Sunday, 11 July 2021 18:48

ከአንድ ወታደር የተላከ

Written by  አሳዬ ደርቤ
Rate this item
(0 votes)


ከርቀት ስትታዘበው -
ተከዜ ወንዝ የሚመስል - በከርሱ ውሃ
የያዘ፤
ተሻግረኽ ስትጠጣው ግን -
ከባሩድ በላይ የሚገድል - በሄምሎክ
የተመረዘ፤
ሸለቆው ማዶ ቁጭ ብለህ -
ባሻገር ያለውን ጋራ - አድማሱን
ስታስተውለው፤
አልፈኸው እስክትሄድ ድረስ -
ሐኖሱ ድባቡ ሁላ - እናት ኢትዮጵያን
መሳይ ነው፤
‹‹ይሄ አገር ማን ነው›› የምትል -
ወንዙን ስትሻገረው፣ መርዙን
ስትጎነጨው፤
ጉድ ነው!
አገሬ ልንገርሽማ፥ ምን ምን እንዳጋጠመኝ-
ስሚማ በመይሳው ሞት
ሕይወቴ ያንቺ ሆኖ ሳለ - ስሜቱን
ከሥሙ ጋር - ለእኔ የሰጠ ድርጅት
ከሴት ደፋሪ መድቦኝ- ሥሜን እንደ ጥጥ
ሲያባዝት
ያንን የሰሜን አርበኛ -
ከአንበጣ ተርታ መድቦ - ጨፍጭፎ ያደረ
ባንዳ፤
ከዝንጀሮ ጋር ሸምቆ-
ሌባ ዘራፊ እያለ- ሲነዛ ፕሮፓጋንዳ፤
ቄስሽ መስቀሉን ጥሎ- ቦንብ ታቅፎ   
ሲንጋጋ
በምሞትለት ስጠቃ- በምዋጋለት ስወጋ፤
ደፍረውኝ እንደ ደፋሪ- ሰልበውኝ እንደ
ሰላቢ
ክደውኝ እንደ ከሃዲ - ወግተውኝ እንደ
ደብዳቢ
ሶሪያ እንደተገኘ-
በባዕድ ስሜት ተውጬ- ስልልሽ ‹‹ያላህ
ያረቢ››
አክሱም ጽዮንን አጥፍቶ- ለደብረ ጽዮን
የሚሰግድ፤
የሚረዳኝ ብቸኛ ጌታ -
ጌታቸው ረዳ ነው ብሎ - እግዜር አላሁን
የሚክድ፤
ሲገድል ጀጋኑ የሚባል - ሲሞት ንጹሕ
የሚሆን፤
ከተኩሶ ክሱ በርትቶ - ሲለቀልቀኝ
እድፉን፤
ታጣቂ ካላየ በቀር-
መባረቅ የማያሰኘው - መተኮስ
የማይችል ክላሽ፤
መያዜን ያወቀ ውርጋጥ -
ተኩሶ ከሸሼ ወዲያ - እኔን ሲያደርገኝ
ተከሳሽ፤
እናም እናታለሜ-
እንደ አምናው ሁሉ ዘንድሮም - ነፍሴን
ልሰጥሽ ወጥቼ
ጠላትሽን ከመታሁ ወዲያ -
እያነባሁ ነው የወጣሁ - ምድሩ ላይ
አንቺን አጥቼ፡፡

Read 1969 times