Saturday, 17 July 2021 14:24

አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ገድሏል የተባለው ተከሣሽ በሞት እንዲቀጣ ተጠየቀ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(0 votes)

  አርቲስት አጫሉ ሁንዴሣን በመግደል ወንጀል ተከሶ ጥፋተኛ የተባለው ጥላሁን ያሚ በሞት እንዲቀጣ ዐቃቤ ሕግ ጠየቀ።
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምደብ ችሎት ከትናንት በስቲያ በዋለው ችሎት፤ በአርቲስቱ ግድያ ጥፋተኛ በተባለው  ተከሳሽ ላይ የዐቃቤ ሕግን የቅጣት አስተያየት  ሰምቷል።
በዕለቱም በአርቲስቱ ግድያ ወንጀል  ተከሰው  ጥፋተኛ የተባሉት 3ቱም ተከሣሾች  ማለትም፤ ጥላሁን ያሚ፣ ከበደ ገመቹና አብዲ አለማየሁ ችሎት ፊት ቀርበዋል።
ዐቃቤ ሕግ ጥፋተኛ በተባሉት ተከሳሾች ላይ የቅጣት አስተያየቱን በጽሑፍ ለፍርድ ቤቱ ያቀረበ ሲሆን፤ የተከሳሾች ተከላከካይ ጠበቃ ደግሞ ቅጣቱ እንዲቀልላቸው ጠይቋል።
የተከሣሾቹ ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት የቅጣት ማቅለያ፤ ጥፋተኛ የተባለ ተከሳሽ ከዚህ ቀደም መልካም ስነ ምግባር ያለው ከነበረና ወንጀሉንም ሆነ ብሎ አለመፈጸሙ ከተረጋገጠ ቅጣቱ ይቀልለታል ይላል።
ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ፤ የቅጣት ማቅለያ አስተያየት ለሶስተኛ ተከሳሽ አብዲ አለማየሁ ካልሆነ በስተቀር ለ1ኛ ተከሳሽ ጥላሁን ያሚ እና ለ2ኛ ተከሳሽ ከበደ ገመቹ የቅጣት ማቅለል ሃሳብ ላይ አልስማምም ብሏል።
ዐቃቤ ሕግ፤ 1ኛ ተከሳሽ ጥላሁን ያሚ፤ “ከዚህ ቀደም ጥሩ ስነ ምግባር ያለው አይደለም” ያለ ሲሆን በ2012 ዓ.ም. ላይ በሁለት መዝገቦች ክስ ተመስርቶበት እንደነበረ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል።
1ኛ ተከሳሽ ከዚህ ቀደም በስርቆትና በባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ ዘረፋ ክስ ተመስርቶበት እንደነበረ ለፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ሕግ አስረድቷል። ከዚህ በተጨማሪም 1ኛ ተከሳሽ ጥላሁን ያሚ “ሕግን በተጻረረ መልኩ መዝናኛ ቦታ ላይ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ይዞ ይገባ ነበር” ብሏል- ዐቃቤ ሕግ።
አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ለመግደል አስቦ ወንጀሉን በመፈጸሙ 1ኛ ተከሳሽ ላይ የቅጣት ማቅለያ ሊደረግለት አይገባም በማለት ጥላሁን ያሚ በሞት እንዲቀጣም ዐቃቤ ሕግ ጠይቋል።
የተከሳሾች ተከላካይ ጠበቃ በበኩሉ፤ ዐቃቤ ሕግ የጠቀሳቸው 1ኛ ተከሳሽ ከዚህ ቀደም የተመሰረቱበት ሁለት ክሶች ውሳኔ ስላልተሰጠባቸው፣ ጥፋተኛ መሆኑ እስኪረጋገጥ ድረስ ነጻ ሆኖ የመታየት መብትን የሚጋፋ ነው ሲል ተከራክሯል።
2ኛ ተከሳሽ ከበደ ገመቹን በተመለከተ፤ በሕገ ወጥ መንገድ የጦር መሳሪያ መግዛቱን፤ የገዛውን ጦር መሳሪያም ለጥላሁን ያሚ አውሶት ጦር መሳሪያው አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ለመግደል ጥቅም ላይ መዋሉን ዐቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
2ኛ ተከሳሽ ከጸጥታ ኃይሎች ለመደበቅ ሙከራ ሲያደርግ ቆይቶ አደዓ ድሬ በተባለ ቦታ ላይ በቁጥጥር ሥር መዋሉን በመጥቀስ፣ ዐቃቤ ሕግ የቅጣት ማቅለያውን በመቃወም ሞግቷል።
በዚህም ምክንያት 2ኛ ተከሳሽ ከበደ ገመቹ ጥፋተኛ በተባለበት ወንጀል አንቀጽ ቅጣቱን እንዲቀበል ዐቃቤ ሕግ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
የተከሳሾች ተከላካይ ጠበቃ፤ 2ኛ ተከሳሽ ከበደ ገመቹ የቀረበበት ሪከርድ ሳይኖር ‘የቀድሞ ባህሪው መልካም አልነበረም’ ማለት ስለማይቻል፣ የቅጣት ማቅለያ ሃሳቡ ተቀባይነት እንዲያገኝ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግና የተከሳሽ ጠበቆች የቅጣት አስተያየትን  ከሰማ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ  የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ለሐምሌ 20 ቀን 2013 ቀጠሮ ሰጥቷል።

Read 957 times