Sunday, 11 July 2021 18:50

የሴኩቱሬ መብረቃዊ ምት ህጋዊነትን (Legitmiacy) በተመለከተ!

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  (ጦርነትን ቀድሞ የጀመረ ቅድመ ሁኔታን የማስቀመጥ ሞራል የለውም!)


             ጦርነቱ በተጀመረ በሁለተኛው ቀን ሴኩቱሬ በድምፀ ወያኔ ቀርቦ ጦርነቱን ሕወሓት እንደጀመረችው በግልፅ ቋንቋና ሰፋ ባለ ማብራሪያ ገለፀ፣ ሴኩቱሬ ይህን ገለፃውን በሚሰጥበት ወቅት በቴሌቪዥኑ እስክሪን ላይ የተጻፈው ርዕሰ ጉዳይ “የመጀመሪያው ምዕራፍ በድል የመጠናቀቅ አንድምታ” የሚል ነበር። ርዕሱ ሴኩቱሬ ይህን በሌላ በየትኛውም አግባብ መለቀቅ የሌለበትን ማስረጃ ለኢትዮጵያና ለዓለም ይፋ ያደረገበትን ምክንያት ግልፅ ያደርጋል፣ በአጭር ቃል ሴኩቱሬ በሰሜን ዕዝ ላይ ስኬታማ መብረቃዊ ጥቃትን መፈፀሙን እንደ መጨረሻው የድል ምዕራፍ ሳይቆጥረው አልቀረም። ሌላ ረዘም ያለ ጦርነት በቀጣይነት እንዳለ ቢያውቅ ኖሮ ይህን መግለጫ ባልሰጠም ብዬ አስባለሁ።
ሴኩቱሬ በ45 ደቂቃ ውስጥ በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃቱ በቅድሚያ መፈፀሙን ይፋ ከማድረጉም ባለፈ ለድርጊቱ ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠትም የአቅሙን ያህል ሞክሯል። እሱ ያለው "...ከሰሜን በኩል አሃዳዊውና ወራሪው የአብይ መንግስት ደግሞ በደቡብ በትግራይ ሕዝብ ላይ ግልፅና የማይቀር (imminent) ጥቃት ሊፈፅሙ እንደሆነ እንደገመገምን ቀድመን በመብረቃዊ ምት ሰሜን ዕዝን “demobilize” አድርገናል...ነው።" በመቀጠልም ሴኩቱሬ እንደዚህ ዓይነት እርምጃ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያለው ፅንሰ ሐሳብ መሆኑን ከገለፀልን በኋላ ስያሜውም በእንግሊዝኛ “Anticipatory Self defence” ተብሎ ይጠራል በማለት አብራርቶልናል። ታዲያ ይህ ዘዴ ትንንሽ ሀገራት በትላልቅ ሀገራት ሊዋጡ እንደሆነ ማስረጃዎች ሲገኙ ጥቅም ላይ የሚውል ራስን የመከላከል እርምጃ ነውም በማለት ነግሮናል።
ሴኩቱሬ ለቅድመ-ጥቃቱ ዓለም አቀፋዊ ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት የጠቀሰው “Anticipatory Self Defence” ምንን ያመላክት ይሆን? ራስን ከታለመ ወይም ከታቀደ ጥቃት ቀድሞ መከላከልን በተመለከተ የሚያጠኑ ምሁራን ሦስት የመከላከል ዓይነቶች እንዳሉ ያመለክታሉ።
1. ለማይቀረው ጥቃት የሚወሰድ የመከላከል እርምጃ (Anticipatory Self Defence)፦ ይህ አንድ ሀገር በሉዓላዊነቱ ላይ እጅግ በጣም ግልፅና በማስረጃ የተደገፈ ጥቃት ከሌላ ሀገር ወይም ታጣቂ ቡድን እንደሚሰነዘርበት እርግጠኛ ሲሆን ቀድሞ የሚወስደው የመከላከል እርምጃ ነው። ይህ ጥቃቱን እንደሚያደርስ ወደሚገመትበት ሀገር ድንበር ገብቶ እስከ ማጥቃት የሚዘልቅ የመከላከል እርምጃ ነው። ስለ ሕጋዊነቱ(Legitimacy) እመለስበታለሁ።
2. ከተገማች ጥቃት ለመከላከል የሚወሰድ እርምጃ (Pre-emptive Self Defence)
ይኼኛው የመከላከል እርምጃ ቀደም ሲል ከጠቀስኩት የሚለየው ጥቃቱ ከሚፈፅመበት የጊዜ ሰሌዳ አኳያ ነው። “Anticipatory Self Defence” ጠላት በጣም ቅርብ በሆነ ጊዜ ጥቃቱን እንደሚፈፅም በተረጋገጠ ጊዜ የሚወሰድ እርምጃ ነው። Pre-emptive Self defence ግን የተገመተው ጥቃት የሚፈፀምበት የጊዜ ሰሌዳ ከ”Anticipatory” ራቅ ሊል ይችላል።
3. Preventive Self Defence
ይኼኛው የመከላከል ዘዴ የታለመው ጥቃት የሚፈፀምበትን ወቅት በእርግጠኝነት ማወቅን እንደ ቅድመ ሁኔታ አያስቀምጥም። ጠላት ወደ ፊት በአሳቻ ጊዜ ጥቃት እንደሚፈፅም ሲታመን “Preventive Self defence” ተግባራዊ ይሆናል።
“Anticipatory Self Defence “ከዓለም አቀፍ ሕግና ከተባበሩት የዓለም መንግስታት ቻርተር አንፃር፦
ከ”Anticipatory” የመከላከል እርምጃ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ የዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ሕጎች፣ የተባበሩት መንግስታት ቻርተር አንቀፅ 51 እና እ.ኤ.አ በ2004 በተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ አማካይነት የተደረገው ውይይት ይጠቀሳሉ። ከነዚህ ውስጥ እ.ኤ.አ. በ1951 በተባበሩት መንግስታት ቻርተር ላይ የሰፈረውን እንደሚከተለው ላስቀምጥ፦
Article 51 of the UN Charter “Nothing in the present Charter shall impair the inherent right of individual or collective self-defense if an armed attack occurs against a Member of the United Nations until the Security Council has taken measures necessary to maintain international peace and security”
ከላይ እንደምትመለከቱት በዚህ አንቀፅ ውስጥ “Anticipatory Self Defence” የሚል ሐረግ የለም። ይህን የሚጨማምሩት ተርጓሚዎቹ ናቸው፣ እንደዚያም ሆኖ ሐረጉ በግልፅ ባለመቀመጡ እስከ ዛሬም አንቀፁ በአጨቃጫቂነቱ ቀጥሏል። በግልፅ እንደምንመለከተው አንቀፅ 51 የሚለው “If an armed attack occurs..” ነው።
ከተባበሩት መንግስታት ይልቅ ለ"Anticipatory Self Defence” የሚቀርበው እ.ኤ አ.አ በ2004 በተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ በተዘጋጀው ውይይት ላይ የተቀመጠው ማጠቃለያ ነው።
“In 2004, the Secretary-General’s High-Level Panel on Threats, Challenges and Change stated “A threatened State, according to long established international law, can take military action as long as the threatened attack is imminent, no.other means would defelect it and the action is proportionate.”
ይህ ውሳኔ ግን እስከዛሬ ድረስ በተባበሩት መንግስታት ቻርተር ስለ አለመግባቱ ልብ ይሏል። እስከ አሁን ይህን የመከላከል መብት በተመለከተ የሚደረጉ ክርክሮች እንደቀጠሉ ነው። ነገር ግን ከ9-11 ጥቃት ወዲህ ይህ የመከላከል እርምጃ በተለይም አሸባሪዎች ጥቃት እንደሚያደርሱ በማስረጃ ከተረጋገጠ ወዲያው ተግባራዊ መሆን እንዳለበት ብዙዎች የሚስማሙበት ነው።
በታሪክ “Anticipatory self Defence”ን ተግባራዊ ያደረጉ ብዙ ሀገራት አሉ፣ ለምሣሌ እንግሊዞች ካናዳን ቅኝ በሚገዙበት እ.ኤ.አ. በ1837 ዓ.ም የካናዳን አማፂያን የተሳፈሩበትን የካሮላይንን መርከብ ለመምታት በኒጋራ ፏፏቴዎች አቅጣጫ ወደ አሜሪካ ድንበር ዘልቀው ገብተው ጥቃት አድርሰዋል። ይህ እርምጃ “Caroline Incidence” ተብሎ ይታወቃል። እስራኤል እ.ኤ.አ. በ1967 ግብፅን አስቀድማ የመታችው በ”Anticipatory Self defence” መርህ ነበር። አሜሪካ ኢራቅን፣ አፍጋኒስታንና ሱዳንን በየወቅቱ ያጠቃችው በ”Anticipatory Self Defence” መርህ ነው። በተለይም በሱዳን ላይ ጥቃትን በሰነዘረች ጊዜ ያወደመችው እንደገመተችው የአሸባሪዎችን ካምፕ ሳይሆን የመድኃኒት ፋብሪካን ነበር፣ ይህም ከፍተኛ ውግዘትን አስከትሎባታል።
ይህን ሁሉ ርቀት የመጣሁት የሴኩቱሬን ቅጥ አምባሩ የጠፋውን ማብራሪያውን legitimize ለማድረግ እንዳልሆነ ብዙዎቻችሁ የምትረዱኝ ይመስለኛል። ሴኩቱሬ ግን አንድ ውለታ ውሎልን አልፏል፦ በቃ “Anticipatory Self-Defence” የሚለውን ፅንሰ ሐሳብ በተነፈሰበት ቅፅበት፣ ጦርነቱ በሕወሓት እንደተጀመረ በቪዲዮ የተደገፈ ግልፅ ማስረጃ ሰጥቶናል፣ ምክንያቱም ይህ እርምጃ ሁሌም የሚወሰደው በጠላትነት ከተፈረጀው ቡድን ጥቃት አስቀድሞ ነው። ታዲያ ታምራት ላይኔ በወቅቱ “ጦርነቱን ማን እንደጀመረው ወደፊት በገለልተኛ አካላት ይረጋገጣል” ብሎ ሲናገር ሰምቼው፣ የምር ይህ ሰው የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ነበር? በማለት ራሴን እስከ መጠየቅ ደርሼአለሁ። ምክንያቱም ታምራት ጦርነትን ከማንም በላይ በተግባር ጭምር የሚያውቅ ሰው ነው፣ ነገር ግን ሴኩቱሬ በግልፅ በ”Anticipatory Self-Defence” ጦርነቱን የጀመርነው እኛ ነን እያለ ሲናገር፣ ታምራት ወደፊት ማን እንደጀመረው ይጣራል እያለ ከሴኩቱሬ ይልቅ ስለ ሁኔታው እንደሚያውቅ ሰው ሊተነትንልን ይሞክራል፣ አያድርስ ነው!
ሌሎች የሕወሓት አክቲቪስቶችና ጋዜጠኞች ደግሞ የሴኩቱሬን ማብራሪያ አንዴ “Pre-emptive” ሌላ ጊዜ ደግሞ ሁለት የጦር አይሮፕላን ቀደም ሲል በትግራይ ክልል ሲበር ነበር እያሉ ያለ የሌለ ማብራሪያ በመስጠት የሴኩቱሬን እውነተኛ ማስረጃ ለመሸፋፈን ደፋ ቀና ሲሉ ተስተውለዋል። Anticipatory ሌላ፣ pre-emptive ሌላ!
ሆኖም ግን ሴኩቱሬ ማስረጃውን ይስጠን እንጂ ማብራሪያዎቹ በሕፀፆች የታጨቁ ነበሩ።
1. “Anticipatory Self Defence” ቢፈቀድ እንኳን ትግበራው የሚመለከተው በተባበሩት መንግስታት ውስጥ በሀገርነት የተመዘገቡ ሀገራትን ብቻ ነው። የተባበሩት መንግስታት ቻርተር የሀገራት እንጂ የክልል መንግስታት ቻርተር አይደለም። ስለዚህ ዓለም አቀፍ ሕጎች የሚፈቅዱት ፅንሰ ሐሳብ ነው የሚለው ማብራሪያው ሙሉ በሙሉ ስህተት ነው። እሱን አይመለከተውም።
2. ሴኩቱሬ “Anticipatory Self Defence” የሚተገበረው... ትንንሽ ሀገራት (ትግራይን እዚህ ውስጥ ከትቷት ይሆን?) በትላልቅ ሀገራት ሊዋጡ እንደሆነ ማስረጃው ሲኖር... እያለ ያብራራውም ስህተት ነው። ይህ ራስን ከጥቃት አስቀድሞ የመከላከል ሕግ የሚሰራው ለሁሉም የተባበሩት መንግስታት አባል ሀገራት ነው። ትንሽ ትልቅ የሚል ተረት ተረት የለውም።
3. “Anticipatory Self Defence” መከወን ያለበት ከአቅም ግምገማ በኋላ ነው። ዘመን ያለፈበትን ክላሽ ይዘህ ድሮን የታጠቀውን ጦር በ”Anticipatory Self Defence” ቀድሜ እመታዋለሁ ብሎ መነሳት የኢንተለጀንስ ሥራ ድክመትን፣ የጦርነት መረጃ እጥረትን ያመለክታል። ሌሎቹ ሀገራት “Anticipatory Self Defence”ን የሚተገብሩት የጠላትን ጦር አቅም በሚገባ ከፈተሹ በኋላ ነው። የሚጠቃው ጠላት አቅሙ የደረጀ ከሆነ ምናልባትም በሰላም ምድር ጦርነትን እንደ መጥራት ይቆጠራል። በሰሜኑ ጦርነት በተግባርም ያየነው ይህንኑ ነው።
4. በመጨረሻም “Anticipatory Self Defence”ን መተግበር ከተጠያቂነት አያስመልጥም፣ ምክንያቱም አንድ ሀገር ይህን እርምጃ ከመውሰዱ አስቀድሞ መፈተሽ ያለባቸው በጥቂቱ ወደ አራት መስፈርቶች አሉ። በነገራችን ላይ ከላይ የጠቀስኳቸው ሀገራት ማለትም እስራኤልና አሜሪካ ጥቃቱን በተመለከተ ለተባበሩት መንግስታት ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠርተው ነበር።
ሳጠቃልል፦ ትናንት ሕወሓት የደረደራቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ተመለከትኩና ሴኩቱሬና መግለጫው ትዝ አሉኝ። የኢትዮጵያ መንግስት ይህን የሴኩቱሬን የማስረጃ አበርክቶት ለሙግቶቹ የተጠቀመበትን አግባብም ለማወቅ ፈለግሁኝ። በነገራችን ላይ እነ አሜሪካ ሕወሓት ጦርነቱን አስቀድማ እንደጀመረችው ያውቃሉ፣ በግልፅ ሲናገሩም ነበር፣ የኢትዮጵያ መንግስት ዲፕሎማቶች ግን በዚህ ረገድ ገፍተው የሄዱ አይመስለኝም። በእርግጥ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር በሶሻል ሚዲያ ለመግለጫው የእንግሊዝኛ ካፕሽን ጨምሮበት ለቅቋል። ከዚህ ባለፈ የዚህ ቪዲዮ ቅጂ ተተርጉሞ ለተባበሩት መንግስታት ተሰጥቶት እንደሆነ መረጃው የለኝም። ምክንያቱም በየትኛውም ሕግ ጦርነቱን አስቀድሞ የለኮሰው አካል ለደረሱት ድህረ ጦርነት ቀውሶች ቅድሚያ ተጠያቂ እንጂ ቅድመ ሁኔታ ደርዳሪ የመሆን ሞራል የለውም። እውነትን መያዝ ብቻውን በቂ አይደለም፣ እውነት በተግባቦት ጥበብ ተከሽና ካልቀረበች ባክና ትቀራለች። ካለመናገር ብዙ ነገር ይቀራል፣ ትኩረት ለዲፕሎማሲያችን!

Read 2810 times