Saturday, 17 July 2021 15:00

“ስተዋወቅህ ደስ ይለኛል”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

   እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ይኸው ሐምሌም አንድ ሦስተኛዋ ሽው አለች፡፡ 2014 እየደረሰ ነው! (የሠይጣንን ጆሮ ይድፈነው ማለት ይሄኔ ነው፡፡)
“ሄሎ፣ አጅሬው!"
”ሄሎ እንዴት ነህ?”
“ስማ፣ ደስ አላለህም?”
“ምኑ?”
“እንግሊዝ ተሸነፈች አይደል! ጣልያንን ደግፌ አላወቅም፡፡ እሁድ እለት ዋንጫውን ሲወስዱ እንዴት ደስ እንዳለኝ አልነግርህም! ከመቀመጫዬ ተነስቼ ነው ያጨበጨብኩት። ገና፣ ገና የእጇን ባታገኝ ምን አለ በለኝ!”
በአሁኑ ሰዓት አንድ ሺህ አንድ የሚያሳስቡን ነገሮች እያሉ በእንግሊዝ ኳስ መሸነፍና አለመሸነፍ እንወዛገብ! ይኸኛው ግን ነገሩ ኳስ አልነበረም፡፡ የምር ግን...አሁን ለአንዳንድ ክፍሎች ያለን አመለካከት እየተለወጠ ነው፡፡ “ሰዋችን ለካስ ውስጥ ለውስጥ እንዲህ ሲሸርቡብን ነው የኖሩት!” እያለ ነው፡፡ አባቶቻችን “የእንግሊዝ ሆድ አይታወቅም...” ይሉ የነበሩት እኮ ከመሬት ተነስተው አልነበረም የሚያስብሉ ብዙ ነገሮች እያየን ነው፡፡ እናማ...የኳሱም፣ የምኑም የምናምኑም ውጤት ዞሮ፣ ዞሮ ከዚህ ጋር የሚያያዝ እየሆነ ነው። (ትረምፕን በመረጥኩ ኖሮ የምትሉ ዳያስፖራ ወዳጆቻችን፤ ነገርዬው ‘ስልቻ ቀልቀሎ፣ ቀልቀሎ ስልቻ’ አይመስላችሁም!)
እናማ... ምን መሰላችሁ እኛ ግለሰቦቹ ብቻ ሳንሆን ሀገራትም በማስመሰል የሚኖሩበት ዘመን ነው፡፡ አሀ... “ከኢትዮጵያ ጋር የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ወዳጅነት አለን...” “ወንድማማች የሆነው የእኛና የኢትዮጵያ ህዝብ ...” ምናምን የምትለዋ እኮ በቃ አጭቤ ቦተሊካ ነች፡፡
የቫት የለበት፣ የኮቴ የለበት...
“እንዴት ነህ!” አንዳችን  በሌላኛችን ላይ መጠምጠም፣ መተቃቀፍ፡፡ ከዛ ደግሞ ጀርባ ቸብ፣ ቸብ፡፡ እና ጀርባ ቸብ፣ ቸብ ስንደራረግ እውነት ናፍቆት ነው! ልከ ነዋ ይሄኔ እኮ ስንታችን በሆዳችን... አለ አይደል... “እንደው አንተን እንዲህ ጀርባ ጀርባህን ብሎ ልክ የሚያገባልኝ ሰው ይጥፋ!” እንል ይሆናላ። ወይ ደግሞ ጀርባ ቸብ፣ ቸብ እያደረግን "ሰው በልቶ ሆዱ ይወፍራል እንጂ ጀርባ እንዲህ ይወፍራል! ይሄኔ የመሥሪያ ቤቱን በጀት ሲሶውን ወደ ኪሱ ላፍ አድርጎ ነው!” እንል ይሆናል፡፡
የአንዳንዱ ሰው አጨባበጥ እንዴት ነው! ለምትጨብጡት ሰው ጣቶችም እዘኑላቸዋ! በሆዳችሁ እኮ... “የእናቴ የአባቴ አምላክ እንዲህ ጭብጥብጥ አድርጎ ይጣልሽ!” የምትሉ ያስመስልባችኋል፡፡
“ስላገኘሁህ ደስ ይለኛል፡፡” ስማቸውን አይተዋወቁ! እንደውም ተያይተው አያውቁ... እንዴት ነው ስላገኘው ደስ የሚለው! በቃ ቀላል ሰላምታ ተለዋውጦ መለያየት አይበቃም እንዴ! ቲራቲሩን ምን አመጣው!
“ቅድም አብራኝ የነበረችውን አታውቃትም?”
“አላውቃትም፡፡"
“እንዴት ነው እሷን የማታውቀው?”
“አላውቃትም... ማነች?”
“የታወቀች ፋሽን ዲዛይነር ነች፡፡”
እንዴት ነው ነገሩ! “እኔ አንድ ነፍስ አላት የምላት ሱሪ ሰፍታኝ ማስጠበቢያ ግራ ገብቶኝ ደግሞ እከሊት የተባለች ፋሽን ዲዛይነር ልወቅ!"
“ስማኝማ... እዛ ጋ ከቪታራው የምትወጣው ሴትዮ ትታይሀለች?”
“አይ አትታየኝም፣ እባክህ መልካም ፈቃድህ ከሆነ አጉሊ መነጽር አውሰኝና ልያት፡፡ እንዴት ነው እዚሁ በዚሁ የማላያት!”
“ቆይ እንጂ፣ ገና ሞቅ ሳትል እኮ ተንተከተክህ፡፡ ሞቅ ሳይል የሚንተከተክ በዝቶ ነው መከራችንን እያየን ያለነው፡፡”
“ጀመረህ እንግዲህ! በቃ ምኑም ምናምኑም ነገር ላይ ፖለቲካ ካልሰነቀራችሁ አይሆንላችሁም!”
“አየህ አንተ ራስህ እኮ ቅልጥ ያለ ፖለቲካ ነው እየተናገርክ ያለኸው! የምናወራው  ሁለታችን አንተ ግን ‘ፖለቲካ ካልሰነቀራችሁ አይሆንላችሁም’ ብለህ ሁላችንንም ፈረጅከን!"
“እንዲህ ነገር እየመዘዛችሁ ነው እኮ የሰዉን ናላ እያዞራችሁ ያላችሁት!”
“አንተ! አንተ! አሁን ያልካትን እኮ እኔ ነኝ ያለ አክቲቪስት አይናገራትም! አንቺ ሰውዬ በር ዘግተሽ ኮሚኒስት ማኒፌስቶ ምናምን ትገርቢያለሽ እንዴ!”
“ወይ ጣጣ! እሺ፣ ያልካትን ሴትዮ አየኋት፣ እና ምን ይጠበስ!”
“አላውቃትም በለኝና ሲገርመኝ እንዳላድር!”
“ለእኔ ስትል ሲገርምህ ማደር አይደለም ሲገርምህ ክረም፡፡ በቃ አላውቃትም፡፡ እና ፌስቡክ ላይ የሆነ  ሀሽታግ ምናምን የሚል ነገር ክፈትና ሼር ተደራረጉብኛ!”
“መገናኛ ምን የመሰለ ሹሮ ቤት ያላት እንኳን!”
ጎሽ! የፋሽን ዲዛይነሯ ነገር ሲገርመን ጭራሽ ወደባለ ሹሮ ቤቷ!
እኔ የምለው... በጽሁፍ መልእክት “የምናከብራችሁ ደንበኞቻችን...” ምናምን በሚል የምትልኩልን ድርጅቶች፣ ተቋማት እስቲ እናንተ እንኳን ‘ፒስ’ ስጡንማ! አታዋክቡንም! እኛን ሳይሆን ከእኛ የምትመጣውን ብሪቱን ነው የምታከብሩት፡፡ እውነት ብታከብሩን ኖሮማ የተለያዩ አገልግሎቶችን ፈልግን ስንመጣ የተጣመመች አግዳሚ ወንበር ማቅረብ ማንን ገደለ! ምስኪን ተገልጋዮቻችን ሊሠራ እየተቻለ በስነምግባር ጉድለት ጉዳዮችን እያንጠለጠሉ ማማረር ምን የሚሉት ማክበር ነው! ትናንት ያስገባነው ማመልከቻ ዛሬ “ጠፍቷል መዝገብ ቤት ይፈለግ...” ብሎ ነገር ምን የሚሉት ማክበር ነው! እንደውም፣ በቃ... ሆድ ያባውን ብቅል እስኪያወጣው መጠበቁ ብቅሉ ለመገኘቱ አስተማማኝ ስላልሆነ (ቂ...ቂ...ቂ...) ያለብቅል እናውጣው። “የምናከብራችሁ...” አይነት የቃላት ትከሻ መታ፣ መታ ስትጽፉ በሆዳችሁ “እንዲህ ጀርባ፣ ጀርባውን ወግሮ ልክ ማግባት ነው!” እንደምትሉ ዲሞክራሲያዊ የመጠርጠር መብታችንን በመጠቀም እንጠረጥራለን፡፡ አቤቱታ ስናስገባም፣ የአገልግሎት ክፍያ ስንፈጽምም ግንባራችሁን ሳምንት ተዘፍዝፎ የከረመ ቀሺም ፎጣ ምናምን የምታስመስሉት ምን የሚሉት ማክበር ነው! “ስንተዋወቅ አንተናነቅ፣” የምትለዋ አባባል ከአገልግሎት ውጪ ባትሆን ኖሮ እንጠቀማት ነበር፡፡
እናላችሁ... እንበልና ከሰውየው ጋር እንዲሁ በዓይን ትተዋወቃላችሁ፡፡ ንግግር ምናምን የላችሁም፡፡ አንድ ቀን ታዲያ ሁለታችሁንም ከሚያውቅ ሰው ጋር ሳላችሁ እሱዬው ይመጣል፡፡ አንደነገሩ አንገት ሰበር፣ ሰበር ታደርጋላችሁ፡፡ የሁለታችሁም ወዳጅ... “እናንተ አትተዋወቁም እንዴ!” አይነት ነገር ሲል፡ ቀሸም ባለ ሀፍረት “በዓይን እንተዋወቀለን...” ትላላችሁ፡፡ ይሄኔ የሁለታችሁም ወዳጅ የሆነው ሰው... “በሉ ከዛሬ ጀምሮ በደንብ ሰላም ተባባሉ...” ምናምን ብሎ ያጨባብጣችኋል፡፡ ይሄኔ ሰውዬው ምን ቢል ጥሩ ነው...
“አንተን በማወቄ በጣም ደስ ይለኛል...፣” ምናምን እያለ እጃችሁን ጠበቅ አድርጎ ይጨብጣችኋል፡፡ እዚህ ላይ የዋሆቹ እኛ...“እኔ ከሀያ አንዱ የቤተሰብ ጉባኤ አባላት ሀያዎቹ ጀርባቸውን አዙረውብኝ ለካስ በጣም ሊተዋወቀኝ የሚፈልግ ሰው ሞልቶ ነበር...” ምናምን በሚል በትከሻችን ስፋት ላይ ዘጠኝ ሴንቲ ሜትር እንጨምራለን። አሀ... አካሄዳችን የትከሻው ስፋት ዘጠኝ ሴንቲ ሜትር እንደጨመረ ሰው ነዋ!
ጨዋታው የሚመጣው ከተለያያችሁ በኋላ ነው፡፡ እናማ... አዲሱ ጓደኛችሁ ሁለታችሁንም ለሚያውቀው ሰው ምን ቢለው ጥሩ ነው...“አንተ ስለሆንከ እንጂ አይደለም ልጨብጠው ዓይኑን  ባላየው ደስታዬ ነበር፡፡”
“ለምን? ያደረገህ ነገር አለ?”
“እንደውም፡፡ መጀመሪያውኑ መች እንተዋወቅና!”
“ታዲያ ይህን ያህል የምትጠላው ለምንድነው?”
“እኔ አንጃ! ገና ሳየው ነው ደሜ የሚፈላው!” (ደምህ እንዲህ በቀላሉ የሚፈላ ከሆነ ባለቤትህን ነጋ ጠባ “ያልፈላ ሹሮ ሰጠሽኝ!” ብለህ መከራዋን የምታበላት ለምንድነው! ኖ፣ እንደዛ አትውሰደው! እኛ ያልፈላ ሹሮ ዘወትር እንደምትበላ ለማሳበቅ ሳይሆን ደምህም ፈልቶ፣ ሹሮውም ፈልቶ እንዴት አብረው መኖር ይችላሉ ብለን ነው! ቂ...ቂ...ቂ...)
እናላችሁ... “ስተዋወቅህ ደስ ይለኛል፣” የሚለው ሰው ሁሉ ‘ከአንድ ሳጥን የወጣ’ አይደለም፣ ለማለት ያህል ነው፡፡
ደህና ሰንበቱልኝማ!


Read 1759 times