Sunday, 11 July 2021 18:36

የአብዮቱ ዘመን ውይይቶችና አመለካከቶች (1966-1969)

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 በኢትዮጵያ የብሔሮች ጥያቄ በ1966 የሕዝባዊ ንቅናቄ ዘመን ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል አንደኛው ነበር፡፡ በአብዮቱ ከተሳተፉት ድርጅቶች መካከል መኢሶንና ኢጭአት የ1963ቱን የተማሪ ማኅበራት ውሳኔ በማራመድ ለብሔሮች መብት መታወቅና መከበር በመታገል እንደፀኑ ቆዩ፡፡ ኢሕአፓም አልፎ አልፎ ከታዩት የአንዳንድ የአመራሩ መዛነፎች በስተቀር፤ በ1963 መንፈስ ቆይቷል፡፡ ደርግ በሌላው በኩል ግን፣ ከ1966 እስከ 1969 እና ከ1970 በኋላ በኢትዮጵያ ብሔሮች ጥያቄ ረገድ፣ ለ17 ዓመታት የሄደበት መንገድ ሁሌም አንድና ያው አልነበረም፡፡ አካሄዱን በሶስት ወቅቶች ከፍሎ ማጤኑ ሂደቱን ግልፅ  ሊያደርግ ይችላል፡፡
የመጀመሪያው፣ ከሰኔ/ሐምሌ 1966 እስከ ህዳር/ታህሳስ 1967 የነበረው ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅት ደርግ በአንድ በኩል በሐምሌ 2፣ 1966 መግለጫው፡
“(ደርግ) በኢትዮጵያውያን መሀከል ለብዙ ዘመናት የቆየውን በጎሳና በሃይማኖት የተመሰረተውን መለያየትና የኑሮ መራራቅ ኢትዮጵያ ትቅደም በሚል እምነት፣ በብሔራዊ ዋስትና በእኩልነት፣ ለአገር ዕድገትና መሻሻል ዓላማ ሕዝቡ ለሥራ ታጥቆ እንዲነሳና በዘመኑ ሥልጣኔ በይበልጥ ተካፋይ እንዲሆን የሚቻለውን ሁሉ ያደርጋል”
የሚለውን አመለካከት አራመደ፡፡ በሌላም በኩል፤ በህዳር 1967 ከጄኔራል አማን አንዶም ጋራ በተለይ በኤርትራ ጥያቄ በተፋጠጠ ጊዜ፣ “የኢትዮጵያ አንድነት ፍፁምነት” የሚለውን አመለካከት አራመደ። በወሩ በታህሳስ 1967 “የኢትዮጵያ ህብረተሰባዊነትን” ሲያውጅ ደግሞ፣ “የኢትዮጵያን አንድነት ለማጠናከር ብዙ መንገዶች አሉ” ካለ በኋላ የሚከተሉትን ሁለት መንገዶች አሳወቀ፡-
“በአገር ውስጥ ያለውን የባህሎችና የልዩ ልዩ ጎሳዎች መቀራረብ ይበልጡን ማጠንከር አንደኛው ዘዴ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአንድ ጎሳ ወይም የአንድ ባህል አገር አይደለችም፡፡ የተዛመዱ ልዩ ልዩ ነገድ ባህል የሚገኙባት አገር ናት፡፡ የዘለቄታ ጥንካሬዋ መሰረትም ይኸው ነው፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብሮ በመኖሩ በጋብቻ፣ በባህል፣ በስሜትና በአስተሳሰብ ዝንባሌ፣ በቋንቋ ጭምር የተሳሰረ ነው፡፡ የአንድነትን ማጠንከር አንደኛው ዘዴ እንዲህ ያለውን የሚያስተባብር ነገር ሁሉ እንዲዳብር ማድረግ ነው፡፡ ዋናዎቹ ቋንቋዎች እንዲስፋፉ፣ ባህል ሁሉ እንዲያድግ፣ የሰው ሁሉ መብት እንዲጠበቅና የአገሪቱን ዜጋ ሁሉ በአንድነት ጥላ ስር በፍቅርና በመተባበር እንዲሰባሰብ ማድረግ ያስፈልጋል፤
“ሁለተኛው መንገድ ደግሞ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር በተለይም ከሱዳን፣ ከሶማሊያና ከኬንያ ጋር ተባብራ የምሥራቅ አፍሪካ ሕብረት - አህጉር እንድታቆም ማድረግ ነው”፡፡
ይህ አመለካከት ከደርጉ “ኢትዮጵያ ትቅደም” ዘመን መግለጫዎች ጋራ ሲነፃፀር የተሻለ ነበር፡፡ ደርጉም በዚሁ ጊዜ ታህሳስ 14 ዕለት የእስልምና ሃይማኖት ክብረ በዓሎችን ያካተተውን የብሔራዊ በዓሎች ዝርዝር አውጥቶ ነበር፡፡ በታህሳስ 18 ደግሞ፣ የአዲስ አበባ ራዲዮ ጣቢያ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፋን ኦሮሞ ፕሮግራሞችን ማስተላለፍ ጀመረ። የባለመሬት/ ጭሰኛን የምርት ግንኙነት የሻረው አዋጅ የካቲት 25፣ 1967 ታወጀ፡፡
ሁለተኛው ወቅት፣ የሕዝብ ድርጅት ጊዜያዊ ጽ/ቤት በሚያዚያ 1968 ከተቋቋመ በኋላ ደርግ የብሔርን ጥያቄ ጨምሮ በተለያዩ የፖለቲካ ጥያቄዎች ላይ የአደባባይ ውይይት ክበቦች በየመሥሪያ ቤቱ ተቋቁመው እንዲወያዩበት በፈቀደበት ወቅት ጀመረ፡፡ 1968 በዚሁም፣ በብሔሮች ጥያቄ ላይ ይፋ ውይይቶች የተካሄደበት ዘመን ሆኖ ተጠናቀቀ፡፡
ሦስተኛው ወቅት፣ በሁለተኛው ወቅት ዘመን፣ ከታህሳስ 1968 አንስቶ እስከ የካቲት 1969 ድረስ በደርግ መሪዎችና በሕዝብ ድርጅት ጊዜያዊ ጽ/ቤት አባል ድርጅቶች መካከል ረጅም ውይይቶች የተደረጉበት ወቅት ነበር፡፡ ደርግም የመጨረሻ መጨረሻ፣ “የራስ-ገዝ አስተዳደር” የተባለውን የአስተዳደር መንገድ እስከ መቀበል ድረስ የሄደበት ወቅት ነበር፡፡
ይሁን እንጂ፣ በ1969/70 የኢትዮጵያን አገር ወዳድ ተራማጆችና ምሁራን አጥፍቶና አግልሎ ሥልጣንን ለመጠቅለል የበቃው የኮሎኔል መንግስቱ የመለዮ ለባሾችና ከፍተኛ ቢሮክራቶች ቡድን፣ በ1970 “የራስ-ገዝ አስተዳድር” የተባለውን ትቶ፣ “አንድ ሰውና አንድ ጠመንጃ እስኪቀር ድረስ” ያለውን አካሄድ ያዘ፡፡
ይህም አራተኛው ወቅት ሲሆን፣ ሻለቃ መንግሥቱ “የአብዮቱ ማዕከል; እየተባሉ የተሞካሹበት፤ “የምሥራቁን ድል በሰሜን እንደግመዋለን”፤ “አንድ ሰውና አንድ ጠብ- መንጃ እስኪቀር ድረስ” በሚሉ ጥሪዎች፣ የኢትዮጵያን የብሔሮች ጥያቄ በጦር ኃይል “ለመፍታት” የተሄደበት መንገድ ነበር፡፡ በኋላና ባለቀ ሰዓትም፣ “የብሔሮች ኢንስቲቱት” የተባለው ተቋም የተመሰረተበት ወቅት ነበር፡፡ ጦርነቱ በግንቦት 1983 በኤርትራ ግንባሮችና በሕውሓት በሚመራው ኢሕአዴግ አሸናፊነት ተደምድሞ ኮሎኔል መንግሥቱ ወደ ዚምባብዌ ሸሹ፡፡ ኢሳይያስ አፈወርቂ በኤርትራ ነገሠ፡፡ ኢሕአዴግ የአዲስ አበባን ሥልጣን ያዘ፡፡
የፖለቲካ ግድያና የጦርነቶች ዓመታት (1969-1983)
የ1969 መጨረሻና የ1970 መጀመሪያ ዓመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አንድ አገር ወዳድና ተራማጅ ትውልድ፣ በኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማርያም መሪነት በተመለመሉ ገዳይ ቡድኖች ተጨፍጭፎ ያለቀበት ወራት ነበሩ፡፡ በዚሁም፣ የ1963ቱ ውሳኔዎች ባለቤት የነበረው አገር ወዳድና ተራማጅ ትውልድ፣ ከ1970 በኋላ በነበረው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ህይወት ውስጥ ይህ ነው የሚባል ሥፍራና ሚና ላይኖረው እስኪሆን ድረስ ተዳክሞ አበቃ፡፡ ከ1970 እስከ 1983 ባሉት የ13 ዓመታት ዘመን ዋና ተዋናዮች ሆነው የቀጠሉት ከላይ እንደተመለከተው ስለዚህም፤ በአንድ ወገን በኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም መልማይነትና መሪነት ከ1970 ጀምሮ የመንግሥትን ሥልጣን የጨበጠው የመለዩ ለባሾችና የከፍተኛው ቢሮክራሲ ቡድንና፤ በሌላው ወገን የኤርትራ ግንባሮችና የተለያዩ የብሔር ድርጅቶች (በተለይም ሕውሓት፣ ኦነግ፣ የሲዳማና የሱማሌ) ነበሩ፡፡
ሕውሓት “የኢትዮጵያ ዓቢይ ቅራኔ በብሔሮቿ መካከል ያለው ቅራኔ ነው” ባለው የቅራኔ አረዳዱ ገፋ፡፡ ከዚያም ከሌሎቹ የትግራይ ድርጅቶችና እስከ መንግሥት ሠራዊት፣ ከኢሕአፓ እስከ ኢዲዩ ጋራ ድረስ ካሉት ኃይሎች ጋራ ተዋጋ፡፡ ከተጠቀሱት ኃይሎች ጋር ያካሄዳቸው ውጊያዎች ስለሚታወቁ አልመለስባቸውም፡፡ በዚሁ ዘመን “የኢትዮጵያን ቅኝ አገዛዝ” ሲዋጉ የነበሩት የኤርትራ፣ የሱማሌያ ግንባሮችና ኦነግ የሄዱባቸው መንገዶችም ስለሚታወቁ እንደዚሁ አልመለሰባቸውም፡፡ እንደዚሁም፣ ሕወሓት ከኢሕአዴግ አመሠራረት እስከ ኤርትራ ሬፈረንደም፣ ከሕገ-መንግሥቱ መረቀቅና መታወጅ እስከ “የፌዴራል” አስተዳደር አወቃቀር ድረስ የሄደባቸው መንገዶች ስለሚታወቁ አልቆይባቸውም፡፡
በአጭሩ፣ ኢሕአዴግ ከ1983 እስከ 2010 ድረስ “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” ባለው አደረጃጀትና አመራር ለ27 ዓመታት ገዛ፡፡ እንዲያም ሲል ለ27 ዓመታት ሙሉ በአንድ ወገን ፌደራላዊ ባልሆነው “የፌደራል አስተዳደር” ግዛቶችን ሲከልልና ሲያጥር ኖረ፡፡ የነፃ ገበያም ሆነ የመንግሥታዊ ካፒታሊዝም ባልሆነው የኢሕአዴግ “ካፒታሊዝም” “ኪራይ ሰብሳቢ” ያላቸውን ሲፈለፍል ኖረ፡፡ በሌላው ወገን፤ ኦነግ፣ የሲዳማ፣ የአፋር፣ የሱማሌና ሌሎች በ1983 ሥልጣንን የተጋሩ ቢሆንም፤ ከጥቂት ወራት በኋላ በኢሕአዴግ ተገፍተው ተሰናበቱ። ኦነግ ከዛም፣ ከ10 በማያንሱ ቡድኖች ተከፋፍሎ በየውጭ አገራቱ ሲንቀሳቀስ ቆየ።
(ከአንዳርጋቸው አሰግድ "ቅን ፍላጎት እስካለ መንገድ አለ" መጽሐፍ የተቀነጨበ፤ 2013 ዓ.ም)Read 2295 times