Print this page
Saturday, 17 July 2021 15:42

ጦርነት መፍትሔ አይሆንም፣ ሆኖም አያውቅም

Written by  ሙሼ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

  በጦርነት አሸንፎም ሆነ ተሸንፎ ልቡ የፈቀደውን ያደረገ ስርዓት፣ መንግስት ወይም ቡድን በዓለም ላይ የለም፡፡ ይዋል ይደር እንጂ ጦር አውርድ ባዮች እርስ በርሳቸው ተጫርሰውና ሕዝብ አጫርሰው አቅማቸው ሲሟጠጥና ጉልበታቸው ሲዝል ሁሉም ወደ ድርድር ጠረጴዛ መምጣታቸው አይቀርም። የትናንት አሳዳጅ የዛሬ ተሳዳጅ፤ የዛሬ ተሳዳጅ ደግሞ የነገ አሳዳጅ፣ ትናንት ግፍ ተፈጽሞብኛል ባይ ዛሬ ግፍ ፈጻሚና ሂሳብ አወራራጅ ተራ በተራ በመሆን ሁላችንም በአዙሪት ውስጥ ተዘፍቀን እንደምንዳክር በተግባር እያየነው ነው፡፡
ጦርነት መፍትሔ አይሆንም፣ ሆኖም አያውቅም፤ ቁጭ ብለን ሰጥቶ በመቀበልና በመርህ እንደራደር ሲባል ሌላ ተአምር ኖሮ ሳይሆን ጦርነት የመጨረሻውን ሽንፈት ለመበቀል በሚደረግ ትንንቅ ተጠምደን ወደ ከፋ እልህ፣ መጠፋፋት፣ ጭካኔና ፈጽሞ ማምለጫ ወደሌለው አዙሪት ውስጥ መግባታችን የሚጠበቅ ስለሆነ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ጦርነቱ ከአንዱ ሕዝባዊ ትግል ወደ ሌላው ሕዝባዊ ትግል ተሸጋግሮ ታጠፋኛለህ ወይም አጠፋሃለሁ የሚል ሆኗል፡፡ ይህንን መጠፋፋት ለመቀልበስ ሲባል ሌላ ሕዝባዊ ትግል ልታዋልድ ሀገራችን በምጥ ላይ ነች፡፡
በዚህ ሂደት ጦርነቱም እየተባዛ በመቀጠል፤ አዳዲስ ጦረኞች ከየራሳችን ክልላዊ እምብርት ተዋልደውና ተራብተው በቅርቡ ሁሉን አቀፍ ጦርነት ውስጥ ተዘፍቀን መፍትሔው እንደ ሰማይ ሊርቀን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ እዚህ ላይ የጎረቤት ሀገሮችና የዓለም አቀፍ ማህበረሰብን ጣልቃ ገብነት ጨምሩበት እንግዲህ !
ሰርቢያ፣ ሶርያ፣ የመንና ሶማሊያ ሩዋንዳ ወዘተ (Sectarianism) በሴክቴርያኒዝም ብጥስጥሳቸው የወጣውና አንዳንዶቹ አጣብቂኝ ውስጥ ተቀርቅረው የቀሩት፣ በዚህ ዘመን ከንግግር ይልቅ አንዳቸው አንዳቸውን በጦርነት ለማሸነፍ እንችላለን ብለው በመታበያቸውና ትልልቅ ጦርነቶችን ቀስቅሰው እልፍ ትንንሽ ጦርነቶችን መጸነስና መወለድ በመቻላቸው ነው፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያ ከዚህ ውጥንቅጥ ብዙም የራቀች አይደለችም፡፡ በየአቅጣጫው የጦርነት ነጋሪት ጉሰማው እያደገና እየጎላ በመምጣት ከአንድ ጦርነት ውስጥ ሌላ ጦርነት እየተረገዘና እየተወለደ ጥላቻውና እልቂቱም በመስፋፋት ላይ ነው፡፡ ጎረቤት ሀገሮች ዛሬ ፈራ ተባ ቢሉም ቀን እየጠበቁልን እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ ምዕራባውያንም በለመዱት መንገድ የቀሰቀሱትና ያባባሱትን ጦርነት ሲከር በቅጡ ሳያቦኩና ሳይጋግሩ ጥለውን እንደሚፈረጥጡ የታወቀ ነው፡፡ ወገን፣ ለራሳችን ያለነው እራሳችን ብቻ ነን፤ ለተሻለ ነገ ዛሬ እንደማመጥ እላለሁ!!

Read 2176 times