ ገላ ሁሉ ይሸፈናል፡፡ እርቃንነት ጥሩ ስላይደለ፡፡ ክብር ኖሮት ይከበራል፡፡

***

ቶማስ (ተጠራጣሪው) ሰውነት አረገዝኩ ባለችው በ21ኛው ቀን ጥምብዝ ብሎ መጣ በስካር፤ ደስታ ይሁን ንዴት ውሉ አልለየም፡፡ እንደዛ ውሃ ውስጥ የገባ ጨርቅ መስሎ “ልገናኝሽ” አላት፡፡ ሴት ልጅ ከፀነሰችበት ጊዜ ጀምሮ ወልዳ ልጇን ክርስትና እስክታስነሳበት ባለው ጊዜ ውስጥ እንዲች አርጐ

መቅመስ የለም፡፡ 36 ሳምንት ተቸገረ…

“ማድረግ አንችልም” አለችው!!

“ለም…ን?” ፊደሎቹን አንድ ላይ ለመከወን የሆነ ጊዜ ፈጅቶበት ነበር…አፉ ውስጥ ሟሙ፡፡

“ፀንሻለሁ” በህልም እምታወራ ነው የምትመስለው፡፡

“እንዳገባሁሽ ነው ያወቅሁት…ከመወለዴ በፊትም እንዲሁ ነበርሽ”

“አይቻልማ!” ከአሁን በኋላ ልጁ እስኪወለድ የወንድ ገላ ባይነካት ወዳለች፡፡

“ማነው…ያለው ሚስቴ እኮ ነሽ! ሚስቴን ደግሞ እንደፈለኩ ላረጋት መብት አለኝ… “ብሆንስ ሚስትህ ብቻ ስለሆንኩ እኔ ሳልፈቅድ ገላዬን በገላህ ማቁሰል አለብህ!”  ልትለው ፈልጋ…ደግሞ በዚህ ብስለት በጐደለው ህሊና ላይ ስካር ተጨምሮበት አይደለም…በደህናውም ጊዜ እምቢ ማለት አልቻለችም ነበር/

ነፃ ገላ በማንም ይደፈራል እንዴ?!/

ያጣ ገላ በማግኘት ንቃቃቱ ሲደፈን እየሆነ ያለውን አያውቅም፡፡ ላይ ያለ ሰው መውረድ አይሆንለትም፡፡ ቢጃማን ከገላ ሥር ማድረግ እንደማይቻለው…የቶማስ ገላም ቋንጣ ነው…በተቀደደ ቢጃማ ገመድ መሠል ትልታይ የተሠቀለ፡፡ ዝቅም ብሎ ከፍ የሚል ሰው ያው ነው! ተመልሶ ማነስ አይወድም…ማንም ያገኘውን ማጣት አይፈልግም፡፡

ያገኘውን ላለማጣት ይጨክናል፡፡ ለእነዛ 21 ብርሃንና ጨለማ ጊዜ ስትፀንስ እንዲህ የገላው ስስነት

የገዛ ራሱን መልሶ እንደሚያስበርደው አላወቀም ነበር፡፡

***

አሁንም ሰፊው አልጋ ላይ ብቻዋን ናት…ሆዷ ውስጥም ያለው እንዳለ ሆኖ ቶማስ የቀኝ…አልጋው ጠርዝን ተደግፎ ርሃቡን በልመና አስተዛዝና ለመመጽወት…መሬት ላይ ተቀምጧል (መሬት ደስ ይላል) የጠጣው ደረቅ አልኮል ከንፈሩ ላይ እንዳልተጠረገ ማዕድ ቤት አመድ በዝቶበታል፡፡ መስጠት ያለብንን ነገር ከሠጠን የፈለግነውን ሳንጠይቅ አንከለከልም፡፡ አዝኖ ለማሳዘን ሀዘን ልብን መጐብኘቱ ግድ ነው፡፡ ህሊናና መልካምነት ከተዋሀዱ..ፅንሱ የማንም ይሁን ይወለዳል፤ እነሱ ባይኖሩ እንኳ የተወለደውን ማንም ያሳድገዋል፡፡ ሠፊው አልጋ የሁሉም ነዋ፡፡ ሁሉም ገላ ስላለው፡፡ ቢጃማ ደግሞ ገላ ይኑር እንጂ ችግር የለብንም፡፡ አሁን የምታጓጓ ጽጌረዳ ናት፤ አጥር ጥግ ሳይሆን መሀል አደባባዩ ላይ የበቀለች፡፡

ቀኗ ደርሷል፡፡

ሆዷም በጣም ገፍቷል፡፡

ቤተመቅደሱ ፍፁም ንፁህ መሆን አለበት፡፡

***

ያቺ ሠፊው ሀገር ላይ የተኛችው፣ ህሊናዋን በስስ መልካምነት ሸፍና ቀኗን ከሚያገላግላት ንፁህ ሰው ጋር የምትጠባበቀው ቆንጆ፣ (ፅንሱ ሊወለድ ከሆነ ደግሞ እሠየው…) የሆነ ብርሃን ይኖራል፡፡ (ብርሃን መች ጠፋ፤ ልቦች አይናቸው ታውሮ እንጂ) ብርሃኑን በገዛ እጃችን በራስ ወዳድነት እናጨልመዋለን፡፡ የጽንሱ ጊዜ ደርሶ ጊዜው ቢያልፍስ? ባይወለድ!?...ልጁ የእኔ ነው ብሎ የይገባኛል ጥያቄ ማን ሊጠይቅ?!...ከዚህ ሌላ 21 በጋና ክረምት ይመጣ ይሆን? (ቀንን አመት…አመቱን ቀን የማድረግ የቤተመቅደሱ ባለቤት ሰጥቶናል)

ሌላ ፅንስ ወይስ ተወልዶ ሌላ የሙሽርነት ጊዜ…?!

እናቱን የሚያገባ ይወለድ ይሆን…?

አባቱን ይገድላል ማለት ነዋ!!!

ወንድምም ልጅም ለመውለድ!!!

የተወለደን ከርክሞ ማሳደግ…ወይስ የተወለደን ቀብሮ

ሌላ ማስፀነስ…? (የገላና የቢጃማ ጥያቄ ነው)

***

ሰፊው አልጋ ላይ በላብ ተጠምቃ፣ ገላዋ ርሶ፣ ቢጃማዋ

ገላዋ ላይ ተጣብቆ ትታያለች፡፡

ሰውነት፡፡

***

“ያውና እዛ ማዶ በግ ያግዳል ሰው

ካላየ ካልሰማ ባል አህያ ነው”

***

 

 

Read 3691 times Last modified on Saturday, 08 September 2012 11:12