Tuesday, 20 July 2021 00:00

ለማንም የተፃፈ ደብዳቤ እነሆ የዘመንህ ቅዝምዝም ቅኔ…

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(6 votes)


         እንደምን ነህ ማንም? ኑሮ እንዴት ይዞሃል? አለሁ እኔ ምንም … አለሁ እንደምንም፡፡ አንተ ግን እንዴት ነህ? በሎሬት ፀጋዬ ሰላምታ ቅማንት ነህ ሽናሻ፣ አገው ነህ ወላይታ፣ ሃድያ ነህ ከምባታ … ወይስ ካህን ነህ አረመኔ፣ ገበሬ ነህ ወታደር፣ ባላባት ነህ ወይስ ገባር… ክርስቲያን ነህ ወይስ ሙስሊም ወይስ ሌላ ወይስ ምንም … ብቻ ማንም ሁን፡፡ ማንም ሆይ ሰላምታዬ ላንተ ይሁን ብየሃለሁ፡፡ ብትመልስልኝ ደግ ባትመልስልኝ ግድ የለም፡፡
ይድረስ ላንተ ለማላውቅህ
ለይድረስ ላንተ ለማላውቅህ
ወንድሜ ሩቅ ለማልፍህ
ለምታውቀኝ ለማላውቅህ ለምታየኝ
ለማላይህ
ማነህ ባክህ?
ሳትወደኝም ሳታምነኝም አጢነህ
ለምትፈራኝ
ስናገርህ አጠንቅረህ አተኩረህ
ለምትሰማኝ
ይድረስ ለክቡር ወንድሜ አረህ ዟሪው
ለገታሩ
ለሩቅ ገጠሬ ነባሩ
ለማላውቅህ ለዳርዳሩ

አገው ነህ ወይስ ሺናሻ
ቅማንቴ ነህ ወይ ፈላሻ
ስምህ የሆነብን ግርሻ
ግራ ጎንደር መተከል
ባላዋቂ የምላስ ቅርስ፣ የዘር ንፍገት
ስትቀበል
ያለዕዳህ ስምህ ሲበከል
እምትችል እምትቀበል፣ እማትሞት
እማትነቀል
ማነህ?
(እሳት ወይ አበባ፣
ጸጋየ ገብረመድህን፤ ገጽ 23)                         
አንተስ እንደምን ነህ ላልከው … እኔማ ምን እሆናለሁ፡፡ በዮሐንስ አድማሱ ሰላምታ ‹‹ያቀረብኩትን ሀሳብ አይሁድ ክርስቶስን በዕለተ ዓርብ ቸንክረው እንደሰቀሉት ሰቀሉት፡፡ ኋላም በማንም ስብሰባ ላይ ‹ጥላቻ፣ ብሔር፣ ጠባብነት፣ ድንበር፣ እምነት› … እቶፈንቶ በተባለ ከፈን ከፍነው በአይቻልም በተባለ የሬሳ ሳጥን ዘግተው፣ በግብዝነት መቃብር ውስጥ ቀበሩት።›› እልሃለሁ፡፡ ከዚያም በኋላ እኔ ማንንም መሆንን ሸሽቼ ምንም ሆንኩ፡፡ እናም መንገዳችን ተለያየ፡፡ አንተ ወደ ኤማሆስ፣ እኔ ወደ ቀራንዮ፡፡ አውቃለሁ ማንም ሆይ፤ የኔ መንገድ ወደ ኤማሆስ መስሎ እንደሚታይህ አውቃለሁ፡፡ በዚህ እበልጥሃለሁ … እነሆ አንተ ከጥላቻህ፣ ከውንብድናህ፣ ከድንቁርናህ፣ ከድድብናህ፣ ከጅልግግናህ አዋጥተህ በሰራህልኝ ክንፌ ርቆ መብረር አቅቶኝ ስር ስርህ እውተፈተፋለሁ፡፡
ማንም ሆይ ግን አንተ አንደምን ነህ? ልክ ነህ እጠላሃለሁ፤ እንቅሃለሁ፤ እፀየፍሃለሁ፤ እሰቀቅሃለሁ፤ … እንደ ዝንብ፣ እንደ ትንኝ፣ እንደ አንዳች፣ እንደ ኢምንት አይሃለሁ፡፡ ምክንያቱም … ምክንያቱም … ምክንያቱም በጭካኔ ያለ ፍላጎቴ ዝንታለም የጠቀምከውን ዕድፋም ድሪቶ በላዬ ላይ ጭነህብኛልና፡፡ እናም ርቆ መብረሩ ቀረና አንተ ያወረስከኝን ድሪቶ መጥቀም ሆኗል ስራዬ፡፡ ግን ደግሞ እወድሃለሁ፡፡ አንድ ዓይነት የጥላቻ ወይም የመውደድ ስሜት ጥርግርግ አድርጎ እንዲወስደኝ ከፈቀድኩማ ምኑን እኔን ሆንኩት? ምኑን ባንተ ዕድፋም ኑረት ተመራመርኩት? ምኑን ምንስ ሆነ?
ለመሆኑ የት ነህ? መተማ ነህ ጅማ? ደንቢዶሎ ነህ ደቡብ ወሎ? ነቀምቴ ነህ ዱርቤቴ? ጋምቤላ ነህ ዲላ? ወይስ አክሱም ወይስ ጭሮ? ወይስ ሌላ … ብቻ የትም ሁን፡፡ ሰላምታዬ ይድረስህ።
 ትገርመኛለህ ስታደንቅ በጅምላ፣ ስትተች በጅምላ፣ ስታመልክ በጅምላ፣ ስትበላ፣ ስትጠጣ፣ ስትደግፍ፣ ስትቃወም፣ በጅምላ ነው፡፡ ኸረ አሁን አሁንማ ስትሞትም በጅምላ ሆኗል፡፡ ስትሞትሞትም ‹በስህተት› ሳይቀር በጅምላ ሆኖልሃል። ተነጥሎ መቆምን አታውቅበትም፡፡ ትፈራለህ። ምክንያቱም የተሰጠህ የዝንተ ዓለም ዕድፋም ድሪቶ መንጋነትን እንጂ ተነጥሎ መቆምን አላስተማረህማ፡፡ በየዕለቱ ደም ካዘለ ጭፍግግ ሰማይ ስር ግራ በተጋባ አውድ እንደሚታረዱ በጎች በሰለፍ እየተነዳህ እንደሆነ አያለሁ፡፡ ሁልጊዜ ጭልፊት እንዳዩ እናት የሌላቸው መንጋ የዶሮ ጫጩቶች፣ መጠለያ ፍለጋ በመንጋ ስትባዝን አይሃለሁ። አሳዛኙ ፍፃሜ ላይቀርልህ ነገር ይህ ሁሉ መሽቆጥቆጥ ለምንህ? ለምንህ? መልስ የለህም አውቃለሁ።
ማንም ሆይ፤ ዛሬስ ስትበላ ስትጠጣ፣ ስትሰራ ለብቻህ ወደ ውስጥ እያነባህ ታንጎራጉራለህ? ዛሬስ የሆነ ዓይነት ሰማያዊ ኃይል መጥቶ ከገባህበት የባርነት ቀንበር ያወጣህ ዘንድ በየዋህነት ታንጋጥጣለህ? ዛሬስ ያለ እቅድ መመራትህን አላቆምክም ይሆን? ለመሆኑ ይህችን የስስት (ምናልባት የቁጣ) ደብዳቤን ለማንበብ የሚያበቃ የንባብ ልምድ አለህ? በአድዋ ጦርነት ወቅት በጋሻና ጎራዴ ያሸነፍከውን ሰራዊት ከ40 ዓመታት በኋላም በጋሻና ጎራዴ እንደጠበቅኸው አትረሳውም መቼስ? ዛሬስ ባለህበት እየረገጥህ መሆኑ ታውቆሃል? ተመልከት እንደ ሀገር ትናንት ብቅ ያለችው ሴራሊዮን በአስተዳደር ዝመና ምን ያህል እንደበለጠችህ! ማንም ሆይ፤ ያንተ ነገር ገና ያለቀለት አይመስል፡፡ ነገርህ ህብሩ የተሳከረና የተወታተበ ነው፡፡ ነጻ ለመውጣት የቋመጥኸውን ያህል ሌሎችን ለመጨቆን ያቆበቆበ ድብቅ ማንነት እንዳለህም አያለሁ። ዘመኑን ለመቅደም ገና አልተዘጋጀህም፡፡  
ማንም ሆይ፤ ስለ እኔማ ምኑን ልንገርህ? ባንተ እድፋም የኑሮ ዘይቤ ግርር ድንግርግርርርርር እንደተሰኘሁ፣ ሁልጊዜ እንደ እንግዳ እንደ ቤት የለሽ መንገደኛ አለሁልህ፡፡ አይገርምህም፤ ሺህ ዓመት እንድኖር ቢፈረድብኝ እንኳን ካንተ የኑሮ ዘይቤ ጋር የምገጥም አይመስለኝም፤ በፍፁም፡፡ ማንም ሆይ፤ ነገር አረዘምኩብህ አይደል? በል ከአንተ አብራክ የወጣው ትንታግ ብዕረኛ ዮሐንስ አድማሱ በአንድ ወቅት ከፃፈልህና ቅድም ከቀነጨብኩልህ እንባ ቀረሽ ደብዳቤ ላይ የምትከተለዋን ላስነብብህና ልሰናበትህ፡፡ ጽሑፉ ዮሐንስ አድማሱ በአንድ የመምህራን ስብሰባ ላይ የታዘበውና ለአንድ ወዳጁ (ምናልባት ጉዳዩን በሚገባ ለሚያውቅ ጓደኛው) የላከለት፣ በብልህ ዘይቤ የተፃፈ ድንቅ ደብዳቤ ነው። የዮሐንስ ትዝብት፣ ምሬት ከአንድ ስብሰባ ባሻገር ሀገርን የሚያክል ምናልባት ሀገርን የሚወክል ነበር፡፡ እነሆኝ አንብቡት…
"ያቀረብነው ሀሳብ አይሁድ ክርስቶስን በዕለተ ዓርብ ቸንክረው እንደሰቀሉት በዕለተ ሰሉስ (ማክሰኞ ህዳር 5 የአቡዬ ዕለተ) ሰቀሉት፡፡ ኋላም በመምህራን ስብሰባ ላይ (ረቡዕ ህዳር 6 የኢየሱስ ዕለት) “ውሳኔ” በተባለ ከፈን ከፍነው ባይቻልም የሬሳ ሳጥን ዘግተው፣ በግብዝነት መቃብር ውስጥ ቀበሩት፡፡ ትንሳኤ ያለውም አይመስልም። ረቡዕ ዕለት በመምህራኑ ስብሰባ ጊዜ የነበረውን ግድየለሽነት፣ ግብዝነት፣ ተደጋጊነት፣ ንዝህላልነት፣ በአንድ ቃል ሃላፊ ቢስነት አታንሳው፡፡ እንደተለመደው የተናገሩት በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ፡፡ …. የቀሩት ግን አፋቸው ቅርቃር የተቀረቀረበት የሚመስል አየር ለመሳብ አፍንጫቸውንና አፋቸውን ከመክፈት ከመዝጋት በቀር ከላይ አፋቸው ከታች አፋቸው አንዲት ቅንጣት ቃል አልተናገሩም፡፡ በተለይ ዕርር ትክን ያደረገኝ ይሄ ነው፡፡ የህሊና ብርሃናቸው የጠፋባቸው ይመስለኛል። ወይም በዘመናችን ያለው ትውልድ ተኮላሽቷል። አጋሰስ ትውልድ ይሉሃል ይሄ ነው፡፡ ምናልባት ተሳስቼ ይሆናል፣ ምናልባት የዚህ ዓለም ፈሊጥ የመኖር ወይም ከመኖር የሚገኘው ጥበብ አልተከሰተልኝ ይሆናል፡፡ የኑሮ ጥበብ ዝምታ ይሆን ነገሩ? ብዙ ነው፤ ህብሩም የተሳከረ፣ ስልቱ የተባ፣ አስተሳሰቡ የተዛባ ነው፡፡ እንኳን በዚህ ደብዳቤ በሌላም በሶስት አራት ደብዳቤ አይከተትም፡፡ ለዚች አገር እድል ፈንተዋ ፅዋ ተርታዋ ምን ይሆን? ብዬ አስባለሁ፡፡ እንጃ የምለምነው ግን የዕድሜ አተላ ሆና እንዳትቀር ነው፡፡ እኛስ ከፋም ለማም ደህና ኑሮ እንኖራለን፡፡ ይህ ስም የለሹ ህዝብስ…;
(ህዳር 7 ቀን 1965 ዓ.ም የተፃፈ ደብዳቤ ውስጥ የተቀነጨበ፤ ምንጭ፡ እስኪ ተጠየቁ)

Read 12256 times