Saturday, 17 July 2021 15:44

ለሰሞኑ እንዲሆን ተደርጎ remix የተደረገ የከረመ ወግ

Written by  በእውቀቱ ስዩም
Rate this item
(0 votes)

  ጎረቤቴ ቺስታ ግብፃዊ ነው፤ "ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን ከገነባች እንግዲህ ተስፋ የለንም" ብሎ አሜሪካ ውስጥ ጥገኝነት ጠይቆ በመኖር ላይ ይገኛል! እኔ ከወራት በፊት “ግድቡ ተሽጧል” እሚለውን ቀደዳ አምኜ ጥገኝነት መጠየቄን የሰማ አይመስለኝም፡፡
ኑሮዬ ለክፉ እሚሰጥ አይደለም፤ አውቶብስ እነዳለሁ፤ በተረፈው ጊዜዬ ዲሽ አጥባለሁ፤ የናሳውን ሳተላይት ዲሽ ማለቴ ነው፤ ግብጡ ግን መና-እጢ ደሃ ነው፤ (by the way “መናጢ ድሃ” ማለት በጣም ከማጣቱ የተነሳ እጢ ሳይቀር የሚቸግረው ድሃ ማለት መሆኑን ስንቶቻቸን እናውቃለን?) ስላሳዘነኝ እኔ በወር ሰማንያ ዶላር እምከፍልበትን ዋይፋይ እንዲጠቀም ፓስወርዱን ሰጠሁት፡፡ አንባቢ ሆይ! ለዚህ ደግነቴ ያገኘሁት ምላሽ ምን ይመስልሃል? ባለፈው መንገድ ላይ አግኝቶኝ፣ እሳት ጎርሶ እሳት ለብሶ፣ ባረብኛ “ኢንቲ አዩኒ” ብሎ ባረቀብኝ! የዛሬ አመት ወደ አሜሪካ ስበርር ለትራንዚት ዱባይ አምስት ሰአት ስለተቀመጥሁ አረብኛ በመጠኑ እሰማለሁ፤ ምን ማለቱ መሰላችሁ፤ “ፊልም ላይ ተጥደህ እየዋልክ ኔትዎርኩን ስሎው እያደረግህብኝ ነው!" ማለቱ ነው! እረ ገለስ! ውፈር ተበገስ it is my Wi-Fi‘ ብዬ ቀወጥኩት!
(በግብጽ የኢትዮጵያ አምባሳደር እንዳጫወቱኝ ግብፆች “ጀ“ የሚል ቃል የላቸውም፤ ገማል ይላሉ እንጂ ጀማል አይሉም! ለዛ ነው ”ጀለስ; ማለት ሲገባኝ “ገለስ; የሚለውን ቃል የተጠቀምኩኝ! ለምሳሌ፤ ባህር ዳርቻ አሸዋ ላይ በጀርባህ ተንጋለህ ተኝተህ፤ ደረትህን ለጸሀይ፥ ጉያህ ላይ ያለውን ፎጣ ደግሞ ለነፋስ ሰጥተህ ዘና ስትል፤ አንዲት ግብፃዊ “ገላህ ያምራል" ካለችህ  ሙገሳ አይደለም፤ ሃራስመንት ነው!
በምነዳው አውቶብስ ውስጥ እንደ ወያላ ሆኖ የሚሰራ ፈረንጅ አለ፤ ትናንት የተቃውሞ ሰልፈኞችን ኒውዮርክ አራግፈን ስንመለስ ያባይ ነገር ተነሳና “ግብጻውያን በፍቅር ዘፈን ውስጥ ሳይቀር ስለ ናይል እንደሚዘፍኑ ታውቃለህ?" አለኝ “አንተ በዚህ ትገረማለህ? የእኛ ዘፋኞችማ ግድቡ ከመሰራቱ ሃያ አመት አስቀድሞ ስለግድቡ ሲዘፍኑ ኖረዋል" ብዬ መለስኩለት፤ የነገርኩትን ሰምቶ አማትቦ ዞር ይላል ብዬ ሳስብ “እስቲ አንዱን ዝፈንልኝ ; ብሎ አያፋጥጠኝም? ዞር ዞር ብዬ አውቶብሱ ውስጥ አበሻ አለመኖሩን ካረጋገጥኩ በሁዋላ የንዋይ ደበበን ዘፈን ተረርር ር አደረኩለት ፤
“ገዳም የፍቅር ገ-Dam
ልቤ አንቺን አይከ-dam”
በነገራችን ላይ፤ ግድቡን ትተን ስለ ባልቦላው ማውራት የምንጀምርበትን ጊዜ አልናፈቃችሁም?! እንደኔ እንደኔ፤ ግድቡ ስራ ሲጀምር ለአንድ አመት ያህል ህዝቡ ለመብራት መክፈል የለበትም! እንዲያውም በጊዜ መብራት አጥፍቶ የተኛ ሰው በወንጀል ቢጠየቅ ደስ ይለኛል!
የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና ግድቡ ተርባይኑን ማንቀሳቀስ ቢያቅተው ወይም ተርባይኑን ለጥቂት ቢስተውስ? ወይ ደግሞ የግልገል ጊቤን አርአያ ተከትሎ ቢገግምስ? እኔ ጣጣ ያለው አይመስለኝም፤ ሌላው ቢቀር ሳልመን እናረባበታለን፤ በነገራችን ላይ ሳልመን የፈረንጅ ሞጃ እሚበላው ምርጥ ያሳ አይነት ነው፤ በአሳ በሎች ግምገማ እንደ ሀረር ሰንጋ ይቆጠራል፤ ሳልመን የበላ ትውልድ ጭንቅላቱ ይሰራል፤ ጭንቅላቱ ከሰራ አጥብቆ ይመራመራል፤ ኤሌክትሪክ የሚያመነጭ ኒውክልየር ይፈጥራል፡፡
ይህ በእንዲህ እያለ፤ አባይ በተነሳ ቁጥር “አባይ ማደርያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል; የሚለው እጅ እጅ እሚል ተረት መጠቀሱ የማይቀር ነው፤ የሆነው ሆኖ፤ ከግድቡ ሙሌት በሁዋላ ግንዱ ለማን ይደርሳል? ዶክተር ዐቢይ፡- ሶስት ቦታ ተቆርጦ እንደ ቅርጫ እንካፈለው እንደማይል ተስፋ አለኝ! እዛው ግብፅ ፈልጣ ሩዝ ትቀቅልበት!
ከአበዛሁት አትፍረዱብኝ! የአገር ፍቅር ሲበዛ ካቲካላ ነው! አናት ላይ ይወጣል!

Read 2045 times