Sunday, 25 July 2021 00:00

“በሉአላዊነታችን ተደራድረን አናውቅም፤”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

“…በ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ያስመዘገብነው ድል በመላው ዓለም ትምህርት የሰጠ፣ ይበተናሉ እያሉ ሲያሟርቱብን የነበሩ ሃይሎች ሁሉ እንደ ብረት የጠነከረ ህብረ-ብሄራዊ አንድነታችንን ያሳየ ድል ነው።
ሉአላዊነታችንንም ለመዳፈር የሚቃጡ አካላት ሁሉ ፍፁም እንደማንበገር በገሃድም ያስመሰከርንበት ነው። የዚህ አንጸባራቂ ድል ባለቤት የሆነው ጨዋውንና አይበገሬውን ህዝባችንን በታላቅ አክብሮት ዝቅ ብለን ምስጋናችንን እንገልፃለን።…
እነኚህ የአሸባሪ ቡድኖች በአንድ ጀንበር ኢትዮጵያን የማፈራረስና ህዝቦቿን አገር አልባ የማድረግ፣ እንደገና አፈር ልሶ የመነሳት አባዜ ውስጥ ናቸው። መንግስት በሰብአዊነት ለትግራይ ህዝብ በማሰብ የተናጠል ተኩስ አቁም እርምጃ ቢወስድም፣ ወትሮም  ቢሆን ለትግራይ፣ ህዝብ ደንታ የሌለው አሸባሪው የህወሃት ቡድን የሰብአዊ እርዳታ ጭምር ወደ ትግራይ እንዳይደርስ እያደናቀፈ ይገኛል። የዚህ እኩይ ተግባሩ ት/ቤት እንጂ አፈሙዝ የማይገባቸውን ህፃናት ለጦርነት በመጠቀም፣ አስነዋሪና አሳፋሪ ድርጊት ሲፈጽም እያየን እንገኛለን።…በኢትዮጵያ እየተመዘገቡ ያሉ ድሎች የኢትዮጵያውያንን አንድነት ያሳዩ ናቸው…”
(የአዲስ አበባ አስተዳደር ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ድጋፉን ለማሳየት፣ የታጣቂውን የህወሃትን ቡድን ተግባር ለመቃወምና በህዳሴው ግድብ ለተገኘው ድል ደስታውን ለመግለፅ በመስቀል አደባባይ ለተሰባሰበው በብዙ ሺዎች የሚገመት ህዝብ ካደረጉት ንግግር የተወሰደ)

Read 11413 times