Saturday, 17 July 2021 15:33

የመጽሐፍ ወዳጁ የህይወት ዳና

Written by  ሳሙኤል በለጠ (ባማ)
Rate this item
(1 Vote)

    የሕይወት ታሪክ የባለታሪኩን ሕይወት ዙሪያ ገብ መተረክ አለበት፤ ነገር ግን ሰው የተጓዘበትን የዳና ፈለገ ውል ለማግኘት እድል ላይቀናን  ይችላል። ስለዚህ የሕይወት ታሪክ ጸሐፊ በገር ልቡናው አመዛዝኖ የመጻፍ ችሎታው ላቅ ያለ ሊሆን ይገባል። ሰሞኑን በገብረክርስቶስ ኃይለሥላሴ የተጻፈውን “የስምዖን የሕይወት ጎዳና (የመጽሐፍ ወዳጅ)" የተሰኘውንና  በስምዖን ተክለሃይማኖት የሕይወት ታሪክ ዙሪያ የሚያጠነጥነውን መጽሐፍ አንብቤ እረክቼአለሁ፡፡ መጽሐፉ በ166 ገጾችና በ 8 ምዕራፍ የተከፋፈለ ነው። አተራረኩ ማራኪ ነው፡፡ አርትዖት ላይ የተደረገው ጥንቃቄ ግሩም ነው።
እውን ጋሽ ስምዖን ታሪካቸው ሊጻፍ ይገባል? ብለን ስንጠይቅ፤ አዎ ይገባል ነው መልሱ፡፡ አንድም “የሞተ ሕልም ተሸክሞ ከመኖር፣ የሚኖር ሕልም ይዞ መሞት ሳይሻል አይቀርም “ ስለሚባል ጋሽ ስምዖን የሚኖር ሕልም ስላላቸው ፣ ሁለትም ጨለማ የዋጣትን አገር በሃሳብ ብርሃን ያደመቁ ነገር ግን በቅጡ ያልተዘከሩ መኖራቸው ሃቅ በመሆኑ፡፡ “ነብይ በአገሩ...” እንዲል ከጀግኖቻችን መንፈስ ክፋይ ሳንካፈል፤ ኅያው ወለላ ታሪካቸው ሳይሰነድ የትም ተንጠባጥቦ መቅረቱ ሁሌም ነው የሚያስቆጨኝ፡፡ ከዚህ አንጻር የስምዖን ተክለሃይማኖት የሕይወት ታሪክ መሰነዱ ብዙዎችን ያነቃቃል ብዬ አምናለሁ...፡፡
መነሻ
የሕይወት ታሪክ ለመጻፍ ስንነሳና ባለታሪክ ስንመርጥ በተለያዩ ምክንያቶች ላይ ሊመሰረት ይችላል፡፡ ነገር ግን ምክንያታችን ምንም ሆነ ምን ታሪኩን መጻፉ አንዳች ፋይዳ ይኖረዋል፤ ብለን የምናምንበትን ግለሰብ መምረጥ ያስፈልጋል፡፡ የሃሳብ ፍኖት ማቅናት እጅግ መታደል ነው። ሆኖም ይህች ዓለም በራሳችንም በሌሎችም ሕልም እንድናንቀላፋ ታስገድደናለች እናም ከዚህ ዘላለማዊ እንቅልፍ መንቃት እንደ ያዕቆብ (እስራኤል) መባረክን ይጠይቃል። ስምዖን ተክለሃይማኖት በሌሎች ሕልም የነቁ ብልህ ናቸው። መንገዶች ሲያንቀላፉ የእሳቸው ሁለቱም የእግር ነፍሶቻቸው የነቁ ነበሩ፡፡ ስምዖን “የምፈልገውን ስለማላገኝ የማገኘውን እወዳለሁ” የሚሉ ተስፈኛም ጭምር ናቸው። ገብረክርስቶስ የስምዖንን ታሪክ ሲጽፉ ስለ ሕይወታቸው መሰረታዊ የሆኑ እውነታዎችን እንደመረመሩ ታሪኩ ይመሰክራል፡፡ ከግለሰቡ ሕይወት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ቦታዎችን ምሥል ከሳች በሆነ መልኩ ተርከውልናል።
ገብረክርስቶስ የስምዖንን ውልደት እንዲህ ይተርኩልናል፤ “ክረምት አልፎ በረጋው በተንሠራፋበት በሕዳር አሥራ ዘጠኝ ቀን 1934 ዓ.ም የተባለው ወንድ ልጅ ተወለደ። የክርስትና ስሙ ወልደ ስምዖን ተባለ። ይኸው ስም የዕለት ተዕለት መጠሪያ ሆኖ ሕጻኑ እድገቱን ቀጠለ። የኋላ ኋላ አስኳላ ትምህርት ቤት እንዲገባ ሲደረግ ስሙ ይረዝምና እንዳይቸገሩ በሚል ታላቅ ወንድሙን ወልደ ጻዲቅ በአጭሩ ስምዖን ተብሎ እንዲጠራ አደረጉ። ሦስት ዓመት ሲሆነው እንደ ማንኛውም የገጠር ሕጻን የጠበቀው የእረኝነት ሥራ ነበር። ወልደ ስምዖንም የእረኝነት ተግባሩን ቀስ በቀስ እየለመደና እየወደደው ሄደ።” (ገጽ 22)
የበጋ መስኮት ተከፈተ፤ በጽንስነት ወቅት ሰው ከእውነትም ከውሸትም ቢርቅም ሲወለድ በሕግጋት ታስሮ፣ ከውብ ሕልሙ ነቅቶ፣ ሕልም የማይመስሉ መራር ልቅላቂዎችን እየተጋተ ኑሮውን ይቀጥላል። ለዚህም ጥንካሬ ይጠይቃል። ጽኑ ሰው ወደ ምድር ሲመጣ ኃውልት ይሰራል። ለምን ኃውልት ይሰራል? ሊያውም በሕይወት እያለ? ሲሞት ማንም ሊያስታውሰው ወይም ሊያሰራለት እንደማይፈልግ ስለገባው?  የእኔም ሙሉ ያልሆነ ቁንጽል ጥያቄ ነው። ጋሽ ስምዖን ያለፉበት የሕይወት መንገድ ገና በማለዳው የሕይወት ልቡና ላይ ለመድረስ እንዲንደረደሩ የሚገፋፋቸው ነበር፡፡ “ወጣቱ ወልደ ስምዖን ቤተ ክርስቲያን በማገልገል፣ በግብርናና ከብት በመጠበቅ ተወዳጅነትን አትርፎና “ወሰው” ተብሎ በእንቢጣጣ ቆይቷል። በገጠር ከሚሰሩ ተግባራት መካከል ባይሰራ የሚወደው የአረም ሥራ እንደነበር ያስታውሳል። በተረፈ ከብቶቹንና በጎቹን በቅርቡ መንከባከቡና ከእነርሱም ጋር እየታገለ ማደጉ፣ ከባድ ጉልበት የሚጠይቁትን እርሻ፣ አጨዳ፣ ሸክምና አሂዶን የመሳሰሉትን ያለገደብ መሥራቱ ለሰውነቱ ጥንካሬን፣ ለመንፈሱም አይበገሬነትና ጤነኝነት እንዳጎናጸፉት ያምናል። “(ገጽ 25) ጋሽ ስምዖን ፊት በልጅነታቸውና በወጣትነታቸው የከወኑት ነገር በሙሉ በኋላ ላይ ለከፍታ አበቃቸው፡፡
የሕይወት ታሪክ ጸሐፊ በባለታሪኩ ተደጋግመው የሚመጡ ክስተቶችን ማጤንን ሥራዬ ሊለው ይገባል፡፡ በግለሰቡ ሕይወት ውስጥ ወሳኝ የሆኑ እንደ ስኬት፣ ውድቀት፣ ሐዘን፣ ደስታ፣ ሕመም ያሉ ሁነቶች ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት፡፡ በዚህም ረገድ ገብረክርስቶስ ተሳክቶላቸዋል የሚል እምነት አለኝ፤ አንዳንድ የዘነጓቸው ጉዳዮች ቢኖሩም፡፡ ስምዖን መሆን የሚፈልጉት ሐኪም ነበር፤ ነገር ግን እድላቸው ወደ ቤተ መጽሐፍ ባለሙያነት መራቸው (የእንግሊዛዊ አስተማሪው “የምትፈልገውን ካላገኘህ ያገኘኸውን ውደድ” የሚል ምክርም ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል)፡፡
የስምዖን ሃኪም የመሆን ሕልማቸው እንደ ቅቤ እየቀለጠ ለመጽሐፍ ያላቸው ጽኑ ፍቅር እንደ ዐለት እየደደረ መጣ፤ ስምዖን ድሮ ዶክተር እሆናለሁ ብለው በጭንቅላታቸው የቀረጹት ሕልም ሕዝብን በማገልገል በሌላ ያልተጠበቀ ሕልም ተቀየረ። የቤተ-መጻሕፍት ባለሙያዎች ለሙያቸው  ፍቅር ካላቸው፣ ትውልድን የማዳን ስልጣን አላቸው። ስምዖንም ይላሉ፤ “መጽሐፍት መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን በጥቅም ላይ መዋል አለባቸው፣ የቤተ  መጻሕፍት ባለሙያነት የቱን ያህል ክብር እንዳለው፣ ሰዎችን ከልብ ማገልገልና በሥራ ዓለም ከሁሉም ጋር ተባብሮ መሥራት ውጤት እንደሚያጎናጽፍና ተሯሩጦ ጉዳዮችን መከወን የላቀ ተግባር መሆኑን የጄኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት፣ ቤተ መጻህፍት የሦስት ዓመታት ቆይታዬ አስተምሮኛል።”
ነገሮች ለስምዖን መለዋወጥ ጀመሩ። “በራሱ የአደረጃጀት ትልምና አካሄድ መሠረት በአጭር ጊዜ ውስጥ የኢሠፓአኮ ማዕከላዊ ኮሚቴ ቤተ መጻሕፍት ሊመሠረት ችሏል። በተከታታይ ዓመታት በተደረገ ጥረትም በዋናው ቤተ መጽሐፍት ከሃያ አምስት በላይ ሠራተኞችን በማሳተፍ፣ በመላው ኢትዮጵያ ደግሞ 300 ቤተ መጻሕፍትና ከ500 በላይ ሠራተኞች አደራጅቶ ለመምራት ተችሎ እንደነበር ስምዖን ያስታውሳል።” (ገጽ48)
የስምዖን ጥንካሬ ያስደንቃል፤ ከባዱን ሃላፊነት ለመወጣት እስከ እኩለ ሌሊት ይሰሩ ነበር፡፡ ስምዖን ለመጽሐፍ የነበራቸው ፍቅር እንዲህ በደብዳቤ መልክ ተቀምጧል። “በሺህ ከሚቆጠሩ የልብ ወዳጆቼ ከእናንተ አልፌ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጥብቅ ወዳጆችን መጻሕፍትን አፈራሁ። ይህ ወዳጅነቴ ከኢትዮጵያ እስከ አሜሪካ፣ ከኮሎራዶ፣ ዴንቨር አውሮራ ከተማ አብያተ መጻህፍት ድረስ  በብዛት የሰፈሩትን መጻሕፍት ያጠቃልላል። ወዳጅና ባልንጀራነቴ። ለሁላችሁም ሰላምታ አቀርብላችኋለሁ”
ስምዖን የንባብ ባህል መቀዛቀዝን አስመልክቶ የራሳቸውን ቁጭት እንዲህ ይናገራሉ፤ “አሁን በትምህርት ተቋማት የሚደራጁ አብያተ መጻሕፍት በባለሙያ የመመራታቸው ጉዳይ እጅግ አጠያያቂ እየሆነ መጥቷል። በመሆኑም ለቤተ መጽሐፍትና ለንባብ መዳከም ዋነኛ ተጠያቂ ትምህርት ሚኒስቴር እንደሆነ አስባለሁ” ለአብያተ መጻሕፍት ይበልጥ ማበብና ለንባብ ባሕል መጠናከር ዋነኛ መሠረት ትምህርት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አሁንም ቢሆንም የበኩሉን ሚና ለመወጣት የተበላሹትን አሠራሮች መርምሮ ማስተካከል እንደሚገባው ስምዖን አበክሮ ያስባል... (ገጽ 57)
ስምዖን በሃይማኖታቸው ለፈጣሪያቸው ታማኝ፣ በማሕበራዊ ሕይወታቸው ሰፊ ዋርካ - ሰው የሚጠለልባቸው እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ለትዳራቸውም ታማኝ፣ ልጆቻቸውንም በግብረገብ ያነጹ ናቸው። "እኔ የማውቀው ሕዝብ ሲያውቅ ነው።" ብለው የሚያምኑ ትጉ ሰው መሆናቸውም በመጽሐፉ ተመልክቷል፡፡
አንባቢ ተኚህ ብርቱ ኢትዮጵያዊ ብዙ የሚማረው ቁምነገር ስላለ መጽሐፉ ሊነበብ ይገባዋል።


Read 333 times