Monday, 19 July 2021 00:00

የትንበያ ቁምነገር - መልካም ምኞቶችን ለማሳካት፣ አደጋዎችን ለማክሸፍ!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

    • የተሳኩና ያልተሳኩ ምኞቶች፣ የከሸፉና ያልከሸፉ አደጋዎች!
                      
              ለአገር ሰላም፣ ለዜጎች ሕይወትና ለብልፅግና የተወጠኑ እቅዶቻችንና መልካም ምኞቶቻችን፣ ምን ያህል ተሳክተዋል?
በአንድ በኩል፣ የሕዳሴ ግድብ አስደሳች የስኬት ጉዞ አለልን። በሌላ በኩል ደግሞ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ከባድ ሸክም አለብን።
ለአምስት ዓመታት እየተባባሰ የነበረው የአገራችን ቀውስና ምስቅልቅል ቀስ በቀስ እየቀነሰ፣ የመረጋጋት አዝማሚያ በበርካታ ቦታዎች አይተናል። ጥሩ ጅምር ነው። ተስፋ ይሰጣል።
ከጦርነት አደጋዎችና ከቀውስ ስጋቶች መካከልስ፣ ምን ያህሎችን አክሽፈናል?
በአንድ በኩል፣ የዘንድሮው ምርጫ በሰላም ተካሂዷል። በማያወዛግብ የምርጫ ውጤት እፎይታ ተገኝቷል። ከምርጫው በሰላም ተርፈናል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ለምርጫ በሰላም አለመድረሳችን ያሳዝናል። የዛሬ ዓመት በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል የተፈጠረው አመፅ እንዲሁም በትግራይ ክልል የተከሰተው  ጦርነት ወርዶብናል አንዳንዶቹን አደጋዎች ማስቀረት ተችሏል፤ ወይም ገና ከጅምራቸው ከሽፈዋል። ትልቅ እፎይታ ነው። አንዳንዶቹ አደጋዎች ደግሞ፣ ባይከሽፉም በጊዜ በርደዋል። አሳዛኙ ነገር፣ ልናስቀራቸውና ዘላቂ መፍትሄ ልናበጅላቸው ያልተቻሉን አደጋዎች መኖራቸው ነው።
ገና ከጦርነት አልተላቀቅንም። የሰላም ምኞታችን፣ ገና አልሞላልንም።
ደግነቱ፣ የተሳኩ የተስፋ ትንበያዎች አሉ። የሕዳሴ ግድብ ግንባታ፣ ከዓመት ዓመት እየተሟላ እየሰፋ የመጣ ትልቅ ስኬት ነው። ስራው ቀላል አይደለም። ፈተናዎቹና እንቅፋቶቹ፣ ከባድና ብዙ ናቸው። በዶላር እጥረትና በኢኮኖሚ ችግር ላይ ጦርነት ታክሎበት የሕዳሴ ግድብ ፈተና በርትቷል። በግብፅ መንግስት መሪነት በየጊዜው የተጋረጡ መሰናክሎች፣ ለአፍታ ጋብ አላሉም።
እንዲያም ሆኖ፣ አደጋዎቹ እየከሸፉ፣ መልካም ምኞቶችና የየዓመቱ እቅዶች ደግሞ እየተሳኩ ናቸው። የሕዳሴ ግድብ፣ ዘንድሮም እየሞላልን ነው። በአምናው ላይ ተጨምሮ፣ የግድቡ ውሃ በሰፊው ሲንጣለል ለማየት የምንበቃበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። አትጠራጠሩ፡፡ የስጋት ትንበያ በጥንቃቄ የከሸፈበት፣ የተስፋ ትንበያ ደግሞ በጥረትና በፅናት የተሳካበት ግሩም ምሳሌ ነው - የሕዳሴ ግድብ።   
ይህም ብቻ አይደለም።
ቀውስን ያላስከተለ፣ በሰላም የተካሄደና በማያወዛግብ ውጤት ወደ እፎይታ የደረሰው የዘንድሮው የፖለቲካ ምርጫም፣ ሳይጠቀስ አይታለፍም። ምርጫው፣ እንደፈራነው ለቀውስና ለነውጥ አልዳረገንም። እንደተስፋችን በሰላም ተርፈናል። እፎይታን አግኝተናል።
በእርግጥ፣ ሁሉም ነገር አልጋ ባልጋ አልሆነም። ከመልካም ምኞትና ከስኬት ትንበያ ጎን ለጎን፣ አብዛኞቹ የአገራችን ጉዳዮች ለአደጋ የተጋለጡ ጉዳዮች ናቸው። ለዓመት ለሁለት ዓመት እንቅልፍ ሲነሱን የቆዩ የስጋት ትንበያዎችን አስታውሱ።
“ከምርጫው በሰላምና በጤና እንተርፋለን ወይ?” ብለን በስጋት ተጠያይቀናል። ደጋግሞም አይፈረድብንም። ቢጨንቀን ቢቸግረን ነው። ከዓመት ከሁለት ዓመት በፊት የነበረውን የአገራችን የፖለቲካ ቀውስና የነውጥ ምስቅልቅል አትረሱትም። በዚህ ላይ፣ የምርጫ ትኩሳት ሲደረብበት፣ በእሳት ላይ ቤንዚን እንደ ማለት ነው። ምን ጥያቄ አለው? የአገራችን የፖለቲካ ፉክክርና ውድድር ምንኛ አጥፊ እንደሆነ በተደጋጋሚ አይተናል።
ከበርካታ የአፍሪካና የአረብ አገራት አሳዛኝ የቀውስ ታሪክ ብዙም አይለይም- የአገራችን አሳዛኝ የፖለቲካ ቀውስ። ፉክክር ማለት፣ የመጠፋፋ ፉከራ ነው የሚመስለን። ውድድር ማለት፣ “ወረድ እንውድ” እያሉ ለሞት ሽረት ፍልሚያ የሚገባበዙበት ድግስ መስሎ ታየናል።
ታዲያ፣ “ከዚህ ምርጫ በሰላም እንተርፋለን ወይ?” ብለን በስጋት ብናሰላስል፣ የጥፋት አደጋዎች በርክተው ቢታዩን ይገርማል? አይገርምም፡፡
 ምርጫ በኋላቀር ፖለቲካ ውስጥ ሁሌም ለአደጋ የተጋለጠ ነው። “አደጋ አለው” በማለት ስጋታቸውን የሚገልፁ ማስጠንቀቂ ደውሎችና ትንበያዎች ቢጮሁ፤ ተገቢ ነው።
ከማስተዋል፣ ከማገናዘብና ከእውቀት የሚመነጩ፣ “ሰው ሰራሽ” የስጋት ትንበያዎች፣ መንታ ባሕርይ አላቸው።
በአንድ በኩል፣ የስጋት ትንበያዎች፣ አይቀሬ እውነታን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ “በዚህ አነዳድህ፣ በጭፍን ስሜት መንገድህ፣  በጥንቃቄ አልባ አዋዋልህ… ለበሽታ ወረርሽኝ፣ ለፀብና ለመኪና አደጋ ራስህን ትዳረጋለህ” እንደ ማለት አስቡት።
ከእውነተኛ መረጃና ከእውቀት የመነጨ የስጋት ትንበያ፣ አይቀሬ እውነታን አስቀድሞ ይገልፅልናል። “በዚህ የጥፋት መንገዳችን፣ መጥፋታችን አይቀሬ ነው”… ይለናል የአደጋ ወይም የስጋት ትንበያ። አይቀሬ እውነትነቱን አስረግጦ ይነግረናል።
ግን ደግሞ፣የስጋት ትንቢያ፣ “አይቀሬ” አይደለም። የስጋት ትንቢያ፣”በምንም መንገድ ብንጓዝ፣ መጥፋታችን አይቀሬ ነው” አይልም። እንዲያውም፤ ማስጠንቀቂያ ብቻ ሳይሆን፣ ምክር አዘል መልዕክት ነው- ትንበያው። “በጥፋት መንገድ ከቀጠልን እንጠፋለን። አይቀርልንም። መንገዳችንን ካስተካከልን ግን አደጋውን እናስቀራለን። “ የሚል ነው- የትንበያው የተሟላ መልዕክት።
በሌላ አነጋገር፣ የአደጋ ትንበያ ትልቁ ቁም ነገር፣ ከአደጋው ለማምለጥና ትንበያውን ለማክሸፍ መጥቀሙ ነው። ለዘንድሮው ምርጫም የጠቀመን ይመስላል።
አብዛኛው ኢትዮጵያዊ፣ አነሰም በዛም፣ በፖለቲካ ቀውስና በአደገኛ መዘዞቹ በቀጥታ ተጎድቷል። የምርጫ ግርግር፣ በጥንቃቄ ካልተገታ፣ አገርን የሚናውጥ ሕይወትን የሚቀጥፍ፣ ኑሮን የሚያመሳቅል እልፍ መዓት  እንደሚያስከትል በተደጋጋሚ  ታይቷል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞችም፣ የአገራችንን የፖለቲካ ቀውስ ከኛው ጋር አብረው አይተዋል። በምርጫ ሰበብ የሚከሰቱ አደጋዎች፣ የእውነት አደጋዎች እንደሆኑ፣ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች፣ በትንሹም ቢሆን ተገንዝበዋል። ባይገነዘቡ ኖሮ፣ መረን ከለቀቀ ነውጠኛ የምርጫ ዘመቻ ቆጠብ ይሉ ነበር?
ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች፣ ከድሮው የትንቅንቅ ግብግብ፣ ከልማዳዊው የሞት ሽረት አባዜ፣ ቆጠብ ማለታቸው ረድቶናል። ከድሮውና ከልማዳዊው አደገኛ የጥፋት መንገድ ፈቀቅ ማለታቸው፤ ጠቅሞናል። በአጭሩ የስጋት ትንቢያ፣ አደጋዎችን ለማስቀረት፣ ትንበያዎችን ለማክሸፍ አግዞናል። የምርጫ ቦርድ፣ ህግና ሥርዓትን በፅናት ይዞ፣በብቃት መትጋቱ ሳይዘነጋ ማለት ነው፡፡
 በእርግጥ፣ ያላመለጥናቸው አደጋዎች፣ ያላከሸፍናቸው ትንበያዎች አሉ። እንዲያውም፣ አንዳንዶቹ አደጋዎች፣ ከስጋታችንም የባሱ አስፈሪና አጥፊ ሆነውብና።
አዎ፣”ከምርጫው በሰላም እንተርፋለን ወይ?” ከሚለው የስጋት ጥያቄ እረፍት አግኝተናል። እፎይ ወደሚያሰኝ ውጤት ደርሰናል። በሰላም ተርፈናል። ነገር ግን፤  “ለምርጫው በሰላም  እንደርሳለን ወይ?” ብለን መጠየቅ ነበረብን። በሰላም ለምርጫው አልደረስንም። ብዙ ሰዎች ለምርጫው በህይወት አልደረሱም።
የዛሬ አመት፣ የአገራችን ህልውናና ሰላም፣ ምን አይነት አደጋ ውስጥ ገብቶ እንደነበር አስታውሱ። በተለይ ከወሎ እስከ አዲስ አበባ፣ ከወለጋ እስከ ሞያሌ፣ ከአርሲ እስከ ሀረርጌ፣ … ከፈራነውም የከፋ አመፅ ሲፈጠር አይተናል። ብዙ ጥፋትም ተፈጽሟል። የፈራነው ደርሷል፤ ለዚያውም ከፈራነው በከፋ ፍጥነት። የስጋት ትንበያው አልከሸፈም። አስፈሪው አደጋ በእውን ደርሷልና።
በቤንሻንጉልና በደቡብ ክልል የተከሰቱ ተደጋጋሚ አመጾችና ግጭቶች፣ ጥቃቶችና ጥፋቶች ጥቂት አይደሉም። ስንት አደጋ እየደረሰ፣ ስንት ጊዜ በስንት ቦታ የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ሃይል እንደተሰማራ፣ ስንት “ኮማንድ ፖስት” እንዳስፈለገ አስቡት።
ከዚያ ደግሞ፣ በትግራይ ክልል እስካሁን እልባት ያላገኘው፣ እጅግ ከባድና በጣም አስፈሪ አደጋ መጣ። ፈፅሞ ያልተጠበቀ አደጋ ግን አይደለም፡፡ ክፋቱ ደግሞ፣ የስጋት ትንበያው አልከሸፈም። አደጋው ደግሞ፣ ከትንበያው የባሰ ነው። የጉዳቱ ብዛትና መጠንም፣ የዚያኑ ያህል አሳዛኝና ዘግናኝ ሆኗል።
የተሳኩልን የሰላምና የግንባታ ምኞቶች አሉ። በጥረትና በጥበብ፣ በርካታ የተስፋ ትንቢቶች ተሳክተዋል።  አንዳዶቹ የተስፋ ትንቢያዎች፣ከምኞታችን በላቀ ብቃትና ፍጥነት በእውን ሲሳካ አይተናል፡፡ ከኤርትራ ጋር እንዴት ሰላም እንደወረደ አስቡት፡፡ ድንቅ ነው ይህም ብቻ አይደለም፡፡
ያበረድናቸውና የተሻገርናቸው አደጋዎች፣ ያስቀረናቸው ጥፋቶች፣ ያከሸፍናቸው የስጋት ትንበያዎችም በርካታ ናቸው። ከእውቀት የመነጨ የአደጋ ትንታኔና የስጋት ትንበያ፣ ከአደጋ ለመዳንና ትንበያውን ለማክሸፍ ይጠቅማል።
ግን፣ ገና ያላሳካናቸው ምኞቶች፣ ያላከሸፍናቸው አደጋዎች፣ መላ ያላበጀንላቸው እቅዶች፣ በመፍትሔ ያልቋጨናቸው መከራዎች አሉብን። ደግሞም፣ ጥቂት አይደሉም።
 ቀስ በቀስ አገርን የማረጋጋት፣ የበሽታ ወረርሽንን የመከላከል፣ ኢኮኖሚውን ከከፋ ውድቀት የማዳን፣ የሕዳሴ ግድብ የስኬት ጉዞን ወደ ምልዓት የመምራት፣ የፖለቲካ ምርጫውን በሰላም ወደ እፎይታ የማድረስ እቅዶች… ሌሎች በርካታ መልካም ምኞቶች መሳካታቸው ጥሩ ነው። ስኬትን መገንዘብ፣ በዚያው መጠንም ማመስገንና ማድነቅ ተገቢ ነው።
 በጥበብና በፅናት፣ ሰላምን የመፍጠርና የማንገስ፣ ህግና ስርዓትን የማደርጀት፣ የገንዘብ ህትመትን በይበልጥ በመግራት የዋጋ ንረትን የማርገብ፣ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚን የማስፋት፣ በዚህም የግል ኢንቨስትመንት እንዲያብብ፣ የስራ እድሎችንም እንዲያፈራ የመፍቀድ፣ የብሽሽቅና የጥላቻ ፖለቲካን የማብረድ፣ የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካን እያስወገዱ፣ የሃይማኖት ፖለቲካንም እየተከላከሉ የእያንዳንዱን ሰው ህይወት የሚከብር የስልጡን ፖለቲካ ችግኝ መትከል፣ እንዲያቆጠቁጥና እንዲለመልም መጣር፣ …
ገና ብዙ ብዙ ስራ ቀረናል- መልካም ትንበያዎችን ለማሳካት፤ የስጋት ትንበያዎችንም ለማክሸፍ።

Read 12806 times