Saturday, 17 July 2021 14:40

“ሀዋሳ ታነባለች” የኪነ ጥበብና የመፃፍት አውደ ርዕይ ትላንት ተከፈተ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)


            በሰማይ መልቲ ሚዲያ የተዘጋጃውና እስከ ነገ ምሽት የሚቆየው “ሀዋሳ ታነባለች” የኪነ ጥበብና የመፅሀፍት አውደ ርዕይ ትላንት ሀምሌ 9 ቀን 2013 ዓ.ም በሀዋሳ ሚሊኒየም አዳራሽ መከፈቱን የሰማይ መልቲ ሚዲያ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ኢዮብ ፅጌ አስታወቁ፡፡
የአውደ ርዕዩ ዋና ዓለማ በሀዋሳ የሚገኙ ወጣቶችን  የማንበብና  የመፃፍ ፍላጎት በማነቃቃት የማህበረሰቡን ንቃተ ህሊና ለማሳደግ እንደሆነም አቶ እዮብ ፅጌ የገለፁ ሲሆን በዚህ የሶስት ቀናት  አውደ ርዕይ፣ ልክ አዲስ አበባ እንደሚደረገው  ሁሉ የመፅሀፍትን ዋጋ ከ20-50 በመቶ ቅናሽ በማድረግ ማህበረሰቡ አቅሙን ባገናዘበ መልኩ እንዲገዛና ወላጆችም ሆነ ልጆች ክረምቱን በንባብ እንዲያሳልፍ ለማድረግ ነው ተብሏል፡፡
ከ15 ቀናት በኋላ ት/ቤቶች በሚዘጉበት ጊዜ ት/ቤቶች ለተማሪዎች የሚሸልሟቸውን መፅሀፍት በጥሩ ዋጋ እና በአማራጭ ለማግኘት ጥሩ አጋጣሚም ነው ተብሏል፡፡
በቅዳሜና እሁድ መርሀ ግብር የተለያዩ ኪነ-ጥበባዊ፣ የግጥም፣ የወግና የሙቃ ድግስ የሚከናወን ሲሆን ለዚህም ከአዲስ አበባ ጭምር አቅራቢዎች መጋበዛቸውን የገለፁት አቶ ኢዮብ ፅጌ፣ የንባብ ባህል ለማሳደግና የማህበረሰቡን ንቃተ ህሊና ለመጨመር ምን መደረግ አለበት  በሚለው ዙሪያ የፓናል ውይይት እንደሚካሄድም ጨምረው ገልፀዋል፡፡ በዚህ አውደ ርዕይ ላይ የከተማው ት/ቤቶች ዩኒቨርስቲዎች፣ የመፅሀፍት መደብሮችና ሌሎችም እንደሚሳተፉ ተገልጿል፡፡ ሰማይ መልቲ ሚዲያ ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ አውደ ርዕይ በማዘጋጀት ልምድ ያለው ሲሆን ይህን መርሃ ግብር በዓመት ሁለት ጊዜ በቀጣይነት ለማዘጋጀት መታቀዱንም ጨምረው የገለፁት አቶ እዮብ ደርጅታቸው ሰማይ መልቲ ሚዲያ በስነ-ፅሁፍ በማህበረሰብ ንቃትና በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥን የሬዲዮ ፕሮግራም በደቡብ ሬዲዮ እያዘጋጀ ለአድማጭ እንደሚያቀርብም ገልፀዋል፡፡

Read 3159 times