Sunday, 11 July 2021 18:49

"ደብረፂዮን ተሰቅሎልሃል እንዴ?"

Written by  ዘውድአለም ታደሠ
Rate this item
(0 votes)

  (አማን መዝሙር)
ጋሼ ... አንዳንዴ ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል። ህውሃት የትግራይ ህዝብ ጠላት ባይሆንም፣ ለትግራይ ህዝብ ግን ጠላት ሲገዛለት ነው የኖረው። ግራ ዘመሞቹ ህውሃቶች ትግራይ ከሰላሳ አመት በፊት ያልነበራት የችግር አረንቋ ውስጥ ጨምረዋታል። ከሰላሳ አመት በፊት ከተራ አተካሮ ባለፈ ኤርትራ የትግራይ ጠላት አልነበረችም። ከሰላሳ አመት በፊት ትግራይ ከአማራ ጋር ምንም አይነት የመሬት ግጭትም ሆነ ይሄ ነው የሚባል ጠብ አልነበራትም። ከሰላሳ አመት በፊት ትግራይ ከሱማሌ ከአፋር፣ ከደቡብ፣ ከኦሮሞ፣ ከአማራ ጦር ጋር ጋር እንዲህ በግልፅ ጠብ ውስጥ አልገባችም። ከሰላሳ አመት በፊት ትግራይ ከፌደራል የሚሄድላት በጀት አልተቋረጠባትም። መብራት፣ ስልክና ነዳጅ አልተቋረጠባትም። ከሰላሳ አመት በፊት የትግራይ ሰው በአማራም ሆነ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ሄዶ ሲኖር ምንም የባይተዋርነት ስሜት አይሰማውም። በጥርጣሬም አይታይም ነበር።
አሁን
ትግራይ ወድማለች። ብዙዎች ተሰደዋል። ብዙዎች ተደፍረዋል። ብዙዎች በረሃብ አልቀዋል። ከፊት ብዙ ርሃብ አለ። ህዝቡ በዚህ ስቃይ ውስጥ ሆኖም ህውሀት ህዝቡን ለማይረባ pride እና ego ሲባል ለከባድ ጦርነት እያዘጋጀችው ነው።
ጥያቄ
ህዝቡ የፈለገውን የመደገፍ መብት አለው። ግን መች ይሆን ያልነበረውን ጠላት ያፈሩለት፣ እነሱ በዘረፉት ንፁሁን ሰው ባልበላው ያስወቀሱትን። 17 አመት በጦርነት አቆይተውት፣ አሁንም ለማያባራ ጦርነት ያዘጋጁትን ያረጁ ያፈጁ ሽማግሌዎች ቆም ብሎ የሚጠይቀው? ህውሀት ሃይማኖት ነች እንዴ። ደብረፂዮን ተሰቅሎልናል እንዴ? ጌታቸው አሰፋን ያመነ መንግስተ ሰማይ ይገባል እንዴ? አብዮታዊ ዲሞክራሲ ከሰማየ ሰማይ የወረደ እንከን አልባ ወንጌል ነው እንዴ? የህውሀት ማእከላዊ ኮሚቴዎች ለነፍሳቸው ያደሩ ደቀመዛሙርት ናቸው እንዴ?
ይሄ መልስ የሌለው ጥያቄ ስለሆነ ይብራብኝና አንድ ነገር ተናግሬ ላምልጥ ...
አለም ላይ የሌለ፣ ምርጫ ቦርድ የሌለበት፣ የክልል ምርጫ አካሂዳለሁ ያለችው ህውሃት። በየቀኑ የኮማንዶ ትርኢት እያሳዩ ክልሏን ሰሜን ኮሪያ ያስመሰሏት እነሱው፣ ምርጫ ካደረጉ በኋላ ከዚህ ወዲያ ለፌደራል መንግስቱ አንታዘዝም ብለው መግለጫ ያወጡት እነሱ፣ ከፌደራል መንግስቱ የሚላኩ አመራሮችን በመጡበት አውሮፕላን የመለሱት እነሱ። መጨረሻም መከላከያን ገድለው ህዝባቸውን ለስቃይ የተዉት እነሱ!
ትግራይ ህዝብ ላይ የደረሰው ስቃይ ቢያሳዝነኝም። ለዚህ ሁሉ ግፍ የመጀመሪያው ተጠያቂ ህውሃትና የህውሃት ደጋፊዎች ናቸው! ለትግራይ እናዝናለን ስንል «ምናገባህ?» የሚል የህውሃት አገልጋይ ይመጣል። ሰውዬ ስለ ትግራይ ለማሰብ ለማወቅ ያንተ አፕሩቫል አያስፈልገኝም። ትግሬ ስለሆንክ ከኔ በላይ ለትግራይ ታዝናለህ ማለትም አይደለም።
ብሔር የምርጫ ጉዳይ ነው። ደም አይደለም። ብፈልግ ነገ ተነስቼ ትግሬ መሆን እችላለሁ።

Read 2211 times