Print this page
Saturday, 17 July 2021 15:40

ፕራግማቲዝም “የትም ፍጪው፣ ዱቄቱን አምጪው” አይደለም

Written by  ጌታሁን ሔራሞ
Rate this item
(0 votes)

   ፕራግማቲዝም ውጤት-ተኮር ውሳኔ የመስጫ ፍልስፍናዊ መርህ ነው፣ ልምድ ላይ ለተመሠረቱ ዕውቀቶች (Experiential Knowledge) ቅድሚያ ይሰጣል። የሳንደርስ ፓርስንና የዊሊያም ጄምስን ፕራግማቲክ ፍልስፍናን “systematize” በማድረጉ ስሙ የሚነሳው አሜሪካዊ ጆን ድዌ፤ ፕራግማቲዝም ልምድን ወደ ዕውቀት ቀይሮ ፍልስፍናን መላ ቅጡ ከጠፋበትና ለማህበራዊ ጠቀሜታ ምንም ፋይዳ ከሌለው ደረቅ ንድፈ ሐሳብ ይታደጋል ይለናል...”Pragmatism intellectualizes practice”
አንዳንዶች እንደሚሉት፤ ፕራግማቲዝም “የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጪው” ዓይነት ፍልስፍና አይደለም። በአጭር ቃል ፕራግማቲዝም ዱቄቱ የት መፈጨት እንዳለበት ቅድሚያ ጥናት ያደርጋል። በጆን ድዌ የፕራግማቲክ ፍልስፍና አቅጣጫ ከሄድን፣ ድዌ ልምዶችን የሚገመግምበት ሳይንሳዊ ሂደቶች አሉት...In fact some postmodern philosophers such as Richard Rorty criticized such scientific and objective methodology of John Dewey... ያም ሆኖ የጆን ድዌ ፕራግማቲዝም ለተሞክሮዎች ቅድሚያ ይሰጣል ማለት የተሞክሮዎቹ ዘለቄታዊ ጠቀሜታዎች በሳይንሳዊ መንገድ አይፈተሹም ማለት አይደለም።
ስለዚህም ምናልባት መንግስት በአሁኑ ወቅት ለውሳኔ አሰጣጥ ፕራግማቲዝምን እንደ አንድ መርህ እከተላለሁ የሚል ከሆነ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት። እደግመዋለሁ... ፕራግማቲዝም “የትም ፍጪው፣ ዱቄቱን አምጪው” ዓይነት መርህ አይደለም። በተቃራኒው ፕራግማቲዝም ወደ ውጤቱ ለመድረስ የመረጥነው መንገድ በአጭርና በረዥም ጊዜ የሚያመጣውን ተፅዕኖ በሚገባ ይፈትሻል፣ በአጭር ጊዜ ጥቅምና ውጤት ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ መወሰን የረዥም ዘመን ሳንካን ይፈጥራል። ለዚህም በምሣሌነት የመፅሐፍ ቅዱሱን አብርሃምን እንዳነሳ ይፈቀድልኝ፦
አብርሃም ከሚስቱ ሣራ ልጅ ለመውለድ ያደረገው ጥረት ሳይሳካለት በመቅረቱ ሳራ ባሏ አብርሃም ከሠራተኛው ከአጋር ልጅ እንዲወልድለትና እሷም ከአጋር የሚወለደውን እንደ ልጇ አድርጋ ለማሳደግ ቃል ገባችለት። አብርሃም የሚስቱን ምክር ከሰማ በኋላ “ፕራግማቲክ” የሚመስል ውሳኔን ወሰነ፣ ውጤት-ተኮር ሆኖ ከአጋር እስማኤልን ወለደ፣ ቆይቶ ግን በሣራ በኩልም የተስፋው ቃል የነበረው ይስሐቅ ተወለደ፣ ከዚያ በኋላ በእስማኤልና በይስሐቅ መካከል የተፈጠረው አተካራ አብርሃምንና ሣራን የቱን ያህል እንዳናጋቸው ከማናችንም የተሰወረ አይደለም። ያኔ በአብርሃምና በሣራ የተወሰነው ፕራግማቲክ ተብዬ ውሳኔ ዛሬም ድረስ ለሁለት ካምፕ ውጥረቶች ምንጭ ለመሆን በቅቷል።
መንግስት ውጥረት ውስጥ ሲሆን በአጭር ጊዜ ውጤት ላይ ብቻ ተመስርቶ እንደ አብርሃምና ሣራ ለትውልድ የሚተላለፍ ውሳኔን ከመወሰን መታቀብ አለበት። ዛሬ ስኬታማ ያደረጉን የሚመስሉ ውሳኔዎች በረዥም ጊዜ ያልተጠበቀ ዕዳ ይዘው ሊመጡ ይችላሉ።


Read 2700 times