Saturday, 17 July 2021 14:29

በትግራይ በሲቪል ሰዎች ላይ የሚፈጸም እንግልት እስርና ጥቃት በአፋጣኝ እንዲቆም ተጠየቀ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  በትግራይ ክልል ከቀጠለው ግጭት ጋር ተያይዞ በሲቪል ሰዎች ላይ  እንግልትና እስር፣ የንግድ ቤት መዘጋት፣ ብሎም በሲቪል ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መከሰቱንና ሕይወት መጥፋቱን፣ እንዲሁም በታሳሪዎችና በምርኮኞች ላይ የሚደርስ ኢ-ሰብአዊ አያያዝ፣ በስደተኞች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችና ሕጻናትን   ለውትድርና መጠቀም የሚያመላክቱ መረጃዎች እጅግ የሚያሳስበው መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ።
ሐምሌ 4 ቀን 2013 ዓ.ም. በደቡብ ጎንደር ዞን፣ ፎገራ ወረዳ፣ ወረታ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነዋሪ በሆኑ ሦስት የትግራይ ተወላጆች ላይ በድንገት በተሰባሰቡ ነዋሪዎች በደረሰባቸው ድብደባ መገደላቸውን  ለኮሚሽኑ የደረሱት ጥቆማዎች ያመለክታሉ።
ይህ  ጥቃት የደረሰው ከእለቱ አንድ ቀን አስቀድሞ ፍየል ውሃ በሚባል ቦታ የሕወሃት/ትግራይ መከላከያ ኃይሎች በወሰዱት የጥቃት እርምጃ የፎገራ ወረዳ ነዋሪዎች የሆኑ የሚሊሽያ ቡድን አባላትና የወረዳው የሰላምና ፀጥታ ኃላፊ መገደላቸው  ከተነገረ በኋላ ነው። ሐምሌ 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ረፋዱን ጉመራ ወንዝ ተብሎ ከሚጠራና  ከተገደሉት የወረዳው የሰላምና ፀጥታ ኃላፊ ትውልድ ቦታ የኃላፊውን እሬሳ ለመቀበል  የመጡ ነዋሪዎች  ጥቃቱን እንዳደረሱ ይነገራል።
የፎገራ ወረዳና የአካባቢው የፀጥታና የአስተዳደር ኃላፊዎች በወሰዱት አፋጣኝ እርምጃ ሁኔታው የተረጋጋና ተጨማሪ ጥቃት ሊፈጽሙ የነበሩ ስድስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉ ቢሆንም፣ የተከሰተው ሁኔታ ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች እንዳይዛመት የሚያሰጋ ነው ብሏል ኢሰመኮ።  በትግራይ ክልል በሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ላይና የሕወሃት/ትግራይ መከላከያ ኃይሎች ተቃዋሚ ናቸው በሚል በሲቪል ሰዎች ላይ እንደተወሰዱ የሚነገሩ የግድያና የአፈና እርምጃዎች የሚያሳስቡ መሆናቸውን ኮሚሽኑ በመግለጫው አስታውቋል። በተጨማሪም፤ በአላማጣና አካባቢው በድጋሚ ያገረሸውን ግጭትና በመኾኒ እየተወሰዱ ስለመሆናቸውን የሚነገሩ የበቀል ጥቃቶች ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰዎች መፈናቀል እያደረሰ ነው ብሏል።
ቴሌኮሙኒኬሽንና ማኅበራዊ አገልግሎቶች መቋረጣቸው የሰብአዊ መብቶች ክትትል ስራውን አዳጋች ያደረገው ቢሆንም፣ ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል ያለውን የተደራሽነት ሁኔታ በተመለከተ የሚያደርገውን ክትትል የሚቀጥልና በቆቦ፣ በወልዲያና በማርሳ ተጠልለው የሚገኙ ከአላማጣና አካባቢው የተፈናቀሉ ሰዎችን የሚጎበኝ መሆኑን አስታውቋል፡፡   
ኢሰመኮ የግጭቱ መባባስና የግጭቱ ተጽእኖ በአፋርና በአማራ ክልል የሚገኙ ቦታዎችን ጨምሮ ወደ ትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ጭምር መስፋፋቱ እጅግ እንደሚያሳስበው ነው የጠቆመው።
እንዲሁም ኮሚሽኑ አዲስ አበባን ጨምሮ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የሚደርሱትንና በትግራይ ተወላጆች ላይ የሚደርሱ ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ እስር፣ የንግድ ቤት መዘጋትና የእንግልት መረጃዎችንም እየተከታተለ ይገኛል።  የሚድያ ሰራተኞችን ጨምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎች ከአዲስ አበባ ውጪ ወደ ሌሎች  ቦታዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን ለኮሚሽኑ ጥቆማዎች ደርሰውታል።
ከሰኔ 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ  ተባብሶ የታየው  ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ ክስተትና እስር ሁኔታ ተገቢውን ትኩረትና መፍትሔ ከአለማግኘቱ በተጨማሪ፤ በስፋት የሚደመጡ የጥላቻና ግጭት ቀስቃሽ ንግግሮች ሁኔታው ሊያባብሱና  ብሎም በማኅበረሰቦች መካከል ያለውን ትስስር ሊያላሉ የሚችሉ ናቸው። ስለሆነም፣ በየትኛውም አካባቢ ከሕግ አግባብ ውጪ የታሰሩ ነዋሪዎች በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁና የፌዴራል መንግስትም ሆነ የክልል መስተዳድሮች በነዚህ ነዋሪዎች ላይ እንግልት ያደረሱና ሌሎች ሕገወጥ ድርጊቶች የፈጸሙ የሕግ አስከባሪ አካላትን ሕግ ፊት ሊያቀርቡ ይገባል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ “በተለይም ይህን በመሰለ ፈታኝና የውጥረት ወቅት መንግስት ለሲቪል ሰዎችና ተጋላጭ ለሆነው ማኅበረሰብ ክፍል ከፍተኛ ጥበቃ የማድረግ ተጨማሪ ኃላፊነት የሚጣልበት ጊዜ ነው። መሰረታዊ የሆኑ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችና የሰብአዊ መብቶች መርሆች በግጭት ወቅት ጭምር ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ የሚያዙና ሲቪል ሰዎችና የሲቪል መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ሁሉም የግጭቱ ተሳታፊ ወገኖች ላይ ከፍ ያለ ግዴታ የሚጥሉ ናቸው።  ስለሆነም ኮሚሽናችን በእስር ላይ ያሉ  ሰዎችን ጨምሮ አጠቃላይ ሁኔታውን በተመለከተ የሚያደርገውን የክትትል ስራ የሚቀጥል ሲሆን፣ በግጭቱ ለሚሳተፉ ወገኖች በሙሉ እንዲሁም የሚድያ ተቋማትን ጨምሮ ለሀገራዊና ለዓለም አቀፍ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በሙሉ ማንኛውንም የማኅበረሰብ ክፍል አደጋ ላይ ከሚጥል ንግግር፣ መግለጫዎችና ተግባራት እንዲቆጠቡ ኢሰመኮ ጥሪ ያቀርባል” ብለዋል። 
በሌላ በኩል ኢሰመኮ፤  ሰኔ 23፣ 24 እና 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በፌደራል የፀጥታ ኃይሎች ተይዘው በእስር ላይ የሚገኙትን በቃሉ አላምረው፣ ያየሰው ሽመልስ፣ ፋኑኤል ክንፉ፣ አበበ ባዩ፣ መልካም ፍሬ ይማም፣ ፍቅርተ የኑስ፣ ዊንታና በርሄ እና ምህረት ገብረክርስቶስን ጨምሮ 21 የኢትዮ-ፎረም እና የአውሎ ሚዲያ ጋዜጠኞችና ሰራተኞች አያያዝን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር በቅርበት ሲከታተል መቆየቱን ጠቁሟል፡፡
ከእነዚህ ታሳሪዎች መካከል ሦስቱንና አንድ ሌላ ታሳሪን ጨምሮ አራት እስረኞች ማክሰኞ ሰኔ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ መለቀቃቸውንና ቀሪዎቹ ታሳሪዎች በወንጀል ስለተጠረጠሩ ለምርመራ ስራ በእስር እንዲቆዩ በፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮ ትዕዛዝ መሰጠቱን ፖሊስ ለኮሚሽኑ  የገለጸ ቢሆንም፣ እስከ ሐምሌ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ምሽት ድረስ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ አለማየቱና ታሳሪዎቹን ለመጎብኘት አለመቻሉ፤ እንዲሁም ታሳሪዎቹ ከቤተሰቦቻቸውም ሆነ ከጠበቆቻቸው ሳይገናኙ ከአንድ ሳምንት በላይ መቆየታቸው ኢሰመኮን  እጅግ የሚያሳስበው ነው ብሏል።
ማንኛውም በወንጀል የተጠረጠረ ሰው በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ ያለበት መሆኑና በእስር ያሉ ተጠርጣሪዎች በጠበቆቻቸውና በቤተሰቦቻቸው የመጎብኘት መብት ፈጽሞ ሊከለከሉ የማይገቡና ተጠርጣሪዎች በሕይወት መኖራቸውንና አካላዊ ደኅንነታቸው መጠበቁን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው መሰረታዊ የሕግ ጥበቃዎች መሆናቸውን በመግለጫው አስታውሷል፤ኢሰመኮ፡፡
ስለሆነም የፌዴራል ፖሊስና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አስፈጻሚ አካላት አሁንም በእስር ያሉ የአውሎ ሚድያና የኢትዮ ፎረም ጋዜጠኞችና ሰራተኞች በሙሉ በአፋጣኝ ከቤተሰቦቻቸውና ከጠበቆቻቸው እንዲገናኙ እንዲያደርጉ፣ የታሳሪዎቹን የእስር ሁኔታ ሕጋዊነት እንዲያስረዱና፣ ከፍርድ ቤት የተሰጠ የእስር ትዕዛዝ ካልቀረበ በስተቀር ታሳሪዎቹ በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁ ኮሚሽኑ  አሳስቧል፡፡
 ሕግን ያልተከተለ ማንኛውም አይነት እስር በሕግና ፍትሕ ሥርዓት ላይ የሚኖርን እምነት የሚሸረሽር በመሆኑ፣ ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ እስር ሙሉ በሙሉ መቆም ያለበት ተግባር ነው ያሉት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ “ኮሚሽኑ ታሳሪዎቹን ለመጎብኘትና የአያያዛቸውን ሁኔታ ለማወቅ የሚያደርገውን ጥረት ይቀጥላል” ብለዋል።


Read 14851 times