Print this page
Sunday, 11 July 2021 18:37

ፖለቲከኞች ህዝቡን “ፕራንክ” እንደሚያደርጉት በጥናት ተረጋገጠ

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(4 votes)

 እኔ በግሌ “ፕራንክ” የሚሉት ነገር ብዙም አያዝናናኝም፡፡ ሰውን መሸወድ፣ ማጃጃል፣ማታለል፣ ማደናገር፣ ማስደንገጥ ወዘተ… ልዩ  ጥበብ ወይም ችሎታ አይጠይቅም፡፡ ድፍረት ብቻ ነው የሚፈልገው፡፡ እንደውም ፕራንክ አንዳንዴ ከ”አፕሪል ዘ ፉል” ጋር  ይመሳሰልብኛል፡፡ በእርግጥ “አፕሪል ዘ ፉል” በዓመት አንዴ ነው የሚመጣው፡፡
በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ህዝቡን ፕራንክ እንደሚያደርጉት ሳይንሳዊ ባልሆነ ጥናቴ አረጋግጫለሁ (ስፖንሰር ሳገኝ ደግሞ ሳይንሳዊ ጥናት አደርጋለሁ) የፖለቲከኞች ፕራንክ ብዙም ባያዝናና፣ ለክፉ አይሰጥም በጥናቴ እንደተገነዘብኩት መቼም ከሃሰተኛ ትርክትና የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ በስንት ጣዕሙ! በእርግጥ  እንዳልኳችሁ ፕራንክ ብዙም አልወድም፡፡ ሰሞኑን  ግን ድንገት ሳላስበው በዩቲዩብ የተመለከትኩት ፕራንክ አስደምሞኛል፡፡ አንዳች ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ሆኖም  አግኝቼዋለሁ፡፡ ለመሆኑ በዩቲዩብ የተመለከትኩት ፕራንክ በምን ዙሪያ ያጠነጥናል? “መንገደኞችን በሃሰት መረጃ ግራ ለማጋባት” የተሰራ” ነው-ፕራንኩ፡፡ እኔ እንደ ሶሻል ኤክስፐርመንት ነው የቆጠርኩት፤ በእርግጥም ነው፡፡ እስቲ ካየኳቸው ጥቂቶቹን ላጋራችሁ!
አንዲት ወፈር ያለች ሞንዳላ ሴት፣ ከስራ ወደ ቤቷ የምትጓዝ ትመስላለች፡፡ እናም ፕራንክ ለማድረግ ካሜራቸውን ደግነው የተሰማሩ ወጣቶች ወጥመድ ውስጥ ትገባለች፡፡ አንደኛው ይቀርባትና “ሲስቱ፤ እዛ ጋ ከ50 ኪሎ በላይ የሆነ ሰው ማለፍ አይቻልም፤ተብሏል ሰው እየመዘኑ እየመለሱ ነው፤ ብትመለሺ ነው የሚሻልሽ” ይላታል-ፍርጥም ብሎ፡፡ የሚገርመው ነገር፣ ይህች ሴት ወዲያው ግራ ተጋብታ ትቆማለች፡፡ ሁለተኛው ወጣት ይከተልና ያንኑ መረጃ ይደግምላታል፡፡ (ወጣቶቹ የማይተዋወቁ መስለው ነው የሚሰሩት) ይሄኔ አላመነታችም፡፡ ፊቷን አዙራ ወደመጣችበት መንገድ ጉዞ ጀመረች፡፡ ወጣቶቹ ደርሰውባት ፕራክ መሆኑን ባይነግሯት ሄዳ ነበር፡፡  እኔን የገረመኝ መረጃውን ላትጠይቅ-ሳትመረምር አምና መቀበሏ ነው፡፡ ቆይ ከመቼ ወዲህ ነው ሰው  እየተመዘነ፤ በመንገድ የሚያልፈው? ሴትየዋስ እንዴት ጥያቄስ አታነሳም? ግራ ያጋባል!! (ግን ምንም ነገር ሳናጣራ መቀበል ለምዶብናል!)
አንድ ልጅ እግር ደግሞ (ከገበያ ሳይሆን አይቀርም) የሸማመተውን ሸክፎ ተፍ ተፍ ይላል- ወደ ቤቱ ይመስላል። ከፕራንክ አድራጊዎቹ አንዱ፤ “ጀለስ፣ ድንች ከ1 ኪሎ በላይ አያልፍም እየተባለ ነው፤ እንዳይቀበሉሽ… ተመለሺ!” ይለዋል። ልጅ እግሩ ትንሽ ተደናገረና መንገዱን ቀጠለ። መረጃው የተዋጣለት አይመስልም። ሁለተኛው ፕራንክ አድራጊ ተመሳሳይ መረጃ ይነግረዋል፡፡ ይሄኔ ሳያመነታ  ቀኝ ኋላ ዙር ብሎ ወደ መጣበት ተመለሰ- ድንቹን እንዳይነጠቅ በመፍራት፡፡ ይሄም ልጅ “ድንች ከ1 ኪሎ በላይ አያልፍም…” ሲሉት እንዴት እንዳመናቸው ፈጽሞ አልገባኝም፡፡ (ድንች የከበረ ማዕድን ሆነ እንዴ?)
ሌሎች ሁለት ጎረምሶች ደግሞ እያወጉ ይጓዛሉ፡፡ ፕራንክ አድራጊዎቹ በቅርብ ርቀት አነጣጥረውባቸዋል፡፡ እንደተለመደው አንደኛው ጠጋ ይላቸውና፤ “ ፍሬንዶች፤ እዛ ጋ ማይክል ጃክሰን እየዘፈነ ነው፤ መንገድ ተዘግቷል፣ ወደ ላይ ብቻ ነው የሚፈቀደው … አልሰማችሁም?!” ጎረምሶቹ አልተገረሙም፤ አልተደነቁም፡፡ ያውም የማይክል ጃክሰን ስም ተጠርቶ! ለአፍታ ግር ተሰኝተው ቆሙ። ሁለተኛው መጥቶ ያንኑ ደገመላቸው፡፡ ተያይዘው ወደ መጡበት መመለስ ጀመሩ። (ግዴላችሁም የተነገረውን ሁሉ መቀበል ለምዶብናል!)
እኒህ ፕራንክ አድራጊዎች  “እዛ ጋ አንበሳ ሰው እየፈጀ ነው!” በሚልም መንገደኞችን ሲያስደነግጡና ሲያስበረግጉም ይታያል። “ከአንበሳ ግቢ አንድ አንበሳ አምልጦ እዛ ጋ ሰው እየፈጀ ነው… ይቅርብህ… ብትመለስ ነው የሚሻልህ” ሲሉ መንገደኛው ሁሉ በድንጋጤ እየራደ እግሬ አውጭኝ ለማለት ሲዘጋጅ ይታያል፡፡ ቶሎ ፕራንክ መሆኑ ባይነገራቸው፣ መጭ ማለታቸው አይቀርም ነበር፡፡
እኒህኞቹ እንኳን ብዙም አይፈረድባቸውም፡፡ “አንበሳ ሰው እየፈጀ ነው” ተብለው ከመፈርጠጥ ውጭ ሊጠይቁና ሊያጣሩ አይችሉም፡፡ (ድንጋጤው ራሱ ዕድል አይሰጣቸውም!)
በፕራንኩ (የሽወዳ ድራማ በሉት) እንዳየነው ሁሉ፤ በተለያዩ ጊዜያት ሆነ ተብለው በማህበራዊ ሚዲያ በተሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች ሳቢያ፣ ብዙዎች ለውዝግብና አንዳንዴም ለግጭት  ተዳርገው አይተናል፤ ሰምተናል እውነቱን ከውሸቱ ማጣራትና መለየት እየተሳነን፡፡
በቅርቡ የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ያደረገውን ስብሰባ ተከትሎ፣ “ጠ/ሚኒስትሩ በስብሰባው ላይ የተናገሩት ነው” በሚል የወጣው ሃሰተኛ እና አደገኛ ኦዲዮ ትዝ አይላችሁም? በዚህ ሃሰተኛ ኦዲዮ  ሳቢያ ለጥቂት ቀናትም ቢሆን እንደታመስን አይዘነጋም፡፡ በርግጥ ዓላማው  ከዚያም በላይ ነበር፡፡ በህዝብና በመንግስት መካከል ጥርጣሬና ቅራኔ በመፍጠር፣  ግጭት ተቀስቅሶ አገርን ማመስ ነበር- በአጭሩ ተቀጨ እንጂ!
በዚህ ሃሰተኛ ኦዲዮ  የተሸወዱት ደሞ ተራ ተርታ ዜጎች ብቻ አይደሉም። “የነቃን የበቃን ጋዜጠኞችና ተንታኝ አክቲቪስቶች ነን” የሚሉም መረጃውን ሳይመረምሩና ሳያጣሩ በቀጥታ ወደ ማራገብ መግባታቸውን ታዝበናል፡፡ በእርግጥ ይሁነን ብለው የተሸወዱ  አይጠፉም፡፡  በተለይ ብልፅግናንና  ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይን አብዝተው የሚቃወሙ ሳይሆን “የሚጠሉ” ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች፣ ይህን መረጃ  ለቀናት ትንተና ሲሰጡበትም ታይተዋል-  “እስከ ዛሬ ጠ/ሚኒስትሩን ስንተችና ስናብጠለጥል የቆየነው ዝም ብለን አይደለም፤ በምክንያት ነው፤ ይሄው ማስረጃው” በሚል መታበይ!!
በነገራችን ላይ ዛሬ ለብዙ ጣጣ የዳረገን የትግራይ ቀውስን በጥሞና ከመረመርነው፤ መነሻው ሃሰተኛ መረጃና ፕሮፓጋንዳ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ አክራሪው የህወሃት ዘረኛ  ቡድን፤ ቢያንስ ለ3 ዓመታት ትግራይ ከትሞ በህዝቡ ውስጥ የዘራው ሃሰተኛ ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ ለዚሁ ሁሉ እልቂትና ውድመት የዳረገን፡፡
እንደ ህወኃት ያሉ የዘር ፖለቲካን የሚያቀነቅኑ  አክራሪ የብሔር ፓርቲዎችም ዋነኛ መሳሪያቸው  ሃሰተኛ ትርክትና የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ  ነው። ደጋፊዎቻቸውን የሚያሰባስቡትና የሚያበዙት…“ተበድለሃል…”፣ “ተፈልጠሃል”፣ “ተቆርጠሃል” … “ተገርፈሃል”፣ “ተጨቁነሃል” ወዘተ…. የሚሉ የሃሰት ትርክቶችን ፈጥረው ነው፡፡ ያለዚያ ለደጋፊው የሚሰጡት ነገር የላቸውም (ያሳዝናል-ጥላቻ ዘረቶ ደጋፊ ማሰባሰብ!)፡፡
መሰል የቂምና የጥላቻና  ፕሮፓጋንዳ ደግሞ የት እንዳደረሰን በደንብ አይተነዋል። ስንቶች በዘር ተኮር ጥቃት እንዳለቁ፣ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለጎዳና እንደተዳረጉ፣ በገዛ ሃገራቸው ስደተኞች እንደሆኑ… አሳምረን የምናውቀው ነው፡፡ ብዙዎቹ የጥላቻና የበቀል ትርክቶች ደግሞ በፖለቲካ ልሂቃን ሆነ ተብሎ የሚፈበረኩ ናቸው፡፡
(ገበሬማ ያመርታል እንጂ ጥላቻ አይፈበርክም) ለዓመታት የተሰራጨውን የዘረኝነት ደዌና ጥላቻ በአንድ ጀምበር ማፅዳት  አይቻለንም፡፡ ዘሩን ለመዝራት ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ የፈጀውን ያህል፣ ከስሩ ነቅሎ ለማምከንም ዓመታትን መፍጀቱ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በምትኩም ፍቅርን፣ በጎነትን፣ መተሳሰብን፣ ዕውቀትን መትከል ይሻል፡፡
እስከዚያው ግን ቢያንስ በእኩይ ወገኖች ሆነ ተብሎ የሚሰራጩ  ሃሰተኛ መረጃዎችና የፈጠራ ወሬዎች ተቀብሎ ከማራገብ በመቆጠብ፣ እንዴትና ወዴት ብለን የምንጠይቅ፣ ምክንያታዊ ዜጎች እንሆን  ዘንድ ብዙ ትጋት ይጠበቅብናል፡፡
መግቢያዬ ላይ ስለ ፖለቲከኞች ፕራንክ አንስቼ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ፕራንክ ብዙም አያዝናናም እንጂ ሁልጊዜ ያደርጉናል ፕራንክ፡፡ ህዝቡን ብቻ ግን እንዳይመስላችሁ፡፡ ሲመቻቸው መንግስትንም ፕራንክ ያደርጉታል፡፡ እርስ በርሳቸውም ፕራንክ ይደራረጋሉ። ተቃዋሚዎች ለተቃዋሚዎች፡፡ ለምሳሌ የፕ/ር መረራ ኦፌኮ ፓርቲ የመድረክ አባል የነበረውን፣ የፕ/ር በየነ ጴጥሮስን ፓርቲ ፕራንክ ሊያደርገው ይችላል፡፡ (እስካሁንም ሳያደርገው አይቀርም!)
መጀመሪያ ላይ እንዳልኳችሁ እኔ በግሌ ፕራንክ አይመቸኝም፡፡ ሳይንሳዊ ባልሆነ ጥናቴ እንዳረጋገጥኩት ደግሞ ፖለቲከኞች ፕራንክ  ሲያደርጉ… እነሱ ብቻ ናቸው የሚያውቁት፡፡ እስካሁን ድረስም ፕራንክ ማደረጋቸውን በይፋ አላመኑም፡፡ እኔም ያወቅሁት ሳይንሳዊ ባልሆነ ጥናቴ አማካኝነት ነው፡፡   በቅርቡ ማንም ሰው በፖለቲከኞች ፕራንክ ሲደረግ የሚያውቅበትን  ዘዴ የሚያስተምር መፅሐፍ ለማሳተም አቅጃለሁ። (ግን ስፖንሰር ያስፈልገኛል!) የሚገርመው ደግሞ ፖለቲከኞች ወይም ፓርቲዎች ህዝብን በጅምላ ነው ፕራንክ የሚያደርጉት (የሚሸውዱት ማለት ነው!) ግን ፕራንክ  እንዳልኳችሁ ፕራንክ መሆኑን ትንፍሽ አይሉም፡፡ ከነቃችሁባቸው ነቃችሁባቸው!
አምና ኮቪድ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ፣  በግንቦት 2012 ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው 6ኛው አገራዊ ምርጫ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ መወሰኑ ይታወሳል፡፡ ምርጫው ሲራዘም የመንግስትም የሥልጣን ዘመን  አብሮ ተራዘመ፡፡ ፓርላማም አንድ ዓመት ተጨመረለት፡፡ ይሄን ጊዜ ታዋቂው አክቲቪስት ጃዋር መሃመድና አንጋፋው  ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌው ድንገት ህብረት ፈጠሩና ሁላችንንም ፕራንክ አደረጉን-መንግስትንም አልቀረለት! ግን  እንደተለመደው ፕራንክ መሆኑን አልነገሩንም፡፡ (የፖለቲከኞች ፕራንክ ችግሩ ይሄ ነው!) እናላችሁ… “ከመስከረም” 25 ወይም 30 በኋላ በእኛና በጠ/ሚኒስትሩ መካከል  ልዩነት የለም፤ አንድ ነን፤ ከዚያን ቀን በኋላም አገሪቱን የሚያስተዳድር ህጋዊ መንግስት አይኖርም” እያሉ በአደባባይ ደሰኮሩ፡፡ ብዙዎች ደንግጠው ነበር፡፡ በአመፅ አገሩን ሊያምሱት ነው ብለው፡፡ ግን አመፅ አይደለም፡፡  ፕራንክ ነው ያደረጉን፡፡
በነገራችን ላይ እኔም ራሴ ፕራንክ መደረጋችንን ያወቅሁት ከዓመት  በኋላ ነው፡፡ ፕራንክ ባይሆንማ… እነ አቶ ልደቱ እንዳሉት፤ ከመስከረም 25 በኋላ ህጋዊ መንግስት አይኖርም ነበር፡፡ ህገ-መንግስታዊ ቀውስም (Constitutional Crisis) በተከሰተ፡፡ እንደተፈራውም አመፅ አልተቀሰቀሰም፡፡ የሚገርመው ሁለቱም ፖለቲከኞች ከተናገሩት በኋላ ረስተውታል። (ፕራንክ ነዋ!) ሌላም ልንገራችሁ፡፡ ምርጫ ቦርድ ሥራ በዝቶበታል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለ6ኛው አገራዊ ምርጫ  ዝግጅት ላይ ናቸው፡፡ በኮቪድ ሳቢያ የተራዘመው ምርጫ ከ1 ዓመት በኋላ ሊደረግ ነው። ሁሉም የዲሞክራሲ ሥርዓት ይተክላል የተባለለትን ምርጫ ለማድረግ ጓጉቷል፡፡ በዚህ መሃል እነ አቶ ልደቱ ግን ምርጫውን መደረግ የለበትም ብለው መቃወም ጀመሩ። “አሁን ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ምርጫ ሳይሆን አገራዊ መግባባት ነው” በሚል አቶ ልደቱ ፕራንክ እንዳደረጉን ያወቅኩት መቼ መሰላችሁ? በምርጫው እንደሚወዳደሩ ስሰማ! በርግጥ  መጨረሻ ላይ በምርጫው ሳይወዳደሩ ለልብ ህክምና ወደ አሜሪካ ተሻግረዋል፡፡ (ይሄ ፕራንክ ይሆን እንዴ?)
አንድ የመጨረሻ የፓርቲዎች ፕራንክ ልንገራችሁና ልሰናበት፡፡ በአንጋፋው ፖለቲከኛ ፕ/ር መረራ ጉዲና የሚመራው ኦፌኮ፤ በ11ኛው ሰዓት ላይ ራሱን ከምርጫው ማግለሉን ሲገልጹ አላመንኩትም ነበር፡፡ አገራዊው ምርጫ በተካሄደ ማግስት ታዲያ ፕሮፌሰሩ ሁላችንንም በጅምላ ፕራንክ አደረጉን፡፡
መንግስትና ምርጫ ቦርድንም ጨምሮ ፕሮፌሰሩ “በ6ወር ውስጥ ምርጫ መካሄድ አለበት” የሚል መግለጫ አወጡ። ፕራንክ መሆኑን ከእኔ በቀር ብዙ ሰው  ያወቀ  አይመስለኝም፡፡ ብዙም ሳይቆዩ ባለፈው ሳምንት ደግሞ ፓርቲቸው ኦፌኮ ከአቶ ዳውድ ኢብሳ ኦነግ ጋር ጥምረት በመፍጠር በድጋሚ ፕራንክ አደረጉን- “የኦሮምያ የሽግግር መንግስት መስርተናል” በማለት፡፡ ድሮ ቢሆን እኮ ፕራንክ መሆኑን የምናውቀው ዓመታት ከተቆጠሩ በኋላ ነበር፡፡
አሁን ግን የፖለቲከኞችን ፕራንክ በቅጡ እያጠናን ስለመጣን  በትኩሱ እያወቅንባቸው ነው፡፡ እነሱ ግን አሁንም   ፕራንክ መሆኑን ትንፍሽ አይሉም፡፡ አጃኢብ ነው!

Read 1348 times