Saturday, 17 July 2021 14:47

“መሳሪያ ደግኖ ሊወጋን የመጣን ሀይል ፈፅሞ አንታገስም”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

         በቂ የዲፕሎማሲ ሥራ ተሰርቷል ተብሎ አይታመንም

መንግስት ከጥቅምት 24 ቀን 2013  ዓ.ም ጀምሮ ለ8 ወራት የዘለቀ የህግ ማስከበር ዘመቻ በትግራይ ክልል ሲያካሂድ ቆይቶ የተናጥል የተኩስ አቁም አዋጅ በማወጅ የመከላከያ ሰራዊቱን ከክልሉ
ማስውጣቱ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በህወኃት በኩል የተኩስ አቁሙ ውሳኔ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ለዚህ ማሳያው በራያና በአላማጣ፣ በወልቃይትና በተለያዩ አካባቢዎች ትንኮሳና ወረራ መፈጸሙ
ነው በሚል የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ለአማራ ተወላጆችና ለመላው ኢትዮጵያውያን “ህልውናን ለማስጠበቅ በማደርገው ትግል ከጎኔ ቁሙ” የሚል ጥሪ አቅርቧል፡፡ ይህንን ተከትሎም ሌሎች ክልሎች ልዩ ሀይሎቻቸውን ወደዚሁ ግንባር እየላኩ ይገኛሉ፡፡ በዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከአማራ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሸን ዋና ዳሬይክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልለስ አድርጋለች፡፡ እነሆ፡

  እስኪ አሁን በትግራይ አጎራባች ድንበሮች ያሉትን አጠቃላይ ወቅታዊ ሁኔታዎች ምን እንደሚመስሉ  ይግለፁልኝ…
እንደምታስታውሺው የትህነግ ሀይል ህዝቡ ካመጣው ለውጥ ጋር አልስማማም፤ በብልጽግና ውስጥ አልካተትም ብሎ አሻፈረኝ አለ፡፡ ከዚያም ጠቅልሎ መቀሌ ገባ። እዛም ሄዶ አርፎ ቁጭ አላለም፡፡ አጠቃላይ ስራው እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ስለሆነ ሲጠብቀውና ሲያገለግለው የነበረውን የሰሜን እዝ ከጀርባው ወግቶ፣ አማራ ክልል ላይ ጦርነት በመክፈት፣ አሸንፎ አራት ኪሎ ቤተ-መንግስት የመግባት አላማ ነው የነበረው፡፡ አገርን እንደ ፈለገ የማድረግ ስትራቴጂ ነበር ሲገነባ የቆየው፡፡ ከዚህ ቀደም ብሔር ብሔረሰቦች ተዋደውና ተከባብረው የሚኖሩበትን  አገር የትርምስ ማዕከል የማድረግ እጅግ አስቀያሚ የመከፋፈልና የጥላቻ ዘር ሲዘራ መክረሙ የቅርብ ጊዜ ትዝታ  ነው፡፡
የአማራ ህዝብ ደግሞ በማንነቱ የሚኮራ፣ አገሩን የሚወድና ከሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ተዋዶና ተከባብሮ የሚኖር በመሆኑ ጥቅምት 24 የሰሜን ዕዝ ሲወጋና ጥቃት ሲደርስበት እኛም ልዩ ሀይላችንና ሚሊሻዎቻችንን ከመከላከያ ሰራዊታችን ጋር አሰልፈን፣ ትህነግ ለከፈተብን ይፋዊ ጦርነት እጅ አንሰጥም በሚል  የጥፋት ሀይሉ የሚማረከው ተማርኮ የሚሞተው ሞቶ ቀሪው በየጫካውና በየዋሻው እንዲበተን ሆኗል፡፡
ከዚያም የፌደራል መንግስት የትግራይን ህዝብ ለማገዝ ባለው ቅን ፍላጎት የለውጥ ሀይሎችን አዘጋጅቶ ክልሉ ተረጋግቶ እንዲቀጥል  የማድረግ ስራ በጊዜያዊ አስተዳደሩ አማካኝነት ተጀመረ፡፡ ይሁንና የትህነግ ሀይል ቀድሞ ስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ለውጭ የዲፕሎማሲ ተቋማትና ሚዲያዎች ጭምርና በተላላኪዎቹ የማህበራዊ ሚዲያ ፕሮፓጋንዳ በመንዛትና ተፅዕኖ ለመፍጠር በለመደውና በኖረበት የውሸት ትርክትና አሉባልታ “ተዘረፍኩ ተገደልኩ” እያለ፣ በሌላ በኩል እራሱ  ንጹሀንን እየጨፈጨፈ ዓለማቀፉን ማህበረሰብ ሲያጭበረብር ሲያደናግር ቆየ። በዚህም ዓለማቀፉ ማህበረሰብ በሀገራችን ላይ ጫና ለማሳደር ቪዛ እስከመከልከልና የሃገራችንን ገፅታ እስከ ማበላሸት የደረሰ እርምጃ ወስዷል፡፡
የተናጥል ተኩስ አቁሙ ከተደረገ በኋላ በአካባቢው ያለው ሁኔታ ሊረጋጋ ይችላል የሚል እምነት ነበር?
እውነቱን ለመናገር የተናጥል ተኩስ አቁሙ የተወሰነው የትግራይ አርሶ አደር የጥሞና ጊዜ አግኝቶ እርሻ እንዲያርስና ዓለምአቀፉ ማህበረሰብም ያለውን እውነታ እንዲረዳ ብሎም መከላከያ ራሱን አደራጅቶ ለሌላ ስራ እንዲሰማራ በሚል ነው፡፡  መንግስት ይህንን ሲያደርግ ሜዳውም ያው ፈረሱም ያው በሚል፣ ህወኃትም ራሱ አሸባሪ ተብሎ ተፈርጆ እያለ በዚህ የተኩስ አቁም ውሳኔ፣ ህዝቡ ተረጋግቶ ወደ እርሻው ይገባል የሚል ተስፋ ነበረ፡፡ ነገሩ እንደሚጠበቀው ግን አልሆነም፡፡
ባለፈው ረቡዕ “በሶስት የአማራ አጎራባች ድንበሮች ህወኃት በአማራ ህዝብ ላይ ወረራና ትንኮሳ ፈጽሟል፡፡” በሚል ነው የህልውና የማስከበር ዘመቻ ለማድረግ ጥሪ ያቀረባችሁት እስኪ ያብራሩልኝ…
እንደሚታወቀው አጎራባች በመሆናችን በሶስት ግንባር ማለትም በዋግ፣ በራያና፣ በወልቃይት ግንባር  ራሱ የህወኃት ወታደር ብቻውን ሳይሆን ህፃናትን፣ እናቶችን፣ ቄሶችን ሳይቀር ከፊት እያሰለፈ፣ “አማራ ጠላትህ ነው፤ ርስትህን ሊቀማህ ነው” እያለ የውሸት ትርክቱን  እየነገረ ወረራ ለማካሄድ ሙከራ አደረገ፡፡ ይሄ ደግሞ በህልውናችን ላይ የተቃጣ ጥቃትና ወረራ ስለሆነ በህልውናችን ድርድር የለም በሚል የመከላከል ስራ እየሰራን ነው፡፡ አሁን ላይ ከመከላከልም አልፈን ወደ ማጥቃትም እየገባን ነው፡፡
የተናጠል ተኩስ አቁም ስምምነቱን ተከትሎ ጀነራል ባጫ ደበሌ በሰጡት መግለጫ፣ “ይህ  የተኩስ አቁም ውሳኔ የተፈፀመው የትግራይ ህዝብ እንዲያርስ የእፎይታ ጊዜ  እንዲኖረውና እንዲረጋጋ ነው… ከመቀሌ ሰራዊቱን ያስወጣው፣ ትህነግ የተበተነና የደከመ ሀይል ነው፤ከባድ መሳሪያም ሆነ የተደራጀ ሀይል የለውም፤ ከመቀሌ አንዲት ስንዝር ቢያልፍና  ትንኮሳ ቢጀምር ተመልሰን መቀሌ ለመግባት የሚያግደን ሀይል የለም” ብለው ነበር። ህወኃት ከመቀሌ አልፎ ራያ እስኪደርስ ከ160 ኪ.ሜ በላይ ነው፤ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ራያ ሲገቡ የሚከላከል ሰራዊት አንዴት ጠፋ በሚል ህዝቡ ግራ ተጋብቶ እንደነበር ታይቷል፡፡ እርስዎ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?  
ትህነግ አሁንም ቢሆን አቅም የሌለው የደከመ ድርጅት ነው፡፡ አብዛኛው ዋና ዋና የሚባለው አመራር የተገደለበትና የታሰረበት የከሰረ ቡድን ነው፡፡ ቀሪ ሃይል አለ፡፡ ቀሪው ሀይል ደግሞ በውሸትና በማደናገር የህዝብ እንቅስቃሴ ነው የፈጠረው እንጂ ብቻውን የመዋጋት አቅም የለውም፡፡ መንግስት ደግሞ ህዝብ እንዴት እንገድላለን፣ እንዴት ህዝብ እናስጨርሳለን በሚል ሰራዊቱ ብዙ ዋጋ ከፍሏል፡፡ አሁንም ለጀመረው ወረራና ትንኮሳ በራሳችን አቅም እየመከትን ነው አሁን ወደ ማጥቃት የገባነው። ትህነግ የተሰጠውን ዕድል አበላሽቶ አሁን የጀመረውን ወረራ የማያቆም ከሆነ ሰራዊቱም ይገባል፡፡ ፌደራል መንግስቱም መዋጋት አለበት፤ እኛም ጥሪ አስተላልፈናል። ለምን ከተባለ፣ ህወኃት አሸባሪ ቡድን ነው። አሸባሪ ድርጅት ደግሞ ለራሱም ብሔር ጠላት ነው፤ አማራን ብቻ ሳይሆን ነገ ሌላውን ጠላት ያደርጋል፡፡ ስለዚህ አሁን  ፌደራል መንግስቱ ትዕግስት እንጂ ያሳየው ጉዳዩ የመሸነፍ አይደለም፡፡ አሸባሪው ሀይል ለትግራይም ህዝብ ቀንደኛ ጠላት  ነው፡፡ ይሄ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ አሁንም የማያርፍ ከሆነ የህልውና ዘመቻ ስለሆነ ለህልውናችን ወደ ኋላ  አንልም፡፡ ሰሞኑንም መከላከል ላይ ነው የሰነበትነው፡፡ የአማራ ህዝብ በታሪክ በሀቅ የራሱ የነበሩትን፣ ለዘመናት የራሱ የሆኑትን ቦታዎች ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ህወኃት ለ30 ዓመታት ሲያስተዳድር ቆይቶ በብዙ መስዋዕት ለአማራ ተመለሰ፡፡ ገበሬው እያረሰ ባለበት ነው ገበሬውን እየወጋ ህፃናትን ለማስገደል እየተንቀሳቀሰ ያለው፡፡ ይህን የማያቆም ከሆነ መከላከያ ይገባል፡፡ መከላከያ ብቻም አይደልም ሌሎች፤ ብሔር ብሔረሰቦችም ጭምር እገዛ ያደርጋሉ፡፡ ለምሳሌ ኦሮሚያ ልዩ ሃይሉን እስከመላክ የደረሰ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቷል፡፡ ሌሎችም ይህንን እያደረጉ ነው፡፡
እኛ የትግራይን ህዝብ አንነካም፤ አንዋጋም ነገር ግን ሊወጋን የመጣን የትኛውንም ሀይል እንመክታለን እዚህ አጠገባችን መጥቶ የሚወጋንን አንታገስም፡፡ እኛ ትግራይ  ድረስ ሄደን አንዋጋም፤ ጦርነትና ውጊያም አንፈልግም፡፡ ነገር ግን ከተከዜ ማዶ ተሻግሮ እኛን ሊነካ አንፈቅድለትም፤ ዕድልም አንሰጥም፤ ምክንያቱም ለዘመናት ብዙ መስዋዕትነት  ከፍለንበታል፤ ብዙ ህዝብ ገብረንበታል፡፡ ትህነግ ብዙ  ህዝብ  ገድሎብናል፡፡ ከዚህ በኋላ በምናደርገው ትግልም መስዋዕትነት እንከፍላለን፡፡ ጦርነት ስለሆነ ከሁለቱም ወገን ጉዳት እንደሚደርስ እናውቃለን፡፡ ነገር ግን ህልውናን የመጠበቅና የማስከበር ስራና ተገደን የገባንበት ነው፡፡ አለም አቀፉ ማህበረሰብም መንግስት ለትግራይ ህዝብ የሰጠውን ዕድል፣ የተናጠል ተኩስ አቁምን ሁሉ እንዳላየ ያልፋል፡፡ አሸባሪው ሀይል በግልፅ መጥቶ “ካልወጋችሁኝ ጦር ጠማኝ” እያለ ጦር ሲነቅነቅ ለማውገዝ ፍላጎት የለውም። በአጠቃላይ ሚዛናዊ አይደለም፡፡ ይህንን የተቃጣብንን ጥቃት ለመመከት ስንነሳ ፀጥ ረጭ ብሎ የነበረው ዓለማቀፍ ማህበረሰብ እንደገና ጩኸት ይጀምራል፡፡ ይሄ ተቀባይነት የሌለው ሚዛናዊነት የጎደለው እንቅስቃሴ ነው፡፡
የፌደራል መንግስቱ እስካሁን እየታገሰ እድል እየሰጠ ነው ያለው እንጂ ከዚህ በላይ ይታገሳል የሚል ግምገማ የለንም። ይህንን እናንተም የፌደራል አካላትን መጠየቅ ትችላላችሁ፡፡ ነገር ግን ህዝቡ እፎይ እንዲል አርሶ እንዲበላ በተሰጠው የእፎይታ ጊዜ ህዝቡ እንዳይጠቀም ተነስቼ  አጠቃለሁ፤ መከላከያን እወጋለሁና መሳሪያ እቀማለሁ የሚል  ከሆነ የሚታገስ መንግስት አይደለም ያለው፡፡ ህግና ሥርዓት መከበር አለበት የሚል  እምነት አለ፡፡ የትግራይ ህዝብ እንዲያደርስ እድል ስንሰጥ የአማራ አርሶ አደርም እንዲያርስ ዕድል መስጠት ነበረባቸው፡፡ ለነገሩ ትህነግ አፍራሽ ሀይል ስለሆነ ከማፍረስ ውጪ ሊሰራ አይችልም፤ ተፈጥሮው ማፍረስ ነው፡፡ አይሳካላቸውም እንጂ አሁንም አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ገብተን እንመራለን የሚል ትምህክት ውስጥ ያሉ፣ በጣም ጥግ የነካ እሳቤ ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ሲጋቱ ያደጉት ሰይጣናዊ ባህሪያቸውም በቀላሉ የሚለቃቸው አይደለም፡፡ መቼም ቢሆን ይሄ ምኞት አይሳካላቸውም፡፡ ይህንን ትዕቢታቸውን ደግሞ ማስተንፈስ ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ አይነቱ አሸባሪነት እየቀጠለ አገር ሊተረማመስ አይችልም፤ አይገባምም፡፡ ጦርነት የመረረው አገር ነው፡፡
ጦርነቱ የአማራ ክልልና የህወኃት ብቻ የሚመስል ቅርፅ እንዴት ሊይዝ ቻለ? የሚል ግራ መጋባትና ቁጣ በማህበረሰቡ ዘንድ ተንፀባርቋል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው?
እውነት ነው፤ እኛ የገፈቱ ዋና ቀማሽ በቅርብ ድንበር ላይ ያለን ተበዳዮች ነን፡፡ ህመሙ ትኩሳቱ በቅርብ የሚሰማን እኛ ነን፡፡ በሩቁ ያለው አካባቢ ህመሙን ቢያውቀውም እንኳን እንደኛ ህመሙን በቅርበት ስለማያየው የእኛን ያህል አይታመምም፤ ማየትና መስማት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። በቅርበት ስታይውና ሲነካሽ ነው ህመሙ የሚሰማሽ፡፡ ስለዚህ የደረሰብንን ህመም መናገር አለብን፡፡ እንዲህ እየሆነብን ነው፤ በደል እየተፈጸመብን ነው፤ ህዝቡን አስቀድመውና በተሳሳተ መንገድ አሰልፈው እየወጉን ነው በርከት ያለ የታጠቀ ህዝብ ነው ሊወጋን እየመጣ ያለው፤ እየወጋንም ነው፡፡ ይሄንን ለፌደራል መንግስት መናገራችንና ማሳወቃችን ልክ ነው፡፡ ፌደራል መንግስት ሰምቶታል፤ ከዚህም  በኋላ  ፌደራል መንግስት ሀላፊነቱን ይወስዳል፡፡ እኛም የፌደራል መንግስቱ አንድ አካል ስለሆንን  ከፌደራል መንግስትና መከላከያ ጋር ሆነን የተደቀነብንን የህልውና አደጋ ለመመከትና ወደ ሰላማዊ መንገድ ለመመለስ እርምጃ ውስጥ ገብተናል፤ የሆነው ይሄ ነው፡፡
ህወኃት እንደ አሜሪካና አውሮፓ ያሉ ትልልቅ ሀገራትን ማሳመን የቻለ የዲፕሎማሲ ስራ የመስራት አቅም ሲያጎለብት፣ በመንግስት በኩል ያለውን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳመን ያልተቻለበት ምክንያት ምንድን ነው ይላሉ?
በእኛ በኩል የብሔር ብሔረሰቦች  ማህበራዊ አንቂዎች ሊሆኑ ይችላሉ፣ የመንግስትም ሆነ የግል ሚዲያዎች ሊሆኑ ይችላሉ፤ በተገቢው መንገድ ያለውን እውነት በማስረዳትና በመናገር ደረጃ ከፍተቶች አሉ። በቂ የዲፕሎማሲ ስራ ተሰርቷል ተብሎ አይታመንም፡፡ ይህን ማጠናከር እንዳለብን ገምግመን ወደ ስራ ተገብቷል፡፡ ሁለተኛው ግን ምዕራብያውያን ሀገሮች በተለይም አሜሪካን ስንወስድ በግልጽ ጣልቃ ገብታብናለች፡፡ ባደረግነው ግምገማ አሜሪካ  እንዲህ የምታደርገው እውነታው ጠፍቷት ነው የሚል እምነት የለንም፡፡ አሜሪካ የራሷ የሆነ  ፍላጎት  ይኖራታል፡፡ በአሜሪካ ትሬንድ ያየነው ብዙ  የአፍሪካና የዓለም ሀገራትን ጣልቃ ገብታ ስትገነባ ሳይሆን ስታፈርስ ነው፡፡ ለዚህ ሶሪያን፣የመንንና ሶማሊያን መጥቀስ እንችላለን፡፡ ከዚህም ውጪ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የፖለቲካ አቋምም ራሱን የቻለ ጉዳይ ነው፡፡ አሜሪካ ከግብጽ ጎን ለመቆም የምታደርገው ነገር በግልፅ የሚታወቅ ነው፡፡ ስለዚህ የእነሱ ፍላጎት ለማስጠበቅ የሚንቀሳቀሱ መሆኑን እንጂ የምንረዳው በትግራይ አክቲቪስቶች ወሬ ላይ ተመስርታ የእነሱን ፕሮፖጋንዳ ተቀባይነት አለው ብላ አምናበት አይደለም፤ ይሄ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ እኛ የUN አካላትም ሌሎችም መጥተው እንዲያዩና እውነታውን እንዲረዱ እየፈቀድን ነው ያለነው፡፡ ነገር ግን ሚዛናዊ ስለማይሆኑና አድልዎ ስለሚፈፀሙ ትልልቅ ሚዲያዎቻቸውን በመጠቀም ይጮሃሉ፡፡ በዚህም እንድንኮታኮትና እንድንወድቅ ነው የሚፈልጉት፡፡ ህዳሴ ግድቡን እንድንገነባ በኢኮኖሚ እንድንጠነክር አይፈልጉም፡፡ ፍላጎታቸው ይሄ ስለሆነ እንጂ የትግራይን አክቲቪስቶች ወሬ በማመን ብቻና የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ባለማወቅ አይደለምና በአጠቃላይ የአሜሪካ አካሄድ የአዋቂ አጥፊነት ነው ብለን ነው የምናምነው።  በዚያው ልክ እኛን የሚረዱን ትክክለኛውን የኢትዮጵያ  እውነታ የሚያውቁ አሉ፡፡ ለምሳሌ ሩሲያን ብንወስድ፣ ቻይናንም ብናይ በተገቢው መንገድ የኢትዮጵያን እውነታና ቁመና ያወቁና ነፃ አመለካከት ያላቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህን አውነታን በአግባቡ የሚረዱ አገራት መዘንጋትም አያስፈልግም፡፡ ሩሲናያ ቻይና ኢትዮጵያ ያለችበትን ትክክለኛ ሁኔታ ያውቃሉ ይገነዘባሉ፡፡ እነ አሜሪካም ያለ አድልዎ መቆም ቢፈልጉ ይሄ እውነታ ጠፍቷቸው አይደለም፤ በአድልዎ መጓዙን ስለመረጡ እንጂ፡፡ አሁን ሰሞኑን የእርዳታ እህል ሲገባ ያልተገባ ነገር አብሮ እንዳይገባ በሚል የሚወስደውን ጥንቃቄ እንደጥፋት ቆጥረው ፍተሻ አደረጉ ብለው ነው በጣም ሲጮኹ የነበሩት፡፡ በሌላው አገር በእርዳታ ስም የጦር መሳሪያ እያጋዙ አገር እንደበተኑት ሁሉ እኛንም እንዲህ ለማድረግ ቢሞክሩ ይህን አንፈቅድም ስነ- ልቦናችንም ለዚህ የተዘጋጀ አይደለም፤ ቅኝ ያልተገዛን በነፃነትና በጀግንነት የኖርን መሆናችንም መዘንጋት የለበትም፡፡ በውጭ አገር ተስፋ የማንኖርና የራሳችንን ባህል ተስፋና መንገድ  ያለን መሆናችን ታውቆ ጉዳዩ በዚህ መልክ ነው መታየት ያለበት፡፡
የሰሜኑን የሀገራችንን ትኩሳት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማብረድና ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ከፌደራል መንግስት፣ ከትግራይ ህዝብና ከህወኃት በኩል ምን ይጠበቃል? ከዓለም አቀፍ ጫና ለመውጣትስ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
የዓለም አቀፉን ጫና ለመቋቋም ዲፕሎማሲው ላይ የሚሰራው ስራ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል፤ ሌላ አማራጭ የለንም፡፡ አንዳንድ ሀገራት ሆን ብለው ሊሰሙን  ባይፈልጉና ፊታቸውን ቢያዞሩብን እንኳን ሌሎች እውነትን የያዙ የዓለም አገራት በተለይም  የአፍሪካ  አገራት የሆነውን ስለሚያውቁ ለአፍሪካ ህብረትና ሌሎች ድርጅቶችም እውነታውን ማሳወቅ ያስፈልጋል፡፡ ለዚሁ ሥራ የተቋቋሙ ተቋማትም አሉ። እነዚህ ተቋማት ሥራቸውን በደንብ መስራት አለባቸው፡፡ በውጭ የሚኖረው ዳያስፖራ ደግሞ ተገቢውን መረጃ ወስዶ እየተፈጸመብን ያለውን ሤራ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በደንብ ማሳወቅና በአግባቡ ማስረዳት አለበት፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ እኛ ኢትዮጵያውያን አንድ ልንሆን ይገባል፡፡  ለትግራይ ህዝብም
አልምቶና ሰርቶ በሰላም የመኖር  መብቱን እንዲጠቀም ጥሪ እናቀርብለታለን፡፡ ምክንያቱም ህወኃት ከራሱ ውጪ ለማንም የማያስብና አስከፊ የሀገር ችግሮች ሁሉ ከዚህ ቡድን የሚመነጩ መሆናቸውን የትግራይ ህዝብ ያጣዋል ብለን አናስብምና ይህን አሸባሪ ቡድን አሳልፎ መስጠት ነው ያለበት፡፡
በሌላ በኩል፤ አሁን የተደቀነብንን የህልውና አደጋ ለመከላከል በምናደርገው ትግል ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከጎናችን እንዲቆሙ ጥሪ እያቀረብን፣ ለዚህ አፋጣኝ ምላሽ ለሰጡ ሁሉ ምስጋናችን የላቀ ነው፡፡ የጀመርነውን በድል እንቋጨዋለን ኢትዮጵያ ወደ ሰላሟ ትመለሳለች፡፡ በዚህ ፅኑ እምነት አለን በተጨማሪም የትግራይ አክቲቪስቶች ከዚህ በኋላ ከኢትዮጵያ ህዝብ ሀብት ላይ እየተዘረፈ የሚሰጥ ገንዘብ የሌለ መሆኑን አውቀው ወደ ስራ እንዲገቡ በአንጽኦት እናሳስባለን፡፡

Read 2757 times Last modified on Wednesday, 21 July 2021 16:42